የማንነት አሻራ

Views: 112

ወሰኔ ኃይሌ በኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉ፣ በቻሉት ሙያ ያገለገሉ፣ ትልቅ ቤተሰብ የመሠረቱና በሕይወት አጋጣሚ ከአገራቸው ርቀው የሚኖሩ ሴት ናቸው። ‹ማን ናቸው?› የሚል አይጠፋም። በየሕይወት ሩጫ መካከል የሚገኙ ብርቱ ሴት ናቸው። ከዛም በተጓዳኝ በዓለም ላይ በድንቅ ብቃቱ የሙዚቃውን ዓለም አጀብ ያሰኘው የትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ሕይወት ውስጥ ያላቸው አሻራ ግዙፍ ነው። አበበ ዘገየም የወጣቱ ድምጻዊ ስኬት ለወጣቶች፣ ድምጻዊው እናቴ የሚላቸውን የአያቱ ታሪክ ደግሞ ልጆቻቸውንና በባህር ማዶ ለሚያሳድጉ፣ የማንነት አሻራን ሳያጠፉ እንዴት ልጅን ለስኬት ማድረስ እንዲቻል እንዲረዱ ሲሉ ይህን ታሪክ አካፍለውናል።

የድምጻዊው ታሪክ ከመሠረቱ
አንድ ትውልድ ከሌላው ትውልድ የሚተሳሰርበት ድልድይ በአስተዳደግ ማነፅ ሲሆን፣ ለነገ ሀገር ተረካቢነት የሚያስፈገውን በጎ ነገር በማስተማርና በማውረስ፣ ዝንባሌን በመከታተልና በማበረታታት የወላጅ ወይም አሳዳጊ ሚና ቀላል አይደለም።
የሥነ-ሕይወት ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣና ሲሄድ ምንም ዓይነት ነገር ይዞ አይደለም ይላሉ። ነገር ግን ከአሳዳጊ ወላጆቹ (ሞግዚቶቹ) እንዲሁም ከአካባቢው ተፅዕኖ የተነሳ አዳዲስ ነገሮችን ይለማመዳል ሲሉም ያክላሉ። ከሌሎች መቅሰም ብሎም በዚያው ተፅዕኖ ስር መውደቅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ቢሆንም፣ በአስተሳሰብ ረገድ በተግባር መበልፀግና ማስመስከር እውነታው ይኸው ነው። ከዚያም የሚኖርበትን ምድር በተናጠል እያስተዋለ ወይም እየተገነዘበ መለማመድ ይጀምራል።
የራሱን ዝንባሌና ተሰጥኦ፣ ማንነትንም ፍለጋ ይቀጥላል። ራስን የመሆን የወደፊት እጣ ፋንታ ሕልም ይጫራል። ይህ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ክስተት ሳይሆን በረጅም ጊዜ አብሮ የሚያድግ ሂደት ነው። የህልውናው መሠረትም ይኸው ነው። ቀስ በቀስ በራስ የመተማመን ችሎታና ብቃት ሲዳብር ለተሻለ ውድድር ራስን ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብ የሚመራውን ፈለግ መከተል ይቀጥላል።

የአንድ አዳጊ ልጅ አስተሳሰብ መዳበር የሚጀምረው ከአሳዳጊ ወላጅ ወይም ሞግዚት አልያም ከማኅበረሰቡ በሚጋራው የእሴት ትስስር አማካኝነት ነው። ለአብነት ብናነሳ አንድ ብላቴና የሙዚቃ ዝንባሌና ፍቅር ሊያድግበት የሚችለው አንድም በሕጻን አዕምሮው የተቀረጸ፣ እቤት ውስጥ ከአሳዳጊው ወይም ከሞግዚቱ አዘውትሮ የሚያየውና የሚያስተውለው ሁናቴ ተፅዕኖ እንደሚያድርበት አያጠራጥርም።

