የእለት ዜና

የጊዜ አበዳሪዎቹ

ፒያሳ፣ ከአንድ ካፌ ተቀምጫለሁ። ቀጠሮዬ እስኪድረስ የፌስቡክ ገጼን አገላብጣለሁ። ከመዝገቤ ላይ ከመጡ በርካታ የእንቶፈንቶና ጥቂት የቁምነገሮች ልጠፋዎች መካከል ከወራት በኋላ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክቶ በአንድ ወዳጄ የሰፈረች አጭር ሐተታ ላይ ቀልቤ አርፏል። ታድያ በሐታተው ላይ ለሰጠው ድምዳሜ ጸሐፊው በአስረጂነት ከተጠቀማቸው ጉዳዮች መካከል ከጊዜያት በፊት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ተቃዋሚዎች (‹ተፎካካሪ› ምትለው ቃል ያኔ አልተጠቀሙም) ፓርቲዎች አብረው በመደራጀት እና ተጠናክረው በመዘጋጃት መወዳደር አለባቸው የሚል ምክራቸው አንዱ ነው።

ከሐተታው ተመልሼ ሰሞኑን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን እያስደመጡን(እያስነበቡን) በሚገኘው ምርጫ ላይ ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች ስንቱ እንደተቀናጀ፣ እንደፈረሰ፣ እንደተዋሃደ ደግሞም በምርጫው ላይ ለመሳተፍ አትችሉም ተብለው በምርጫ ቦርድ ተሰርዘው ወደ ግለሰቦች ስብስብነት የተቀየሩትን ‹የቀድሞ ፓርቲዎች›ን ምን ያህል እንደሆነ መቁጠር ጀመርኩኝ። ሆኖም ቆጥሬ ሳልጨረስ ከተወሰኑ ወራት በፊት ወደ ነበርኩበት ኹነቶች፣ ከአያቴ ጋር ከነበሩኝ የመጨረሻዎቹ ቆይታዎች መካከል ወደ አንዱ በትውስታ ተመለስኩኝ።

ከአያቴ ቤት ሳሎን ላይ እኔ እና አያቴ አያወጋን ነው። የጀምርነውን ወሬ በቅጡ ሳንጨርስ በፊት ‹‹ልጄ፤ ብዙ ያልተመለሱ ብድሮች እንዳሉብኝ፣ ባለ እዳዎቼም በርካታ እንደሆኑ ነግሬህ አውቃለሁ?›› አለኝ። ምላሼ የነበረው ረጅም ሳቅ ነበር። የሳቄ ምክንያት አያቴ እና ብድር ፍፁም የማይተዋወቁ እንደሆኑ ስለማውቅ ነበር። አያቴ ‹‹የትኛውም ተበዳሪ በቃሉ የተገኘበት ኩነት በብድር ታሪክ አልተፈጠረም›› የምትል እንደ አንዳንድ የአገራችን የታሪክ ምሁር ነን ባዮች፣ ከግለሰብ ምኞት እና ፍላጎት የመነጨች የታሪክ መደመደሚያ ነበረችው። ለብድር ባለው የመረረ ጥላቻ ከመንደሩ አልፎ በከተማው ሥሙም ዝነኛ ነበር። በፊቱ አማካኝነት ሳቄን እንዳቆም ትዕዛዝ ሲደርሰኝ ‹‹ጋሼ፣ ብድር እጅግ ትጠላ አልነበረም እንዴ? ከየት የመጣ ብድርና ባለ ዕዳ ነው?›› አልኩት።

ጊዜ ሳይፈጅ ‹‹አይ ልጄ! የብርና የንብረት ብድርማ ከሆነ እውነት ብልሃል። ነገሩ ሌላ ነው እንጂ።›› አለኝ። ‹ምን ይሆን?› ማውጠንጠናዬ ሥራ በዛበት። ‹‹ስማ ልጄ! ከጊዜ የተለቀ ውድ ነገር ምንም የለም። ከብድሮች ሁሉ ትልቁ ብድር ጊዜን ማበደር ነው። ማንም ጉልበቱ ላይ ወድቅህ፣ ምንም ያክል ተንስቅስቀህ ብትለምነው ጊዜን የሚያበድርህ አንድም ሰው አታገኝም። ግና እኛ በተለይ በአሁን ዘመን ሕዝቡ ካለ ስስት የሚያበድረው ነገር ቢኖር ጊዜን ነው።›› ሲለኝ ስለ ወጣትነት፣ ስለ ሥራ ሊመክረኝ እንደሆነ ገባኝና ለወሬው የነበረኝ ጉጉት ቀነሰ።

