የፓርቲ አባላት ደኅንነት ይጠበቅ!

Views: 99

በኢትዮጵያ ተፈጠረ በተባው የለውጥ ሒደት ላይ አዳዲስ አካሔዶች እና ታይተው ማይታወቁ ይበል የሚያሰኙ ሁኔታዎች እና ክስተቶች መካሔዳቸው አይካድም። ጽንፍ እና ጽንፍ ቆመው የነበሩ አካላትን በተመለከተ ምን መደረግ ይኖርበታል በሚል ትክክለኛውን አካሔድ እንዲይዙ በማቀራረብ እና ወደ አገር ውስጥም በማስገባት በውስጥ ሆነው መታገል ወይም መቃወምም የሚችሉበት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተሰራውም መንገድ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ደግሞ የስድስተኛው አገራዊ ምርቻ መቅረቡን ተከትሎ እታዩ ያሉት ተግባራት ምህዳሩ በተወሰነ መንገድም መሻሻል ባሳየበት ልክ ጽንቶ እንዲቆይ የሚስመኝ እና መንግሥትም ይህን ከማስከበር እንዳይጎድል ማሳሰቢያ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ይህም ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ የቢሾፍቱ ከተማ አድአ ምርቻ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት ግርማሞገስ ለገሰ በየካቲት 7/2013 ምሽት ላይ መገደላቸው ይታወሳል። በወቅቱ የቢሾፍቱ ፖሊስ በግለሰቡ ግድያ ዙሪያ የግል ጸብ ጋር በማገናኘት ከተጎጂው የፖለቲካ አመለካከት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ግድያው ሁኔታ ፖሊስ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ሟች ከጊዜያት በፊት በግል ፌስ ቡክ ገጻቸው ማወከብ እንደሚደርስባቸውም ‹‹ደብረዘይት ላይ ያለው ኢዜማን እና ሕዝቡን ማዋከብ ቆሞ በሰለተነ መንገድ ሃሳባችን ቢሞገት ከተማዋ ከንቲባ ለኢዜማ ድምጽ እንደምትሰጥ ጥርጥር የለኝም›› የሚሉ ጽሑፍ በመለጠፍ የማዋከብ ስራ እንደሚሰራም ማመላከታቸው ይታወሳል። ይህን ጉዳይ ተመልክቶም ፓርቲው ኢዜማ በአባላቸው ግርማ ሞገስ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች አባላትን በማደራጀት እና መዋቅሮችን በመዘርጋት በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም የሀገር አንድነት እና ቀጣይነትን የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ አወንታዊ አስተዋፅዖ እያደረግን ከመቆየታችን በተጨማሪ አጠቃላይ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ባህል ለመቀየር የበኩላችንን ጥረት ስናደርግ የቆየን መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመወያየት፣ አባላትን ለመመልመል እና ለማደራጀት በምናደርገው ሙከራ ውስጥ ሥራችንን ለማደናቀፍ እና ተስፋ ለማስቆረጥ የመንግሥትን መዋቅር ጨምሮ የተለያዩ ኢ-መደበኛ አካላት ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ረጅም ጊዜ እና ትልቅ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ በማመን ችግሮቹን ከማጉላት ይልቅ ችግሩን እና ፈተናውን ተቋቁመን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።

የሚደርሱብንን ጫናዎች በመቋቋም የዘረጋነውን ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የተጠራቀሙ ችግሮችን የሚፈቱ በባለሙያዎች የተዘጋጁ ፖሊሲዎች ይዘን የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ዝግጅታችንን ባጠናቀቅንበት የመጨረሻ ሰዓት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሾፍቱ ከተማ አድአ ምርጫ ወረዳ 1 የኢዜማ መዋቅር ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ ሞገስ ለገሰ እሁድ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በጥይት ተመተው ሕይወታቸው አልፏል።

