በአዲስ አበባ ዘመናዊ የአየር ጥራት መለኪያ መሳሪያ ሊተከል ነው

Views: 106

የአዲስ አበባ ከተማ አካበቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን አማካሪ የሆኑት አቶ ጥበቡ አሰፋ እንደገለፁት፣ ኮሚሽኑ ከC40s የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተቋቋሙ ትልልቅ የአለም ከተማዎች ህብረት ጋር በመተባበር የአየር ጥራት መለኪያ መሳሪያ ሊተከል ነው ብለዋል።
በከተማዋ ከ8 በላይ የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በስራ ላይ ሲሆኑ አሁን ደግሞ አንድ ተጨማሪ የአየር ጥራት መለኪያ መሳሪያ እንደሚተከል ተገልጿል። መሳሪያው የአየር ጥራትን ከመለካት በተጨማሪ ሌሎች የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ስራቸውን ለመከታተል የሚያስችል ነው ብለዋል።
እንዲሁም በከተማዋ በየቀኑ ያለውን የአየር ፀባይ ቀድሞ በመተንበይ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለመውሰድ ይረዳል ብለዋል። በዋናነት ግን በከተማዋ ያለው አየር ፀባይ መበከሉንና አለበከሉን በማመላከት ለከተማዋ ማህበረሰብ ለጤና ተስማሚ የሆነውን የአየር ፀባይ ለመለየት ያገለግላል ሲሉም ገልፀውልናል።
የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኒካል ፕሮጀክት በአዲስ አበባ በከተማ ደረጃ የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በመግዛት እና በማቅረብ እንዲሁም ለከተማዋ የአየር ጥራት ክትትል ማድረጊያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከአባል ሃገራቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ ገብተዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከብሄራዊ ሜቲዮሮሎጅ ኤጀንሲ፣ ከፌደራል ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራንስፖርት ባለስልጣን፣ ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድ ቁጥጥር እና ማረጋገጫ ባለስልጣን፣ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ከአባል ሃገራቱ የተውጣጡ ከኬንያ፣ ጋና እና አሜሪካ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአየር ጥራት መቆጣጠርና የአየር ጥራት መረጃ አያያዝ ዙሪያ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
የሲ40 ከተሞች የአየር ንብረት አስተዳደር ቡድን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቁርጠኛ የሆኑ የዓለም ትልልቅ ከተሞችን በብቃት ለመተባበር፣ ዕውቀትን የማጋራት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትርጉም ያለው፣ ሊለካ የሚችል እና ዘላቂ እርምጃዎችን እንዲነድፉ የሚደግፍ ተቋም ነው።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com