በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተያዙ ክፍት ቦታዎች በግል ባለሀብቶች እንዲለሙ ሊደረግ ነው

Views: 200

በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተያዙ ቦታዎች ውስጥ ያሉ ክፍት ቦታዎች ላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን ፍቃደኛ ለሆኑ እና የቢዝነስ ሀሳብ ካላቸው ሰዎች ጋር በጋራ ለማልማት ሃሳብ እንዳለው ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ ካለት 54 ሺሕ ካሬ የቆዳ ስፋት ውስጥ 5 ነጥብ 48 የሚሆነው በፌድራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተያዘ እንደሆነ የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን ገልጸዋል።
በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስር የሚገኙ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎች ከ85 በመቶ በላይ የልኬትና የይዞታ መረጃዎቻቸውን ማደራጄቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አሳውቀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ከ600 መቶ በላይ የሚሆኑ ተቋማትን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማሠራት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሆነ ተናረግዋል።
አክለውም “ለሸገር አዲስ ገጽታ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የተለያዩ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ይዞታዎችን ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ላይ የማዋል እንቅስቃሴ ለይዞታዎቹ አዲስ፣ ውብና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ለማቅረብ በፕሮጀክት መልክ ተቀርፆ ሁሉንም የኅብረተሰብን ክፍል የሚያቅፍ ውድድር እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።

ቁጥራቸው በርከት ያለ የመንግሥት ተቋማት ይገኙባቸዋል የተባሉ አምስት መዳረሻዎችን ማልማት ሚያስችል አዲስ፣ ውብና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ውድድር ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የተለያየ ሙያ ላላቸው ግለሰቦችም ሆነ ባለሀብቶች ክፍት እንደሚሆን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

የመጀመርያው መዳረሻ ቦሌ ሲቪል አቪዬሽንን መሥሪያ ቤትንእነደሚያካትት ተናግረዋል። ኹለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚገኝበት በተለምዶ ደምበል አካባቢን እንደሚይዝ ታውቋል።
ሦስተኛው እና በስፋቱ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለት የግዮን ሆቴል መዳረሻ ሲሆን፣ አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር በአራተኛ መዳረሻነት ሲያዝ፣ የመጨረሻውና አምስተኛው መዳረሻ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የፕላንና ልማት ኮሚሽንን እንደሚያካልል ተገልጿል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በተለይ ከቦሌ ጫፍ እስከ እንጦጦ እንዲሁም በለገኻር በኩል እስከ ማዘጋጃ ቤት ወይም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉት ሥፍራዎች በአብዛኛው በመንግሥት ተቋማት የተያዙ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ይኸንን ሥራ ለመሥራት መነሻ ምክንያት መንግሥት የምጣኔ ሀብት ልማትና ዕድገት ለማረጋጥ እየቀረፃቸው ያሉት የአገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርም፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ትኩረት ናቸው ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ከዕቅዶቹ ጋር ተጣጣሚ የሆኑ የልማት ዘርፎችን በመለየት በከተማው ውስጥ ያሉ የፌዴራል መንግሥት ይዞታዎችን በድጋሚ በማልማት ወይም አዲስ ገጽታ በመስጠት ሥራ ላይ የበለጠ ትኩረት የሚሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን መኖሪያ ቤቶችን ከግል ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መገንባት አንዱ ሲሆን ፤በአገልግሎቱ ዘርፍ የስብሰባ ማዕከልና ባለ ሰባት ኮከብ ሆቴል መገንባት እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል መገንባት እና የቴክኖሎጂና ትምህርት ማዕከላትንም ማቋቋም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሥራዎች እንደሆኑ አስታውቀዋል።

እዚህ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ለሚያሳዩ እና አብረው ለመሥራት ሀሳብ ላላቸው ዜጎች ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው ሁሉ በአካል በመቅረብ እንዲሁም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለተቋሙ ማሳወቅ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ለተከታታይ አራት ሳምንታት የፍላጎት መግለጫ ሰነዶችን ከመሬት ኮርፖሬሽን መሰብሰብ በመጀመር፣ በሀሳቡ ላይ የቀረቡ ሥራዎችን ለዕይታ በማቅረብና በባለሙያዎች በማስገምገም እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ አሸናፊው እንደሚገለጽ ከኮርፖሬሽኑ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com