ይህን ነጥብ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ ጉዳይ ይቆየንና አንድ ሌላ ታሪክ እናንሳ፤ ስለ ዘመናዊ ትምህርት። በአገራችን ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት የመስፋፋቱ ጉዳይ ሲነሳ አጼ ምኒልክ ያደረኩት ጥረት የሚጠቀስ ነው። ይህ በጎ ጥረት ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው ዓላማቸውን ሕዝቡ ሲገነዘብና ሲቀበላቸው በመሆኑ፣ መንግሥታቸውን ከማዋቀር ባሻገር ቀዳሚ እርምጃ የወሰዱት ዘመናዊ ተማሪ ቤት በመክፈት ነው፤ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት።

ይህንን ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ እንዲህ የሚል አዋጅ አስነገሩ፤ «መኳንንትና መሳፍንት በሙሉ ልጆችህን እየሰበሰብክ እከፈትኩልህ ትምህርት ቤት ድረስ አምጣልኝ። ባታመጣልኝ ግን ትቀጣለህ» ይህንን አዋጅ ተከትሎ የመኳንንትና የመሳፍንት ልጆች ወደዚህ ትምህርት ቤት ተሰበሰቡ።

በታሪክ አጋጣሚ ከእርሳቸው ቀጥሎ አገሪቱን ለመምራት ሥልጣን የተረከቡት አቤቶ ኢያሱ እና ራስ ተፈሪ መኮንንም በዚሁ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ዳግማዊ ምኒልክ መምህራንን ከግብጽ በማስመጣት በሰኔ 1899 ዓ.ም የመጀመሪያውን ዘመናዊ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲቋቋም አደረጉ። ዳይሬክተሩም ሚስተር ሙሴ ሃናቤይ ሰሊብ ሲሆኑ ለጊዜው ትምህርት ቤቱ ‹እሪ በከንቱ› ተብሎ በሚጠራው ሠፈር የሙሴ ኢልግን መኖሪያ ቤት በመጠቀም የነበረ ሲሆን፣ ከዚያም አራት ኪሎ ወደሚገኘው ግቢ ሕንጻ ውስጥ ተዛወረ።
የአጼ ምኒልክን ፈለግ በመከተል ተፈሪ መኮንን ለትምህርት መስፋፋት ካደረጉት ትልቁ ሥራ አንዱ ትምህርት ቤት መክፈት ተጠቃሽ ነው። የተፈሪ መኮንን ትምህርት አዳሪ ቤት በሚያዝያ 1917 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ዋና ሹም የነበሩት ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ነበሩ። ይሰጡ የነበሩት የትምህርት ዓይነቶችም የፈረንሣይኛ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ግዕዝና አማርኛ ቋንቋ፣ ሥነ-ስዕል፣ ሙዚቃ፣ ጅምናስቲክ ትምህርቶች ናቸው።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ በርካታ ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻም ሳይሆን በሐረር፣ አስመራ እና ሌሎችም የጠቅላይ ግዛት ዋና ከተሞች ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲስፋፋ አድርገዋል።
የተደገረው ጥረት ለወንዶች ተማሪዎች ብቻ ያመቻቸ ስለነበር ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ተልከው የመማር እድል አልነበራቸውም። እጅግ ጥቂቶች በየቤታቸው ቄስ መምህራን እየተቀጠሩ ፊደል አስቆጥረዋል። ሆኖም ዳዊት ለመድገም ብቻ የሚያበቃ ነው። በተለይ ፊደል ለማስተማር የፊደል ገበታን በማዘጋጀት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱት ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ አይዘነጉም።

