የእለት ዜና

‹አደይ› እና የስጦታ ዕቃዎቹ

ብዙ ሰዎች ስጦታ ለመስጠት በጣም ሲጨነቁ ይስተዋላል። እንደ ሠርግ፣ ምርቃት እና የልደት ዝግጅቶች በሚኖሩበት ሰዓትም ምን ልስጥ በማለት ብዙ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ ይህንን የተመለከቱት የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች  ይህን ክፍተት ለመሙላት እየተፍጨረጨሩ ነው – አማኑኤል ከበደ እና  ዮሃንስ መኮንን።

ሥራውን ከጀመሩ አንድ ዓመት አልፏቸዋል ። የሚሰሩትም ኖት ቡክን (ማስታወሻ ደብተር)፣ ፎቶ በቆዳ ላይ   እየሰሩ መሸጥ ጀመሩ የሚሰሩትን ማስታወሻ ደብተርም ወደ ክፍለ አገር ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጣውላ፣ማይካ እና ቆዳዎች ለስጦታ እንዲመች አድረገው አበጃጁ።

አማኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮንስትራክሽን ማኔጅመነት ነው ያጠናው። ዮሃንስ መኮንን ደግሞ አርክቴክት ነው ያጠናው። ተስፋሁን ስፌት የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ሲኖሩ እና  ዋሌቶችን በመስፋት አብሯቸው ይሰራል።

አማኤል የመጀመሪያ ድግሪውን ያገኘ ሲሆን በአሁን ወቅት ደግሞ ኹለተኛ ድግሪውንም እየሰራ ነው። አማኑኤል እና ዮሃንስ በአሁን ወቅት ሥራ የመፈለጉ ነገር እምብዛም አያሳስባቸውም። ምክንያቱም እንደቀልድ የጀመሩት ሥራ ውጤታማ ሊያደርጋቸው  ወይም ተስፋን እንዲሰንቁ ስላደረጋቸው ነው።

መነሻ ሃሳብ

በዩኒቨርስተው ውስጥ ሆነው ኖት ቡክ (ማስታወሻ ደብተር) የሚሰሩት አማኑኤል እና ጓደኞቹ ‹‹ብዙ ሰዎች ሲወዱት እና ሲቀባሉት አየን ይህን ጊዜም ለምን ወደ ቢዝነስ (ገንዘብ) አንቀይራቸውም? የሚል ሃሳብ መጣልን። ደብተሮችን ብቻ መስራት ጀምርን›› ይላል።‹‹ከዛ በኋለ ግን ሌሎች ነገሮችን መጨማመር ጀመርን።እኛ የተለያዩ ሶፍትዎሮችን ስለምናውቅ እና ዲዛይንም ማድረግ  ስለምንችልም ሥራውን ጀመርነው። አስፈላጊ በሆነ ሰዓትም ሌሎች ማሽን ያላቸው ሰዎች ጋር በመሄድ እናስቆርጣለን›› በማለት ነው ወደ ሥራው እንዴት እንደገቡ የሚናገረው።

ገንዘብ ማግኘት ሲጀምሩ፤ የሥራ ውጤቶቻቸውን የወደዱት ሰዎችም ምላሻቸው ጥሩ እንደሆነ እና ስጦታ ለመስጠት ቸግሯቸው እንደነበርም ያነሳል።

ሥራዬ ብለው ያልጀመሩት እና አልፎ አልፎ እንዶሁም  በሠው በሠው ትውውቅ ሥራቸው ሲለመድ ከደብትር ውጭ የሰዎችን ፎቶ በቆዳ ላይ በማስቀረጽ ሥራውን ጀመሩ ።በቀጠል ደግሞ በቆዳ ላይ የሚወጠሩ ፍሬሞችን መስራትም ቀጠሉበት። አሁን ላይ ደግሞ ሥራቸው ተወዳጅነትን እና ተቀባይነትን እያገኘ በመምጣቱ ብዙዎች ትዕዛዝ እየሰጧቸውም ይገኛሉ።

ትምህርት እና ሥራ?

