ድጋፍ ሰጪ አውቶቢሶች እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ እንደሚሠሩ ታወቀ

Views: 134

በአዲስ አበባ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኙት ድጋፍ ሰጪ ከተማ አውቶብሶች ለስድስት ወራት ተብሎ የነበር ቢሆንም እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ ድረስ ድጋፍ መስጠት እንደማያቋርጡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ስጦታው አከለ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርቱን ችግር በመመልከት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ድጋፍ በማድረጉ እስከ ሰኔ ወር ድረስ አገልግሎቱን እንደሚቀጥሉም አየያይዘው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለሌላ ስራ በመፈለጋቸው ከአምስት መቶ አውቶቢሶች ኹለት መቶ የሚሆነት ድጋፍ ሰጪ አውቶቢሶች ድጋፍ መስጠት አቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።
አሁን ግን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ስጦታው የታሪፍ ማሻሻያን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የታሪፍ ማሻሻውን በተመለከተ ባለፉት ኹለት ወራት በነዳጅ ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አክሎ አስታውቋል።
ይህ ማሻሻያ ሲደረግ ግን የድጋፍ ሰጪ አቶቢሶችን እንደማይመለከት እና ከዚህ ቀደም ሲሰሩበት በነበረው ታሪፍ እንደሚቀጥሉም ስጦታው ተናግረዋል።
የታሪፍ ማሻሻያው የነዋሪውን የኑሮ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በሚኒ ባስ እና በሚድ ባሶች ላይ ብቻ ጭማሪ የተደረገ መሆኑንም ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደ ኪሎ ሜትሩ ሁኔታም ጭሪው እንደሚለያይ የገለፁ ሲሆን በዚህም ሚኒ ባሶች ላይ የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከ 50 ሳንቲም እስከ ሦስት ብር ድረስ እንደሚሄድ አዲስ ማለዳ ካየችው መረጃ ለማወቅ ችላለች።
በሚኒ ባስ ወይም ታክሲዎች ላይ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪን በተመለከተ እስከ ኹለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ይከፈል የነበረው ኹለት ብር ሲሆን ምንም ጭማሪ ሳይደረግበት ባለበት እንዲቀጥል ተደርጓል።
ከኹለት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር እስከ አምስት ኪሎ ሜትር አራት ብር የነበረው አራት ብር ከ 50 ፣ ከ አምስት ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር እስከ ሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ስድስት ብር የነበረው ስድስት ከሀምሳ መግባቱን አክለው አስረድተዋል።
ከ 10 ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር እስከ 12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ 10 ብር የነበር ሲሆን 11 ብር ፣ ከ 15 ነጥብ አንድ እስከ 17 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር 13 ብር የነበረው 15 ብር ከ50 ሳንቲም እንዲሁም ከ 17 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር እስከ 20 ኪሎ ሜትር 15 ብር የነበረው 17 ብር ከ 50 ሳንቲም መሆኑም ተመላክቷል።

ሚድ ባስ ላይ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪም እንደየ ኪሎ ሜትሩ ከአንድ ብር ጀምሮ እስከ ኹለት ብር ድረስ ጭማሪ መደረጉንም ኃላፊው አስታውቀዋል።
ሚድ ባስ ወይም የሃይገር ላይ የተሻሻለው ታሪፍ እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር ሦስት ብር የነበረው ባለበት የሚቀጥል ሲሆን ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ ያሉት ላይ አንድ አንድ ብር ጭማሪ ተደርጎባቸዋል።
በዚህም ከ ስምንት እስከ 12 ኪሎ ሜትር አራት ብር የነበረው አምስት ብር ፣ ከ 12 ኪሎ ሜትር እስከ 16 ኪሎ ሜትር 5 ብር የነበረው ስድስት ፣ 7 ብር የነበረው 8 ብር ፣ ስምንት ብር የነበረው ዘጠኝ ብር ሲሆን ከ 24 ኪሎ ሜትር እስከ 28 ኪሎ ሜትር ያለው ግን ኹለት ብር በመጨመር 11 ብር መግባቱም ተነግሯል።

ከስድስት ወር በፊት ጳጉሜ ኹለት ቀን 2012 ዓመት ላይ ከመኪና መለዋወጫ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ጋር በተያያዘ የከተማዋ ትራንስፖርት ማሻሻያ መደረጉም ተጠቁሟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com