በኋላም እቴጌ መነን ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ መኳንንቶችን እየለመኑና እያሳመኑ እንዲሁም ደግሞ የእርሳቸውን ዓላማ በመደገፍ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊ ተማሪ ቤት እንዲልኩ ይህ የመጀመሪያው የሴቶች ትምህርት ቤት ተቋቋመ።
የእቴጌ መነን የሴቶች ተማሪ ቤት የተቋቋመው በግርማዊት እቴጌ መነን የግል ገንዘብ ወጪ ተደርጎ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ። ይህም ለወንዶች ብቻ ተስፋፍቶ የነበረውን የትምህርት እድል በሴቶች ረገድም እንዲሟላ ታላቅ ምኞት ስለነበራቸው ነው። በዚያን ጊዜ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሆነው ከውጭ ዜጎች የተሾሙት ማዳም ካሪኮይስ እና ማዳም ጋሪጉ ሲሆኑ ተማሪ ቤቱ በጣልያን ወረራ ምክንያት ተዘጋ።

ከዚያም በኋላ የተሾሙት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ሲሆኑ ከ1936 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ ለአስራ ኹለት ዓመታት በኃላፊነት አገልግለዋል። በትምህርት ቤቱ ይሰጡ የነበሩት የትምህርት ዓይነቶች ፈረንሣይኛ ቋንቋ፣ ግዕዝ፣ ሣይንስ፣ ሒሣብ፣ ባልትናና የቤት አያያዝ፣ የልብስ ስፌት፣ የሰውነት ማጎልመሻ፣ ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ እጅ ሥራ የመሳሰሉት ነበሩ። የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ እየሰፋ፣ ብቃታቸውም እየተረጋገጠ የምስክር ወረቀት ያገኙና በልዩ ልዩ ሙያ እየተሰማሩ አገራቸውን ያገለግሉ ነበር።
ለግርማዊት እቴጌ መነን የሴት ተማሪ ቤት እንዲቋቋም ብርታት የሆናቸው እናታቸው ወይዘሮ ስኂን ሚካኤል ለዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ወሎ ውስጥ በደሴ ከተማ የድኻ ልጆች እንዲማሩበት በ1920 በግል ገንዘባቸው መክፈታቸው ነው። ይህ መልካም ኣርአያነት ከእናት ወደ ልጅ ይሸጋገራልና ግርማዊት እቴጌ መነንም ምኞታቸው ተሳክቶ ትልቅ ተግባር ከወኑ። ከንጉሣዊው ስርዓት ለውጥ በኋላ ትምህርት ቤቱ የካቲት 12 ተብሎ ሥያሜው ተቀይሯል።

ስለ…..
በዚህ ትምህርት ቤት ከተማሩ ሴቶች መካከል ናቸው፤ ወይዘሮ ወሰኔ ኃይሌ። ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት ወደሆነን ጉዳይ የሚያዘልቁን ናቸው። የተወለዱት በአዲስ አበባ በፈረንሣይ ሌጋሲዮን አካባቢ በተለምዶ ቤላ አቦ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በእቴጌ መነን የልጃገረድ ሴቶች ተማሪ ቤት ገብተዋል።

በዚህ የሴቶች ተማሪ ቤት ለመማር እድል ያገኙት ወሰኔ ኃይሌ፣ በትምህርት ቤት ቆይታቸው በትጋት በመማር እንደማናቸውም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሴት ልጃገረዶች በየመንግሥት መሥሪያ ቤት የመቀጠር እድል አገኙ። በቴሌኮሙኒኬሽን ማሠልጠኛ ሥልጠና አግኝተውም በመሥሪያ ቤቱ በመቀጠር ጡረታ በአምሳ አምስት ዓመት እድሜያቸው ወጥተዋል። ከዚህ በኋላም ኑሮአቸውን በቶሮንቶ-ካናዳ አደረጉ።
ወሰኔ ጥሩ የድምፅ ቅላፄ ስለነበራቸው በቴሌኮሙኒኬሽን ቁጥር ስምንት ዓለማቀፍ ኦፕሬተርነት ተመድበው ለአገራቸው የበኩላቸውን አበርክተዋል።
ታድያ ከጡረታ በኋላ የወንድሞቻቸውን ልጆች በመርዳት ይተጉ ጀመር። በዚያው በውጭ አገር እየኖሩ በእናት የሚዛመዷትን ኹለቱን እህቶቿን ማለትም ሚሚ(ዘውድነሽ) ዘገዬ እና ትዕግስት ዘገዬ ልጆች እንዲሁም የልጃቸውን የሣምራዊት ኃይሉ ልጅ የሆነውን አቤል ተስፋዬን እንዲሁም የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ልጆች ያግዙ ነበር።

