ምርጫ 2013 – ሴቶች የት አሉ?

Views: 202

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ ውይይት ከተነሳ፣ ‹የሴቶች የመሪነት ተሳትፎ ወርቃማ ዘመን› ተብሎ የተቀመጠ የሚመስልና የሚነሳ ኹነት አለ። ይህም ወደኋላ መቶ ዓመታትን ተጉዞ እቴጌ ጣይቱ እና ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱን የሚያወሳ ነው። ያንን ወቅትና በጊዜው በነበረው የፖለቲካ አሠራር ውስጥ የነበሩ ሴቶች ጀግንነትን ለማውሳት አሁን ላይ መድከም ባይታይም፣ አረአያነቱን የተከተለ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎም ሆነ የተሰጠ ምቹ እድል ግን የለም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2013ን ምርጫ በማስተባበርና በመምራት ሥራው ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ትኩረት ስጡልኝ ብሎ ካሳሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የሴቶች ተሳትፎ ነው። እንደውም ሴቶችን በሚገባ ካሳተፋችሁ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅም ታገኛላችሁ የሚል ማባበያ የመሰለ ማበረታቻ ሳይቀር አክሏል።

እንዲያም ሆኖ ታድያ የሴቶች ተሳትፎ በጭራሽ አለ ለማለት እንኳ የሚጠጋ አይደለም። ‹በዝተዋል› ከሚባሉ በርካታ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህም የ2013 ምርጫ ላይ ሴቶችን በላምባ መፈለግ ሳይጠይቅ የማይቀር ነው።

በተለያየ ጊዜ ሴቶችን ወደ አመራነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት እየተሠራ እንደሆነ ቢስተዋልም፣ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት እንዳልተቻለ ግን ሁኔታዎች ምስክር ናቸው። ‹ዩ ኤን ውመን› የተባለው ድርጅት አደረግኩት ባለው ዳሰሳ መሠረት፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አሁን በያዘው አካሄድ ከቀጠለ፣ በሕግ አውጪነትና በሚኒስትርነት ሴቶች በስፋት ተሳትፈው ለማየት ቢያንስ ከ40 ዓመት በላይ መጠበቅ ያስፈልጋል።

የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ ጾታ አካታችነትን በተመለከተ ከተለያዩ አጋር ዓለማቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር 70 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ ጥናት ይፋ አድርጓል። የጥናቱ ግኝት ታድያ ‹ሴቶቹ የት ሄዱ?› የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ኹለት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በቆንጂት ብርሃነ የሚመራ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ በምክትል መሪነት ማርታ ካሳን የያዘ ሆነው ተገኝተዋል።

በግልጽ ሴቶችን ከውሳኔ ሰጪነት እንዳይሳተፉ አድልዎን በመፈጸም የከለከሉ ስድስት ፓርቲዎች ሲገኙ፣ 21 የሚሆኑት ደግሞ በአንጻሩ በተለያየ የፓርቲው የኮሚቴ መዋቅር ውስጥ ሴቶችን አካተዋል። ከዛ ሁሉ የሚብሰው ደግሞ ከ15 ፓርቲዎች በቀር የተቀሩት ከያዟቸው የፖለቲካ አጀንዳዎች ውስጥ ስርዓተ ጾታን በሚመለከትና በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የታሰበ አሠራር የላቸውም።

የት አሉ?
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተገፍቶ 2013 ግንቦት ወር ሊሆን የታቀደው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ፣ የሴቶች ተሳትፎ የጎላበት እንዲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሞከሩን ግን የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ተናግረዋል። ቦርዱ የሴቶችን ተሳትፎና እጩነት ለፓርቲዎች እንደመስፈርት ቢያስቀምጥ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቅሬታና የአንቀበልም ግፊት እንደደረሰበትም አውስተዋል።
እንደውም የፖለቲካ ፓርቲ አባላቱና መሪዎቹ ‹‹እንኳን ለሴት ለወንድ አይሆንም›› ይላሉ፣ የፖለቲካውን ምህዳር።

ምርጫ ቦርድ በርከት ያሉ ሴቶችን በእጩነት ለያዙና ላሳተፉ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞችን እሰጣለሁ ማለቱ ሳይቀር ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞታል። ‹‹በእኛ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ትኩረት እንዲሰጡ የምናደርገው ጥረት ብቻውን በቂ ነው ብለን አናምንም።›› ብለዋል ሶልያና።

