በክልሎች ከተሞች ነዳጅ በጥቁር ገበያ እስከ 70 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው

Views: 143

በአገራችን የተለያዩ የክልል ከተሞች አንድ ሊትር ነዳጅ በጥቁር ገበያ ከ50 ብር እስከ 70 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ተናገሩ።
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ ነዳጅ በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ እየተሸጠ እንደሆነ የተናገሩት አሽከርካሪዎቹ እሱንም ለማግኘት ከፍተኛ የሆነ ሰልፍ እንዳለ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው በባህር ዳር ኑሮውን ያደረገው የባጃጅ ሹፌር እንደተናገረው ነዳጅ ለማግኘት በየቤንዚን ማደያው ከፍተኛ ሰልፍ መኖሩን እና ከነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።ለመኖር መስራት አለብኝ ያለው ሹፌሩ በጥቁር ገበያ ነዳጅ ከሚሸጡ ሰዎች አንድ ሊትር ቤንዚን ከ 60 እስከ 70 ብር እየገዛ እንደሆነ ተናግሯል።

አንድ ሊትር እስከ 70 ብር ገዝተን ምንም ስለማያተርፈን መንቀሳቀስ አልቻልንም እሱም ቢሆን በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ ለመግዛት ጭምር ከፍተኛ የሆነ ሰልፍ አለ ብሏል።
በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ እንዲሁ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ከነዳጅ ማደያዎች ጋር በመደራደር ነዳጅ ገዝተው ያስቀመጡ ባለሀብቶች የፈጠሩት ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት በከፍተኛ መልኩ ሀዋሳ ነዳጅ እንዳይገኝ በማድረጉ በጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ነዳጅ 50 ብር እየተሸጠ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡

በ 26 ብር የሚሸጠውን አንድ ሊትር ነዳጅ በ50 ብር ሂሳብ መግዛታቸውን አክለው አስረድተዋል። ምንም እንኳን በጥቁር ገበያ መገበያየት ህጋዊ ባይሆንም የማስተዳድረው ቤተሰብ አለኝ የግዴታ መስራት አለብኝ ይህንንም ለማድረግ በውድ ዋጋ ከጥቁር ገበያ ነዳጅ በውድ ገዝቻለሁ መንግስት ያለውን ገበያ ለማረጋጋት በህገ ወጥ መልኩ ነዳጅ ላይ የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት ብለዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ማለዳ የተወሰኑ የአማራ ክልል ቦታዎች ላይ በስልክ ለማጣራት እንደሞከረችው በጥቁር ገበያ ነዳጅ በውድ ሲሸጥ እንደነበር ፣ እንዲሁም በርካታ የቆሙ መኪናዎች እንዳሉ ለማወቅ ችላለች ይህንንም ተከትሎ ደብብ ወሎ ፣ ኮምቦልቻ ፣ ሀርቡ ፣ ገርባ እና ደጋን ጭምር ይህ ሁኔታ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

ማደያዎች ከቸርቻሪዎች ጋር እየተደራደሩ ያለችዋን ትንሽ ነዳጅ ይቀራመቷል ፤ የኹለት ብር ታሪፍ ያስከፍል የነበረው የባጃጅ መንገድ እስከ አምስት ብር ድረስ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ እንዳሉ እና አራት ብር የሚያስከፍለውን መንገድ ስምንት ብር እየተባሉ እንዳሉ ጨምረው ገልፀዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኮምቦልቻ ነዋሪ የሆኑ ቃልአብ ታዬ የተባሉ ግለሰብ እንደተናገሩት በክልሉ የማይታወቀው የታሪፍ ጭማሪ የሚጎዳው የማህበረሰብ ክፍሉን ነው፣ ታሪፍ በላይ እንድንከፍል እየተገደድን ነው አንከፍልም ካልናቸው አንሄድም ብለው ይቆማሉ ብለዋል።

እንደነዚህ አይነት ጭማሪዎች ማህበረሰብን ይጎዳል በተለይም የመንግስት ሰራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ አናሳ በመሆኑ ለኑሮ አዳጋች ይሁንበታል ብለዋል። መንግስት ህገ ወጦችን መቆጣጠር አለበት ዜጎች መበዝበዝ የለበንም ሲሉም ያላቸውን ሀሳብ ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በተመለከተ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የቢሮው ምክትል ሀላፊ ተዋቸው ወርቁን አነጋግራ ምላሽ ልታገኝ አልቻለችም እንዲሁም የሀዋሳ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ በስልክ ያለውን ሁኔታ ጠይቃ ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ካስያዙ በኋላ በተደጋጋሚ ስልክ ቢትደውልም ማግኘት አልቻለችም።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com