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ
አቤል ተስፋዬ የተወለደው እ.ኤ.አ የካቲት 16 ቀን 1990 በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ ሲሆን እድገቱም በዚያው ነበር። የስድስት ዓመት ሕጻን ሳለ ወላጅ አባቱ ተስፋዬ መኮንን ከባለቤታቸው (ከአቤል እናት) ተለይተው ሌላ በማግባታቸውና ልጆች በመውለዳቸው፣ አባቱን በቅጡ አያስታውስም።

የአቤል ወላጅ እናት ቤተሰቦቿን ለማስተዳደር ልዩ ልዩ ሥራዎች በመሥራት ጥረት ታደርግ ነበር። አቤልም እስከ ወጣት እድሜው ድረስ አያቱ ወይዘሮ ወሰኔ አሳድገውታል። የአማርኛ ቋንቋንም አቀላጥፎ ይናገራል። በዚያን ጊዜም ቢሆን የእነ አስቴር አወቀን፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አሕመድ፣ የሙላቱ አስታጥቄን የጃዝና ብሉዝ ጨዋታዎች እና ሌሎችንም የሀገር ቤት ሙዚቃዎች አዘውትረው ማዳመጥ ይወዱ ስለነበር የወጣቱ አቤል ድምጻዊነት የመጣው ከእሳቸው እንደሚሆን አሳማኝ ነው።
ቀጥሎም የፖፕ ንጉሥ በሆነው የማይክል ጃክሰን ሙዚቃ እየተሳበ በመምጣቱ ለፖፕ ሙዚቃ ልዩ ፍቅር አድሮበታል። አቤል በዚህ ሁኔታ ከአያቱ ወሰኔ ጋር አብሮ ሙዚቃ እያዳመጠ እና ወደ ቤተክርስትያንም እየሄደ አገልግሎት እየሰጠ በማደጉ አሁን ለደረሰበት የሙዚቃ ሕይወቱ ጉልኅ ተፅዕኖ ፈጥሮበታል። እ.ኤ.አ በ2007 በአስራ ሰባት ዓመት ለጋ እድሜው ትምህርቱን አቋርጦ ሲወጣ አያቱ ወሰኔ አብረዉት ነበሩ።

እ.ኤ.አ 2010 ወደ ሙዚቃው ዓለም ጭልጥ ብሎ የገባው ወጣቱ አቤል፣ ዝናን በማትረፍ በአሜሪካና አውሮፓ እየተዘዋወረ የሙዚቃ ድግሶችን አቅርቧል። በ2014 ሥሙ በቢል ቦርድ ሠንጠረዥ በመውጣት ለግራሚ ሽልማት በቅቷል። ምንም እንኳ ስለራሱ መናገር እምብዛም የማይፈልገው ወጣቱ ድምጻዊ፣ ከሙዚቃ ሕይወቱ ባሻገር በበጎ አድራጎት ሥራ በመሳተፍም ይታወቃል።

በ2014/15 ለአብነት ለዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ የግዕዝ ትምህርት ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሐምሳ ሺሕ ዶላር ለግሷል። በተጨማሪም ለራያንሲያክረስት ፋውንዴሽ ለሕጻናት ሆስፒታል መርጃ እና በአትላንታ የጥቁሮች ሕይወት ማሻሻያ በሚል ወደ ኹለት መቶ ሐምሳ ሺህ ዶላር ወጪ በማድረግ አበርክቷል።