ወዲህ ደግሞ ‹በማባበል ብቻ አይሆንም› የሚል ሐሳብ አላቸው፣ ሴቶችን በማብቃት ላይ የሚሠራው ‹ትምራን› የተሰኘ የሲቪክ ማኅበር የፕሮጀክት አስተባባሪና መሥራቾች መካከል የሆኑት ሀዲያ ሐሰን። ምንም እንኳ ምርጫ ቦርድ በተለያየ መንገድ ማበረታቻ በመስጠት የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ለማድረግ የሚያደርገው ሙከራ ቢበረታታም፣ የተጻፈው ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን መጫንና መግፋት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

‹‹ስለተጻፈ ደስ ብሏቸው [ፖለቲካ ፓርቲዎች] ይቀበላሉ/ይተገብራሉ ማለት አይደለም። ያንን የማበረታታትና የማንቃት ሥራ መሥራት አለብን።›› ያሉ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ድርጅታቸው ሲሠራ የቆየውን ዳሰሳና ጥናት አያይዘው አንስተዋል።
እርሳቸው የሚሠሩበት የሲቪክ ማኅበር በሠራው የዳሰሳ ጥናት፣ እውቅና ከተሰጣቸው ፓርቲዎች መካከል ከሃያዎቹ ፓርቲዎች አንድ የሴትና አንድ የወንድ ተወካይ በመሰብሰብ ‹ሴቶቹ የት አሉ?› ሲሉ በመጠየቅ መድረክ ከፍተው አናግረዋል። በዚህም ከአባላቱ የተሰጡ መልሶች የእውነታው ማሳያ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ሀዲያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ያንን መድረክ መለስ ብለው ሲያስታውሱ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አስጨናቂ ከባቢ በመሆኑና ባህሉም ግጭት ስለማይጠፋው ነው ሴቶች ራቅ የሚሉት የሚል አስተያየት መሰጠቱን አንስተዋል። ሴቶች ይህን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጸባይ ለመቻል የታገሱ እንኳ ቢሆኑና ሊጋፈጡ ቢገቡ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ ማኅበረሰባዊ ተጽእኖ ይከተላቸዋል።

‹‹አንቺ ምን ለውጥ ልታመጪና ልትቀይሪ ነው!›› የሚለው በራሱ ጭንቀት ነው ሲሉ ሀዲያ ተናግረዋል። ከትዳር አጋራቸው፣ ከቤተሰብም በተዘዋዋሪ ‹ለወንዶቹ የከበደ ለእናንተማ…› የሚል ሐሳብ በተሸከመ አነጋገር፣ ‹‹አርፈሽ ተቀመጪ!›› ይባላሉ።
ታድያ ይህንንም አልፈው የተገኙ አልጠፉም። እነዚህ ሴቶች ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ራሱ የተለያየ ጾታዊ ትንኮሳና ተጽእኖ ይደርስባቸዋል።

ከዚህ ትንኮሳ አንደኛው ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ ነው። ‹‹ሴት ፕሬዝዳንት ቢሰይሙ እድል የሚያሳጣቸው ይመስላቸዋል።›› ይላሉ ሀዲያ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የተሳተፉ ሴቶች ፈተና ነው ያሉትን በመጥቀስ። በዛም ላይ ጾታዊ ጥቃት አለ። ስብሰባዎች ምሽት ላይ ይካሄዳሉ። ሴቶች በቤታቸውና በማኅበረሰቡ ያላቸው ድርሻ ከግምት አይገባም፣ ፓርቲዎቹ ለሴቶች ምቹ ኹኔታንና ከባቢን መፍጠር ላይ አይሠሩም። እንደውም ከውጪው የበለጠ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ራሳቸው ሴቶቹን ያስጨንቃሉ። ይህን ያየችና የሰማች ሴት ወደ ፖለቲካው መጠጋት ከሕልም የዘለለ ሩጫ አታደርገውም።

ነገሩ ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ እንዳይሆን፣ ከእነዚህ ችግሮች የጸዱ አይሁኑ እንጂ፣ በአንጻራዊነት በጎ የሚባልና የሚበረታታ፣ የተሻለ ለሴቶች ቦታ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልጠፉም። ነገር ግን በቂ ናቸው ማለት አይደለም። ሀዲያን ጨምሮ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ሐሳብ የሰጡ ሰዎችም የሚፈለገውን የሴቶች የምርጫ ሰሞንና የፖለቲካ ተሳትፎ በዚህኛው ምርጫ ላይ ለማየት የሚያስችል ሥራ አሁን ላይ መሥራት አይቻል ይሆናል የሚል እይታ አላቸው።

እንደውም ‹ሠርገኛ መጣ!› የመሰለ የ‹ሴቶችን አሳትፉ!› ጥሪና ቅስቀሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነተኛና ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ሴቶችን እየጠቀሱ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኛ እንዳያደርጉት የሚሰጉም አልጠፉ። በአጠቃላይ ግን ይህ የአሁን ላይ የተነሳው ‹ሴቶች የት አሉ?› የሚል ጥያቄ አምስት ዓመት ጠብቆ በሚካሄደው ቀጣዩ ምርጫ መልስ እንዲያገኝ የሚያስችለውን ጉዞ ማስጀመሪያ ሊሆን ይገባል።

