ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ በሦስተኛ አማራጭ ቤቶችን ሊገነባ ነው

Views: 245

ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ የተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የንግድ ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት የቤት መሥሪያ ቦታ እና የገንዘብ አቅም ያላቸውን ሰዎች በማገኛኘት ከሪል እስቴት ገንቢዎች እና የመንግሥት ኮንዶሚኒየም ግንባታ በተለየ አሰራር ለቤት ፈላጊዎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ጥናት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የመሬት ባለይዞታዎችን፣ ቤት ፈላጊዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማገኛኘት ለአዲስ አበባ አዲስ አሠራር ይዤ መጥቻለሁ ያለው ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ የመጀመሪያ ዙር አንድ ሺሕ ቤቶችን በአዲስ አበባ ሊገነባ እንደሆነ ተነግሯል።
ድርጅቱ ያቀረበው አገልግሎት ለአዲስ አበባ ሦስተኛ አማራጭ አንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ይህም በግለሰቦች ይዞታ ላይ በአነስተኛ ዋጋ የሚገነባ ነው ተብሏል።

ሦስተኛ አማራጭ ሲባል ነዋሪው በዋነኛነት ቤት እያገኘ ያለው በኮንዶሚኒየም ግንባታ እና በሪል እስቴቶች አማካኝነት ነው። የኮንሚኒየም ቤት ለማግኘት በእጣ በመሆኑ መቼ ለማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ አይቻልም ፣በሪል እስቴት በኩል ደግሞ የቤት ባለቤት ለመሆን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመጠየቁ ጎጆ ያቀረበው ሦስተኛ አማራጭ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ ቦታ ላይ በአነስተኛ ዋጋ ለመገንባት የሚያሥችል አማራጭ ነው ተብሏል።
በማኅበር ተደራጅተው ቤት ለመሥራት ለሚፈልጉም የተዘጋጀ ቦታ እንዳለ እና በማንኛውም ሰዓት ወደ ግንባታ ለመግባት እንደሚቻል ተገልጿል።

በመጀመሪያው ዙር የቤቶች ግንባታ አራት ሳይቶችን ለመገንባት ባለይዞታዎችንና ቤት ፈላጊዎችን በማገኛኘት ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ተቋሙ የካቲት 11/2013 በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በነበረው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ሥርዓት ላይ ገልጿል።
ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ኹለት ሺሕ 800 ቦታቸውን ማጋራት የሚፈልጉ ባለ ይዞታዎች መመዝገቡን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት መርሀ ግብሩን ለማስጀመር በአራት ሳይቶች ላይ የግንባታ ዲዛይን ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በእነዚህ አራት ሳይቶች 1 ሺሕ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል። በጠቃላይ በያዝነው 2013 ፤10 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል እቅድ እንደተያዘ እና በርካታ ባለይዞታዎችም የሥራውን መጀመር እየተጠባቁ እንደሆነ ተገልጿል።

የድርጅቱ የመካከለኛ ጊዜ እቅድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 100 ሺሕ ቤቶችን መገንባት መሆኑን እና ባለይዞታዎችም የእቅዱን መሳካት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
በመጀመሪያው ዙር የሚገነቡ ቤቶች በጎሮ 760 አፓርትመንቶች ያሉት ባለ 12 ወለል ህንፃ፣ በቡልጋሪያ 110 አፓርትመንቶች ያሉት ባለ 22 ወለል፣ ጣሊያን ኢንባሲ 96 አፓርትመንቶች ያሉት ባለ 12 ወለልና በላንቻ 84 አፓርትመንት ያሉት ባለ 21 ወለል መኖሪያ ቤት መሆኑ ተገልጿል።

ለቅድመ ምዝገባ ማመልከቻ ቅድሚያ ክፍያ 350 ሺሕ ብር በዝግ አካውንት ገቢ በማድረግ ተመዝጋቢው ከድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በሚሰጠው የቀጠሮ ቀን የከፈለበትን የባንክ ደረሰኝ በመያዝ ውል እንደሚፈጽም እንዲሁም ለጋራ ልማት የተመዘገቡት የግል ይዞታዎች እንደየ ምዝገባ ቅደም ተከተላቸው እንደሚመደቡ ታውቋል።

በአጠቃላይ ይህ የቤቶች ግንባታ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሥራ ፈላጊዎችን የሕንጻ ግንባታ ተቋራጮችን እንዲሁም የገንዘብ ተቋማትን እና መንግሥትን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
የመሬት ባለይዞዎች ከ 500 ካሬ ሜትር ጀምሮ የመሬት ይዞታ ያላቸው ባለይዞታዎች ይዞታቸውን ለማልማት በአቅም ምክንያት ካልቻሉ ይዞታቸውን እንዳይለቁ ከቤት ፈላጊዎች ጋር በማገናኘት በጋራ የመኖሪያ ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችል አሠራር ውስጥ ይካተታሉ።
ቤት ፈላጊዎች ወይንም ገንቢዎች ደግሞ ዝቅተኛ ወይንም መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ሲሆኑ በጎጆ ብሪጅ አሠራር እነዚህን ኹለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ማኅበር እንዲመሰርቱ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com