የፕራይቬታይዜሽን ገቢ የልማት ድርጅቶችን እዳ ለመክፈል ይውላል

Views: 22

ከፕራይቬታይዜሽን ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን እዳ መክፈያ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴሩ አህመድ ሺዴ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ፖሊሲ ማተርስ ላይ ባደረጉት ውይይት አስታውቀዋል።
በዚህም ከ21 ትልልቅ የመንግስት ልማት ድርጅቶች መካከል ሰባት የሚሆኑት 780 ቢሊየን ብር እዳ ያለባቸው ሲሆን ይህንን እዳ ድርጅቶቹ በራሳቸው መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ስለደረሱ 570 ቢሊየን ብሩ በእዳ ሽግሽግ መልክ እንዲነሳላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ታህሳስ ወር ላይ ውሳኔ አስተላልፈው እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የእዳ እና ሀብት አስተዳዳሪ ድርጅት ተቋቁሞ የመንግስት ልማት ድርጅቶች መክፈል የማይችሉት እዳ ወደ እራሱ አዘዋውሮ እዳውን እንዲከፍል ተወስኗል፤አዲስ የሚቋቋመው ድርጅት በወራት ጊዜ ይቋቋማል ተብሎ ይገመታል።
አዲሱ የሚቋቋመው ድርጅት እዳውን እንዴት እንደሚከፍለው ኹለት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው ወደ ግል ከሚዞሩት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚገኘው ገቢ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ተናግረዋል። ኹለተኛው ደግሞ አትራፊ ከሆኑት የመንግስት ልማት ድርጅቶች መንግስት የሚያገኘው የትርፍ ገቢ (ዲቪደንድ) ናቸው። በተለይም ይህንን እዳ ለመሸፈን በከፊል እየተሸጠ ካለው ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚገኝ ይገመታል።

ይሁን እንጂ የሰባቱም እዳ ሙሉ በሙሉ እንደማይዘዋወር እና መክፈል የሚችሉት ተለይተው እንደየ አቅማቸው በከፊል ብቻ እንዲነሳላቸው መደረጉን አክለው ተናግረዋል።
በዚህም መክፈል በሚችሉበት አቅም እንደየ አቅማቸው የተከፋፈለ ሲሆን እዳው ከተነሳላቸው የመንግስት ልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ሀይል 50 በመቶ ፣ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ 76 በመቶ ፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሀይል አቅርቦት 21 በመቶ ፣ የኢትዮጵያ ባብር ትራንስፖርት 100 በመቶ እንዲሁም የኬሚካል ኮርፖሬሽን 94 በመቶ እዳው እንደተነሳለቸው ሚኒስቴሩ ጠቁመዋል።

ይህን ብድር የሚተላለፍበት ብዙ የተለያየ መንገዶች ታስበው እንደነበር ለአብነትም ባንክ ለማቋቋም ታስቦ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስቴሩ ነገር ግን አዋጪ ሆኖ የተገኘው ይህ ሊያብሊቲ ኤንድ አሴት ማነጅመንት የተባለ ካምፓኒ ማቋቋም እንደሆነ ስለታመነበት እንደሆነም አስረድተዋል።ይህ የሚቋቋመው የእዳ እና ሀብት አስተዳዳሪ ድርጅት በንግዱ ላይ የሚሰማራ እና ሌሎች ትርፍ ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎች ላይ የሚሳተፍ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ቀጥተኛው የሆነው እዳውን የማንሳት መንገድ እዳውን በጠቅላላ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ማዞር ነበር ነገር ግን እዳው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ቢዞርና ገንዘብ ሚኒስቴር እዳውን ተረክቦ ከበጀት ላይ ነው የሚከፍለው ይህ ደግሞ የረጅም አመት የበጀት መቃወስ ያስከትላል ብለዋል።
የልማት ድርጅቶቹ ባለባቻው የእዳ ጫና ምክንያት መስራት ያለባቸውን ያህል እየሰሩ አይደለም፤ የእዳ ሽግሽጉ አላማ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የእዳ ጫና ነፃ በማድረግ አዋጭነታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

ላለፉት አስር አመታት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከግሉ ዘርፍ የብድር አቅርቦትን ሲሻሙ የነበረ ቢሆንም ጠቅላላ የአገራዊ ምርት ያላቸው ድርሻ 10 በመቶ ብቻ መሆኑን አዲስ ማለዳ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በ2012 ዓመት ባወጣው ሪፖርት ላይ አመላክቷል።

የልማት ድርጅቶቹ እዳ ሊከማች የቻለው መንግስት በተከተለው ዘላቂነት የሌለው የገንዘብ ፍሰት ፣ አዋጭነታቸው በጥናት ያልተረጋገጠ ፕሮጀክቶችን መጀመር እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶት አለመጠናቅ የቁጥጥር አለመሮር እና ሙስና ተጠቃሾች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የልማት ድርጅቶቹ የያዝዋቸው ፕሮጀክቶች ወደምርት ገብተው ውጤታማ ባለመሆናቸው ምክንያት ብድሩን ሲያቀርብ በነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይም ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር እንደነበር ተጠቅሷል ይህም ጫና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም እንደሚጎዳው ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com