መራጮችስ…ጫና መፍጠር አይችሉምን?
ሴቶች ለምን እቴጌ ጣይቱን ከማድነቅ፣ ንግሥት ዘውዲቱን ከማሞገስ በተጓዳኝና በበረታ መልኩ በፖለቲካው በብዛት አይሳተፉም? ብዙ ምክንያት ሊዘረዘር ይችላል። እርግጥም እጩ ለመሆን ብቅ ብቅ የሚሉ ሴቶችን ዙሪያ የሚከባቸው ፈተና፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ጸባይ በማንኛውም ሰው ላይ ሊያደርሰው ከሚችለው ጫና ላይ በተጨማሪ ተደራቢ መልክ ያለው ነው።

ሴቶች በተመራጭነት ተሳታፊ ከመሆን በተጓዳኝ፣ የእጩነት በሮችን ለማስከፈት የሚያስችል የመራጭነት አቅማቸውንስ አውቀውታልን? ብለን እንጠይቃለን። ይህን ስንል ፖለቲካውን በፍትሐዊ ሚዛን ላይ እንደተቀመጠ በማሰብ ነው።
በአገራችን እንዲሁም በዓለም ደረጃ የሴቶች ብዛት ከጠቅላላ ሕዝብ ግማሽ በመቶ በላይ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የወጡ የሕዝብ ቆጠራ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በምርጫ ደግሞ ሕዝብ ባለድምጽ ነውና ትልቁ ኃይል እንዳለው ይታወቃል። ተመራጮችም ሕዝቡን ይሰማዋል፣ ይነካዋል፣ ያሳስበዋል ያሉትን ጉዳይ መርጠው ነው በጉዳዩ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርቡትና በዛ ላይ ለአሸናፊነት የሚወዳደሩት።

ታድያ የሴቶች ቁጥር ብዛት ችግሮቻቸው ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማስቻል ትልቁ አቅም ነው። በድምሩ ሴቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የጋራ አቅም አላቸው ማለት ነው። በኢትዮጵያ የ2013 አገራዊ ምርጫስ ይህን ተጽእኖ መፍጠር አይቻልም ወይ?
እንደ ሀዲያ ገለጻ ከሆነ ሴቶች እንኳንና እንዲህ ያለ ተጽእኖ ለመፍጠር እንዲሁም ‹አማራጭ ፖሊሲያችሁ ለእኔስ ምን ይዟል?› ብሎ ለመጠየቅ ይቅርና የመምረጥ መብታቸውን ራሱ እንዲያውቁና ያም እንዲከበርላቸው ገና ብዙ ቀሪ ሥራዎች አሉ። ሴቶች ድምጻቸውን መስጠታቸውና መምረጣቸው ታሪክ ሊቀይር እንደሚችል፣ የመረጡት ፓርቲ እንደሚመራቸው የማመንና የማወቅ ባህል ገና አልዳበረም ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራዊ ቅንጅት የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ መሠረት አሊ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳነሱት፣ ቅንጅቱ ሊከውን ካሰበው ሥራ አንዱ ለመራጮች ሥልጠና መስጠት ነው። ‹‹ለመራጮች ትምህርት የሚሰጡ ሰዎችን ለማሠልጠን ፈቃድ እየጠየቅን ነው። …ሴቶች እንዲመርጡም የሚያነቃቃ ራድዮን እና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን በቀጣይነት እንሠራለን።›› ብለዋል።

አብዛኞቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ታድያ ከአስቸጋሪውና ከመነጋገር ይልቅ መቃቃርና መገዳደል የሚስተዋልበት የፖለቲካው ምህድር ውስጥ ሆነው፣ የሴቶችን ተሳትፎ ማንሳትና ማገናዘብን ‹እዬዬም ሲዳላ!› ዓይነት ያደረጉት ይመስላል። ‹እንኳን ለሴቶች ለእኛም ከብዶናል› የሚለው አስተያየታቸውም ከዚህ የሚወለድ እንደሆነ መገመት አያስኮንንም። ሆነም ቀረ ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ አሠራሮች፣ አመለካከቶችና ስርዓቶች 40 ዓመት ሳይጠብቁ በቀጣይ ምርጫ እንደሚስተካከሉ ተስፋ በማድረግ፣ 2013 ምርጫ ላይ ሴቶቹ የት አሉ የሚለውን ጥያቄ ይዘን እንቆያለን።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com