የሙሉ ሰዓት ተማሪዎች የነበሩት እነ አማኤል ከትምህርት ጋር እንዴት እያስተሳሰሩ ሥራውን  ይሰሩት እንደነበር ሲናገርም ‹‹በተለይም የፈተና ወቅት ላይ ስራውን ዞር ብለን አናየውም ማለት ይቻለል። በፈተና ወቅት አስገዳች እና አስቸኳይ ነገር ካልገጠመን በቀር ትዕዛዞችንም አንቀበልም ነበር። ይህም ፈተናው አንድ ሳምንት ቀረው ሲባል እንኳን አንሠራም። እኛ ሥራውን እንደ መዋያ ነበር የምናየው። ከተመረቅን በኋላ ነው ጠልቀን የገባንበት።›› ሲልም ያስረዳል።

ትምህርቱ እና የስጦታ ዕቃዎችን ማዘጋጀት ከተማሩት ትምህርት ጋር ይገናኝ ይሆን በማለት ከአዲስ ማላዳ ለአማኑኤል ጥያቄ ቀረበ እርሱም ሲመልስ ‹‹በግቢ ውስጥ ነጻ ኢንተርኔት በመኖሩ ሥራዎችን ኤዲት ለማድረግ፣ሥራ ቦታ ላይ ለሚሰሩ ሰዎች ፋይል ለመላክ ጠቅሞናል።›› ከዛ በተጨማሪ ግን ሥራው እና የተማሩት ትምህርት ግንኙነት የላቸውም።

ከምርቃት በኋላስ?

እነ አማኤል ከምርቃት በኋላ ራሳቸውን በገንዘብ አጠናክረው ሱቅ ለመከፈት እያሰቡ ነው ።እስካሁን ሰዎች የሚገዙን በኦንላይን ብቻ ስለነበር አሁን ግን የግድ ሱቅ ከፍተን መሥራት እንዳልን በማመናችን እየሞከርን እንገኛለን ይላይ – አማኑኤል። ሰዎች ሥጦታ ለመሥጠት ሲቸገሩ ተመለክተናል። በተለይም ከስተም ሜድ ላይ መስራቱ ጥሩ እንደሆነ መረዳታቸውንም ሥራውን እንድንገፋበት አድርጎናል ሲልም ይደመጣል። ከስተም ሜድ ሲባል የሚሠራው ደንበኛው በፈለገው እና ባዘዘው መንገድም ሲሰራ ማለት ነው።

በቀጣይ ያቀዱት እና በዚህ ዓመት ለመክፈት የወጠኙት ሃሳብ ዋናው ዓላማ ደንበኞቻው  መጥተው የተሰራውን እንዲያዩ፣እነሱም(አማኤል እና ጓደኛው) በአንድ ቦታ ላይ ተገኝተው ቀጣይነት ያለውን ሥራ ለመስራት ነው።

የ‹አደይ› ስያሜ?

የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያለ የማይጨንቀው ተማሪ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም። ‹‹ከዚህ በፊት ቀድመው የተመረቁ ተማሪዎች ሥራ አላገኘንም ሲሉ የሚሰማ ስሜት አለ። ይህንን ምክንያት በማድረግ ተስፋ እንዳለ ለማሳየት ‹አደይ›(ላልቶ ሲነበብ) የሚለውን ስያሜ የተሰጠው ሲሆን እንዲሁም ‹አደይ› (ጠብቆ ሲነበብ) በትግርኛ  እናት ማለት ነው። በመሆኑም ይህንን ስያሜው መስጠት ያስፈለገበት ምክንያትም ‹ተስፋ እና እናት› አንድ ላይ ስለያዘልን ይህንን ስያሜ ሰጥነዋል ይላል። በይበልጥም ከተስፋ ጋር አያይዘውታል።

ኦንላይን ገበያ

እነ አማኑኤል ‹አደይ ጊፍትስ› ብለው በሰጡት ስያሜ፤  ስራዎቻውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እያተዋወቁት እና ትዕዛዝ እየተቀበሉበት ይገኛል። የሚጠቀሙት ማህበራዊ ሚዲያም ቴሌግራም፣ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ይጠቀሳሉ።

ምንም እንኳን ሥራው ወቅት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም  በተለይም በምርቃት ወቅት ፣በሠርግ እና በሌሎች ወቅት የተለያዩ ስራዎችን እንድንሰራላቸው ትዕዛዝ ይሰጡናል ሲልም አማኤል ለአዲስ ማለዳ ይገልጻል።

መልካም ነገር

ይህን ሥራ እንደ ሥራ ቆጥረው አልነበርም ሲሰሩ የነበረው። ይህም የበለጠ የሥራ ፈጣሪ ( ክሬቲቭ) እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ‹‹እኛ ውጭ አገር የሚሠሩትን ወደ እኛ አገር  በማውጣት ከቆዳ እና ከማይካ ውጪም የተለያዩ መብራቶችንም በመጠቀም አቅማችንን እያሰደግን  መጥተናል የሚለው አማኤል ፤ አዲስ ነገር እንድፈጥርም አበረታቶናል። ደንበኞቻችንም ይሁኑ ስለ እና የሰሙ ሰዎች  ምን አዲስ ነገር አለ? ብለው በመጠየቃቸው ሌላ ያልተሰራ  አዲስ ነገር ለመስራት ጥረት እንድናደርግ እረድቶናልም ይላል። ‹‹እዚህ ሥራ ላይ በየጊዜው አዲስ ነገር መፍጠር  ግዴታሽነው ።ይህም የሥራው መልካም ነገር ነው።››

ፈታኙ ነገርስ?