በአቤል ሕይወት ውስጥ የወሰኔ ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ወሰ የወንድሞችና የእህቶቻቸውን ልጆች በማሳደግ የነበራቸውን ልምድ በማስፋት፣ በውጭ አገር የዘመዶቻቸው ልጆች በሥነ ምግባር የታነፁ፣ በትምህርታቸው ትጉህ እንዲሆኑ፣ ራሳቸው በየጊዜው ዝንባሌያቸውን በመከታተል ማበረታታት ዋናው በጎ ተግባራቸው ነው። ለዚህ የልጅ ልጃቸው ወጣቱ አቤል ተስፋዬ ማንነትና እድገት ማሳያ ነው።

አቤል እስከ ወጣት እድሜው ሁለንተናዊ ስብዕናውን ቀርጸው ባሳደጉት አያቱ ወሰኔ ኃይሌ እጅ መታነፁ ቁም ነገሮች በእሱ ሕይወትና ስኬት ዙሪያ የማንነት አሻራ እንዲያጠነጥን አስችሎታል።
አቤል በወጣትነት እድሜው ይህንን የመሰለ ውጤት ለማግኘት የቻለው በልጅነቱ በሁሉም መስክ ታታሪ በመሆን፤ ጥረት በማድረግ የተሰጠውን ኃላፊነት በመቀበል፤ የተሰጠውን ትእዛዝ አሟልቶ በመፈፀም ነው። ለዚህም የረዱት ወሰኔ ኃይሌ ናቸው። የእርሳቸው ልምድ በሚያሳድጉት የልጅ ልጃቸው አቤል ሕይወት ውስጥ እንዲንፀባረቅ፣ የጥበብ ዝንባሌውን ከማንም ሰው በፊት በቀላሉ ለመገንዘብ እድሉን ያገኙት እርሳቸው ናቸው። በእርግጥ የወጣቱ የራስ ጥረት ቢኖርም አንድ ዛፍ ቀጥ ብሎ ለምልሞ ሊያድግ የሚቻለው ገና በለጋነቱ ተገቢው እንክብካቤ ሲደረግለት እንደመሆኑ ለወደፊትም ተስፋ፤ ብቃትና ንቃት እንዲኖራቸው ወጣቶችን ለማድረግ በሕጻንነት የሚደረገው ክትትል አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሕጻናትም በሥነ ምግባር እንዲታነፅ በእውቀት የማደግና የመማር ፍቅር እንዲኖር፤ ተሰጥኦውንም እንዲለማመድና ለአደባባይ እንዲበቃ የአሳዳጊ ትኩረት፤ የአስተማሪ እገዛ እጅግ ወሳኝ ነው።

ዛሬ በዝነኛ አርቲስትነቱ በዓለም የሚታወቀው አቤል ተስፋዬ በዓለም ሙዚቃ መድረክ ስሙ እየናኘ ጥረቱ፣ በሙዚቃ ጥበብ ልዩ ችሎታው ይደነቃል።
ለማጠቃለያ ይሆን ዘንድ ሙዚቀኛ አቤል ተስፋዬ ለአንድ መገናኛ ብዙኀን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሰጠው ቃለ መጠይቅ (በዩትዩብ ከተለቀቀው – ታህሳስ 8, 2018) ስለቤተሰቦቹ የሚከተለውን ብሏል፡- ‹‹ቤተሰቦቼ በተለይም እናቴ/አያቴ እኔን ስለ አገሬ ባሕልና ማንነት እንድገነዘብና እንድኮራ አድርገውኛል። በተለይም ትምህርት አቋርጨ ፍላጎቴ ወደ ሙዚቃ ማዘንበል፣ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ ታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች በማዜም ጭምር ተፅዕኖ ነበራቸው። በልጅነት እድሜዬ አንድ የምወደውን ነገር ሳደርግ ሁሉ እናቴ/አያቴ ደስ እያላት ታበረታታኝም ነበር።”


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com