በመተከል ዞን አሁንም ሰዎች እየተገደሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ

Views: 228

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በአንዳንድ ወረዳዎች አሁንም ድረስ ግድያዎች አንደቀጠሉ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ አረጋገጡ።
በዞኑ በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች በርካቶች ቢፈናቀሉም በአንዳንድ ከተሞች አቅራቢያ የሚገኙ ዜጎች ላይ ግድያዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻው ምንጮች ውስጥ በክልሉ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ያገለገሉ አሁን በዞኑ ለተፈናቀሉ ዜጎች የበጎ ፈቃድ ሥራ በማስተባበር ላይ የሚገኙ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ እንደሚሉት ከሆነ በመተከል የንጹሐን ዜጎች ሰቆቃ መፍትሔ አላገኘም ብለዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በየቦታው በየቀኑ ተገድለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ግድያ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች ውስጥ በቡለን እና ኤፓር ወረዳ መካከል ልዩ ቦታው በደሬ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ የታጠቁ ኃይሎች 11 ሰዎችን በአንድ ቦታ ገድለዋል ሲሉም ምንጫችን ከስፍራው ተናግረዋል። በቦታው ላይ የታጠቀው ኃይል በብዛት የሚገኝበት መሆኑንም ምንጮች ጠቁመዋል።

በዚህም ኤፓር ወረዳን ከቡለን ወረዳ የሚያገናኘው መስመር በታጠቁ ኃይሎች ከተዘጋ ስድስት ቀን አስቆጥሯል ተብሏል። በመሆኑም ቡለንን ከኤፓር የሚገናኘው መስመር በመዘጋቱ ለታጠቀው ኃይል ጥቃት አመች ሆኗል ነው የተባለው።
በዚሁ መስመር ላይ በአከባቢው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት በስምሪት ላይ እያለ የታጠቀው ኃይል ጥቃት አድርስተ የአንድ ወታደር ሕይት ሲጠፋ አንድ ወታደር ማቁሰሉ ተጠቁሟል። ይህን ተከትሎ በአከባቢው የተሰማራው የመከላከያ ኃይል ባሳለፍነው ማክሰኞ የካቲት 9/2013 በወሰደው እርምጃ የታጣቂ ኃይሉ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱ ታውቋል።

በዞኑ በየቦታው የዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር በደረሰባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ቤትና ንብረት በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቀው ኃይል እያወደመ ነው ተብሏል። በታጣቂ ኃይሉ እየወደሙ ነው ከተባሉ የተፈናቃይ ቤትና ንብረቶች መካከል በቡለን ወረዳ የሚገኙ ቀበሌዎች በከፍተኛ ደረጃ የወደሙ ናቸው ተብሏል። በቡለን ወረዳ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ቀበሌዎች በኩጅ፣ አዲስ ዓለም፣ ጭላንቆና ጎጃ ይገኙበታል። በሌሎች ወረዳዎችም የንብረት ማውደም ሥራውን ታጣቂው ቡድን እንደቀጠለ መኖኑን የአከባቢው ምንጮች ጠቁመዋል።

የታጠቀው የመተከል አጥቁ ኃይል በየወረዳው የሚገኝ የተፈናቃይ ቤትና ንብረት እያወደመ የሚገኘው ዞኑን የሚመራው ግብረ ኃይል ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ቅድመ ሥራዎችን እየሠራ በመሆኑ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል።
የዞኑ ግብረ ኃይል በዞኑ ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ አከባቢያቸውን የሚስከብሩ ሚኒሻዎችን እያሰለጠነ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ስልጠኛውን የሚሰጠው ከተፈናቀሉት የማኅበረሰብ ከፍሎች ውስጥ የተውጣጡ ሚኒሻዎችን ነው ተብሏል። የዞኑ ግብረ ኃይል ሚሊሻዎችን እያሰለጠነ የሚገኘው ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ሲመለሱ እራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ታስቦ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በመሆኑም መልካም አፈጻጸም ያላቸውን አመራሮች ወደ አመራርነት በማሰለፍ ችገሩን በውይይትና ማኅበረሰቡን በማግባባት የተሻ አማራጭ ለሆን አንደሚችል ነው ምንጮች የጠቆሙት። ይህ ካልሆነ ጥቁርና ቀይ የሚለው የልዩነት አጥር እየሰፋ ችግሩ የተራዘመ አንዳይሆን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአከባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከመተከል ዞን ግብረ ሀይል ምላሽ ለማግኘት ያደረችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። ይህም የሆነው የግብረ ኃይሉ አመራሮች እና ችግር ያለባቸው ወረዳ አመራሮች ስልክ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው። የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን በመተከል ዞን ጉዳይ ምላሽ አንደማይሰጥ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com