በምሥራቅ ወለጋ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አርሶ አደሮችን ትጥቅ እያስፈታ መሆኑ ተገለጸ

Views: 366

በአሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦሮሚያ ልዩ ኀይል የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና አርሶ አደሮችን ትጥቅ እያስፈታ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የክልሉ ልዩ ኀይል ማኅበረሰቡን ትጥቅ ማስፈታት የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙ ሲሆን፣ ልዩ ሀይሉ ማኅበረሰቡ እራሱን ከኦነግ ሸኔ ጥቃት የሚጠብቅበትን መሳሪያ በግድ እያስፈታ በማለት ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በዚህም ማኅበረሰቡ እና የክልሉ ልዩ ኀይል ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ግጭቱ የተፈጠረው የክልሉ ልዩ ሀይል ማኅበረሰቡን ትጥቅ ፍቱ ማለቱን ተከትሎ፣ ከኦነግ ሸኔ የሚጠብቀን ዋስትና ሳይኖረን እራሳችንን የምንከላከልበትን መሳሪያ አናስረክብም በማለታቸው መሆኑ ታውቋል።

ልዩ ሀይሉ ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቆ በገባበት ሁኔታ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሰባት አርሶ አደሮች በልዩ ሀይሉ በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸውን እንዳጡ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል።
የችግሩን ዳራ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ማኅበረሰቡ እራሱን በአከባቢው ከተሰማራው ኦነግ ሽኔ ታጣቂ ቡድን የሚከላከልበት መሳሪያ በመሆኑ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከኗሪዎቹ አንደበት እንደሰማችው ከሆነ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይል ትጥቅ ለማስፈታት ባደረገው ሙከራ እና ማኅበረሰቡ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር መከላከያ መሀል ገብቶ እንዳረጋጋው ተመላክቷል።
በልዩ ሀይሉ በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸውን አጥተዋል ከተባሉት ውስጥ በምስራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን መንደር 10 የሚኖር ዋሲሁን በላይ የተባለ ወጣት ይገኝበታል። ወጣቱ የካቲት 9/2013 አንደተገደለም ተመላክቷል።
ከሳምንት በፊት በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ጀምረው የነበረ ሲሆን፣ ጥቃቱን አስመልክቶ የአከባቢው ነዋሪዎች በወሰዱት የመከላከል እርምጃ ከኦነግ ሽኔም እራሱን ለመከላከል ከወጣው ማኅበረሰንም ሕይወት ማለፉ ተዘግቦ ነበር ።በዚህም ከኹለት ሳምንት በፊት

የአካበቢው ማኅበረሰብ እራሱን ለመጠበቅ ባደረገው ፍልሚያ ከስምንት ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን በፍልሚያው ላይ የነበሩ የአይን እማኞች መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ ባለፈው እትሟ ዘግባለች።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ኦነግ ሽኔ ከዚህ በፊት ሲደርስ ከነበረው ጥቃት በላቀ ሀይል ጥቃት ለማድረስ መሞከሩን ተከትሎ ካሳለፍነው የካቲት 1/2013 እስከ የካቲት 4/2012 ባሉት አራት ቀናት የአካባቢው ማኅበረሰብ እራሱን በማደራጀት ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሀይል ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲደርግ አንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ይህን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይል የአከባቢውን ማኅበረሰብ ትጥቅ ለማስፈታት መሞከሩን እና የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ኗሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የአከባቢው አመራሮች ጥቃት የሚደርስበት የማኅበረሰብ ክፍል እራሱን ከጥቃት እንዳይጠብቅ እገዛ እያደረጉ ነው በማለት ወቅሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ በአካባቢው ግጭቶች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ አረጋግጠዋል። በዚህም የሰው ሕይወት እንደጠፋ ኃላፊው አምነዋል።
ይሁን አንጅ የክልሉ ልዩ ሀይል ከማኅበረሰቡ ጋር መጋጨቱን መረጃ አልደረሰኝም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የትጥቅ ማስፈታት ተግባሩን በተመለከተም ሕጋዊ ያለሆነ ትጥቅ ካለ ሕግ የማስከበር ሥራ በልዩ ሀይሉ ሊሰራ ይችላል ብለዋል።
ጌታቸው አክለውም የአከባቢውን ችገር ለመፍታት በየጊዜው የተሰሩ ሥራዎች እየተገመገሙና የአመራር ለውጥም እየተደረገ ነው ብለዋል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪም በቅርቡ በአዲስ ተተክቷል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከዞኑ መረጃ ኃላፊ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ሊሳካ አልቻለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com