እሱ ቀጥሏል ‹‹ምን መሰለህ ልጄ፣ ‹ወያኔ› ከመጣ በኋላ ንጉሡ ቀድሞ አምጥተው የነበረውን ምርጫ የሚባል ነገር አመጣና፣ ከአሁን በኋላ 4 ኪሎ የሚገባውን እናንተ ነው የምትመርጡት አለን፤ እንዴት ደስ ብሎኝ ነበር መሰለህ! አወይ ሽወዳ!›› ሲለኝ ፈገግ አሰኝኝ። ‹‹አያስቅም ልጄ፤ አያስቅም። ምርጫ ማለት ቦለቲከኞች ከመረጣችሁን የጎደለውን ሁሉ እንሞላለን፣ መሻታቸሁን እንፈጽምላቸኋን ብለው ሰብክው፣ ከዛች ሳጥን ነገር ውስጥ ይሻለኛል የምትለውን ባርቲ የሚወክላቸውን ምስልን በሚሰጡት ካርድ ላይ አስቀመጥክ ማለት ነው። ይህን ስታደርግ ጊዜ አበድርከው ማለት ነው ልጄ። ለአምስት ዓመት ኑሮዬን ያሻሽላል፣ ነፃነቴን ያረጋግጣል፣ ለሚመጡት ትውልዶች የሚጠቅም ቁምነገር ሠርቶ ያልፋል ብለህ አይደል ከቀረቡልህ ተበዳሪዎች መካከል የተሻለውን የምትመርጥ።›› መስማማቴን በምልክት ገለጽኩለት።

‹‹እኔም አስቀድሜ ያልተመለሰሉኝ ብድሮች ያልኩህ እሱን ነው ልጄ። በተለይ ክፍለ ዘመን ሳንቀየር በፊት የሆነው ምርጫ ሳስብ፣ ከምንም ነገር በላይ ያብከነክነኛል።›› ብሎ በከዘራው ወለሉን ደብደብ አደረገ። ቀጠለና ‹‹ስመርጥ እኔስ አርጅችያለሁ፣ ግና ለሚመጣው ትውልድ የሚበጅውን ሐሳብ የያዘ፣ ጥሩ ተበዳሪ የትኛው ነው ብዬ አሰላስዬ ነበር የነበረው። ግና አንዱም ተበዳሪ ቃሉን አክባሪ ሆኖ አላገኘሁትም፤ ሀገሬ ብድሩን በጊዜው መላሽ መች አግኝታ ታውቅና! ለነገሩ ምርጫችን የሆነው ቀድሞስ መቼ አክሊል አንስ›› ሲለኝ አስገረመኝ። ‹‹ያኔ ብድሮቻችን በጊዜው እያስመለስን፣ አስፈላጊም ሲሆን ተበዳሪዎችን እየመዘንን ብንቀይር ኖሮ ዛሬ ለእናንት የተሻለች ኢትዮጵያ ባስረክብናችሁ ነበር›› እንዲህ ስሜታዊ ሆኖ አይቼ አላቅም እና አስደነገጠኝ።

‹‹ያለፈው አልፏ ልጄ፤ አሁን እየው ምርጫው ደርሶ አይደል?!፤ በል አደራዬን ተቀበል። እምቢ የማለት ፍላጎት ባይኖረኝም፣ ምርጫም አልነበረኝም። ‹‹በእድሜም ሆነ በብስለት ብቁ ሆነ ከአበዳሪዎች መካከል አንዱ አንተ ሆነሃልና፣ አደራ አበዳሪህን ስትመረጥ በጥንቃቄ፤ አደራ ልጄ!›› አደራውን ለመቀበል ጊዜ ሳይሰጠኝ ‹‹የዛሬ አበዳሪዎች ምርጫችሁ በሥርዓት እንዲነግስ አድርጉ፣ እንደሱም ከሆነላችሁ ብድሩን በጊዜው እና በቃሉ መሰረት እንዲመልስ ይሆን ዘንድ ተከተታሉ።››

የስልኬ ጥሪ ከትውስታዬ መለሰኝ። ወዲያው ከወራት በፊት ያለፈውን አያቴ የሰጠኝን አደራ እኔም ሆነ ሌሎች እንዴት እንደምንጠብቅ ማሰብ ጀምርኩኝ። የጠቅላይ ሚስትሩን ምክር ሰምተው ይሆን ምርጫ መድረሱ ትዝ ብሏቸው ፓርቲዎቹ የጊዜ ተበዳሪ ለመሆን በግልጥም ሆነ በስውር ዝግጅት እያደረጉ ነው። ‹‹እኛ አበዳሪዎቹስ?›› ተቃዎሚዎቹን የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነ ሌላው ተዘጋጁ ሲሉ እኔ አልሰማሁም። እኔ ግን እንዲህ እላለሁ ‹‹ዘንድሮ አምስት ዓመታችንን ስናበደር በጥንቃቄ ነው። ለዛውም በውዴታችን ብቻ! የውዴታችን ተበዳሪ በስርዓት ካሸነፈም፣ ከሹመቱ ማግስት ጀምሮ የሰጠነውን ብድር ቆጥረን ነው የምንቀበለው።›› እንዴት ለሚለው ጥያቄ በቀጣይ እንመለከተዋለን።

በመንግሥት የልማት ድርጅት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ናቸው በኢሜል አድራሻቸው firewutopia@gmail.com ይገኛሉ።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com