‹‹ሥራው ሲሰራ በጣም ጊዜ ይወስዳል። በተለይም የቆዳ ሥራው ብዙ ሰዓታትን ይፈጃል። ከዲዛይን በኋላ ወደ ማሽን ቤት ይላካል። ከጊዜ መውዱ ግን የሚያስቸግረን በየእለቱ የሚደረገው ዋጋ ጭማሪ ነው።ይበልጥም ችግሩ የሚታየው ማሽን ባላቸው ሰዎች ላይ ነው›› የሚለው አማኤል፤  ለምሳሌ ባለፈው ክረምት ወር  ሰዎች ቤታቸው ውሰጥ እያሰለፉ በመሆናቸው፣ የማሰብ አቅማቸውን እንዲጨምሩ ለማድረገም ፐዝል እንሰራ ነበር። ይህን ሥራም  ክረምት ላይ በደንብ ሰርተናል።ታዲያ በዚህ ጊዜ ከአራት ጊዜ በላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎብናል ይህም ቀላል የሚባል ፈተና አይደለም። የዋጋ ጭማሪውም በኹለት ወር ውስጥ ከ200 ብር እስከ አንድ ሺህ ብር ደርሶ እንደነበር አስታውሷል።

ምንም እንኳን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ  ያላጠቃው የሥራ መስክ የለም ይባል እንጂ፤ ለእነ አማኑኤል ግን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ይህም አብዛኛወ ሰው እቤቱ ስለነበር ፐዝል በጣም እንሰራ ነበር። እንደውም በዛ ጊዜ ሠው ቀጥረን እንሰራለን ፐዝሉም በፎቶ የሚሰራ ነው። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የናፈቋቸውን እና በሚወዷቸውን ሰዎች ፎቶ አሰርተውን ሄደን እድንሰጣቸው አድርጓልም በማለት ያነሳል። ከዚህ በተጨማሪም ማሽን ቤቶች ሥራ የተቀዛቀዘባቸው ወቅት ቢሆንም ‹‹እኛ ግን ብዙ ሥራዎችን በማሰራት እነሱን  ማንቀሳቀስ ችለናል። እነዚህ ተቋት ሥራቸው ጨረታ ላይ  የተመሰረተ ሲሆን አብዛኛው እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙም ሥራቸው ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም ከእኛ ጋር ግን ጥሩ ሥራዎችን መስራት ችለናል›› ይላል አማኑኤል ።

መልዕክት

‹‹ማንኛው ሰው በተመረቀበት የሥራ ዘርፍ ሥራ አገኛለሁ ማለት የለበትም። አብዛኛው ተማሪ ከትምህርቱ ጎን ለጎንም ሲጨነቅ የሚታየው ተመርቄ ሥራ አገኛለሁ ወይ? የሚለው በመሆኑ በተቻለ መጠን ጎን ለጎን ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮችን ማሰብ ፣መሞከር እንዲሁም ያላቸውን ተሰጥኦ ማሳደግ ጥሩ ነው።›› በማለት አማኑኤል ሄደበትን መንገድ ምሳሌ በማድረግ ያሳስባል። እንደ ቀልድ የተጀመረው ሥራም ለዚህ ጅምር አብቅቶናል ሲል የሚደመጠው ወጣቱ አማኑኡል፤ ‹‹እንደውም አንዳንድ የግቢ ተማሪዎች ለጎን የተለያዩ ሥራዎችን በመስራ ራሳቸውንም እያስተዳደሩ ይገኛሉ እና ሌሌችም ቢሆኑ ትምህርታቸው በማያስተጓጉል መልኩ  ጎን ለጎን ማስኬድ ይኖርባዋል›› ሲል አማኑኤል ተሞክሮውን አጋርቷል።

ዛሬ ላይ በቅጥረኝነት ሕይወት ውስጥ ብዙ የመቆየት ፍላጎት የሌላቸው የ‹አደይ ጊፍትስ› መስራቾች የግድ በተማርንበት እንስራ ብለው ሙጥኝ ሳይሉ ራሳቸውን እያስተማሩ እና የሥራ ባለቤትም ማድረግ ችለዋል።

 

 


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com