ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ሊሰጥ ነው

Views: 142

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) በመስመር ዝርጋታ የማያዋጣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቦታዎች ላይ በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ለደንበኛቹ ለማቅረብ ስምምነት ተፈራረመ።
የኤሌክትሪክ ኃይል ለኅብረተሰቡ በኹለት መንገድ እንደሚደርስ እና ከዋናው መስመር በጣም የራቁ እንዲሁም በመስመር ኃይል ለማቅረብ እጅግ ከፍተኛ ወጭ ለሚጠይቁ 25 የገጠር ከተሞች ከፀሃይ ኃይል በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል መብራት በስድስት ወራት ውስጥ እንዲያገኙ የሚያደርግ ስምምነት መፈራረማቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒዩኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መላኩ ታዬ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለው 25ቱ የገጠር ቀበሌዎች የተመረጡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰነው መሰረት እና ለክልሎች ኮታቸውን ተጠቅመው በራሳቸው መስፈርት ቦታ መርጠው ይልካሉ ብለዋል። አሁን አገልግሎት ከሚያገኙ 25 የገጠር ቀበሌዎች መካከል ስምንት ከኦሮሚያ ክልል አምስት ከአማራ ክልል እና አራት ከደቡብ ክልል የሚገኙ ከተሞች እንደተካተቱበት ለማወቅ ተችሏል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የሥራ እድል በመፍጠር እና የእውቀት ሽግግር ከማምጣት ባለፈ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምርም ከ145 ሺሕ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታውቋል።

ስምምነቱን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ በተገኙበት ከስራ ተቋራጮቹ ጋር ተፈራርመዋል። ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና ከኢትዮጵያ መንግስት ማለትም ከተቋሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት 161 ሚሊየን ብር የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል። አጠቃላይ ስምንት ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ኘሮጀክት 68 ነጥብ ሰባት የመካከለኛ እና 233 ነጥብ ሦስት ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ይከናወንበታል ተብሏል።

ይሕንን ሥራ ለመሥራት ዓለማቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊ ለሆኑ ሦስት የቻይና እና አንድ የኮሪያ ድርጀት መሰጠቱን የኮርፖሬቱ የኮሚውኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ተናረዋል። ሥራው በስድስት ወራት ውስጥ በስድስት ምዕራፍ ተከፈሎ ይገነባል ተብሏል። በምዕራፍ አንድ በአማራ ክልል ታች አርማጭሆ ወረዳ ደለሳ ከተማ (ቀበሌ) ፣ምስራቅ በለሳ ወረዳ አርባ ፀጉር ከተማ፣ ተኩሳ ወረዳ በግ መንክር ከተማ፣ አለፍ ወረዳ ፈንጅት ከተማን እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክል ጉባ ወረዳ አልማሃል ከተማ በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
በምዕራፍ ኹለት በኦሮሚያ ክልል አሬሮ ወረዳ መልካሃሉ ከተማ ሲሆን በምዕራፍ ሦስት በሶማሌ ክልል በምዕራፍ አራት በኦሮሚያ ክልል አና ሶራ ወረዳ አደሌ ከተማ፣ ጎሎልቻ ወረዳ ድሬ ሸክ ሁሴን ቀበሌ፣ ሃዊ ጉዲና ወረዳ ቢሊቃ ከተማ፣ ሃዊጉዲና ወረዳ ቃበናዋ ከተማ፣ አና ሶራ ወረዳ ሳይ ከተማ፣ ጉራዳሞሌ ወረዳ ሆኮልቱ ከተማ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

በ2013 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ለ125 አዳዲስ የገጠር መንደሮች እና ትንንሽ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተገልጿል። የኤሎክትሪክ መረብ በማይደርስባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በታቀደው መሰረት ባለፈው 2012 የበጀት ዓመት ግንባታቸው ተጀምሮ ከነበሩት 12 ያህል የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስምንት ያህሉ ተጠናቀው ሥራ መጀመራው ተገልጿል። ከቀሪዎቹ አራቱ ውስጥ አንዱ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሳይጠናቀት መቆየቱን መላኩ ገልጸዋል።

መላኩ አክለውም በጄኔሬተር ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ የአገራችን ክፍሎች መኖራቸውን አስታውሰው በተለይ ደግሞ በሱማሌ ክልል የሚገኙ አካባቢዎች በጂኔሬቴር የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት ያገኛሉ ብለዋል። አሁን ካለው የነዳጅ ዋጋ መናር ጋር ተደማምሮ በጄኔሬተር የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com