ከዚህ በፊት በቢሾፍቱ ከተማ የምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙን እና አባላቶቻችን ላይ ማዋከብ ሲያጋጥመን ነው የቆየው። በከተማው ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ፈልገን በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ በከተማው አስተዳደር እምቢተኝነት ምክንያት መሳካት አልቻለም። የምርጫ ወረዳ መዋቅራችን የሚጠቀምበት ጽሕፈት ቤትም ለመክፈት ብዙ ውጣውረድ ብናልፍም ከከተማው አስተዳደር በሚደረግ ጫና መሳካት አልቻለም። በከተማው ኢዜማ ከነዋሪዎች ጋር ሊያደርግ የነበረውን ስብሰባም ሆነ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ለማስተባበር ሲሠሩ የነበሩት አቶ ግርማ ነበሩ። ከዚህም የጎላ እንቅስቃሴያቸው ጋር በተያያዘ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር።

በቢሾፍቱ የሚገኘው የኢዜማ መዋቅር በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በዋናው ጽሕፈት ቤት እገዛ እንዲስተካከል አቤቱታቸውን ቀደም ብለው አስገብተው ነበር። ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከከተማው እና ከክልሉ ኃላፊዎች እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ሙከራ አድርገን ነበር። ሙከራችን የነበረውን ችግር ማቃለል አልቻለም። እንደውም ችግሩ ተባብሶ የሁለት ልጆች አባት እና የቤተሰብ ኃላፊ እና የኢዜማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ በጥይት ተመተው መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን አጥተዋል።›› እያለም ይቀጥላል።

በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የመልካም ጅማሮ ወደ ኋላ ለማድረግ እና ከተነሳንበትም ወደ ታች ለመውሰድ የሚደረግ ክፉ አካሔድ ነው እና ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት እና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሻቸው ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ማካሄድ ሕገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸው ሁሉ መንግሥትም ተፎካካሪ ፓርቲዎችንም ሆነ የገዢውን ፓርቲ ዕጩዎች በሔዱበት ሁሉ ደኅንነታቸውን ማስተብቅ ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ይህ በሚሆንበት ሁኔታ የታሰበው እና ያለመውን የዲሞክራሲ ግንባታ ዕውን ለማድረግ ሚደረገውን ግስጋሴ እንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚገፋ ይሆናል። ከዚህ ቀደም እንደተባለውም በተደጋጋሚም በጠቅላይ ሚንስትሩ ሲገለጽ እንደሚሰማው ፍትሀዊ ሆነን ምርጫ በማካሔድ ተሸናፊው ሽነፈቱን አምኖ ሚቀበልበት አሸናፊውም በፍትሐዊነት ስልጣን የሚያገኝበትን አካሔድ በዚህ አይነት ሁኔታ መፍጠር እንደማይቻል ግን አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች። በመሆኑም የዜጎችን ብቻም ሳይሆን ምርጫ እደረሰ ሲመጣ ደግሞ ከሚፈጠሩ ችግሮች ውስጥ ይህን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ድኀንነታቸው ተጠብቆ የሚንቀሳቀሱበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። አሁንም ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ ምርጫን ማካሔድ ወደ ነበርንበት አዙሪት ከመክተት ባለፈ ምንም አይነት አዲስ ነገር በተለይም ደግሞ ለአገር ጠቀሜታ እንደሌለው ከወዲሁ መንግስት ሊገነዘብ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ አገር እና አገረ መንግስት ሚገነባው በዚህ በሴራ እና በጥፋት ሳይሆን አገርን እና መንግሥትን በሚያስመሰግን መንገድ የዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል። አንዱ ቀዳሚውን እየጠላ ለማጥፋት ሚሮጥባት ኢትዮጵያን በዚህ ትውልድ ላይ ሰብሮ ለተተኪው ትውልድ አዲስ አገር እና በረታን ሕዝብ ማቀበል የሚቻለው በትክክል ቆም ብሎ በማሰብ እና ቀድሞ በሕዝብ ዘንድ የተጠላውን ነቅሶ በማውጣት ሊሆን ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ደኅንነትን ማስተበቅ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ማስጠበቅ በራሱ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን እና ጠንካራ መንግስትን ከመገንባት አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለውም ይታወቃል። በመሆኑንም ገና ምርጫ ቅስቀሳው በለጋ ዕድሜ ላይ ባለበት ሁኔታ ይህን አይነት ጥፋት መከሰቱ የሚያሳፍር ቢሆንም በቀጣይ ግን አሁንም መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አባላትን ደኅንነት እያስጠበቀ የምርጫ ሒደቱን ማሳለጥ ይኖርበታል ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com