ኮሮና የነጠቀን ታላላቆች

Views: 208

ወደ አገራችን ከገባ አንድ ዓመት ሊሞላ ቀናት ብቻ የቀረው የኮሮና ቫይረስ እያዋዛ ሥርጭቱ ጨምሮ ዛሬ ላይ በአጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደርሷል። ከእነዚህም መካከል ላለፉት 11 ወራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከሁለት ሺህ ሶስት መቶ በላይ ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

መጋቢት 3/2012 አንድ ጃፓናዊ ዜጋ ላይ በተደረገ ምርመራ ነበር ቫይረሱ በአገራችን መከሰቱ የተረጋገጠው። ኮሮና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መልኩን እና አይነቱን ቀይሮ ለብዙ አገራት የራስ ምታት እንደሆነ ቀጥሏል።
በእኛም አገር ኮሮና ሕይታቸውን ካሳጣቸው መካከል ታዋቂ ሰዎች ያገኙበታል፡፡ ከዚህ ሳምንት ካጣናቸው አንጋፋዎቻችን ብንጀምር እንኳን የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነ ብርሃንን ማንሳት ይቻላል።
በ 72 ዓመት ዕድሜያቸው በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈው የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃን ከኢትዮጵያ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥነ ቆዳ ሕክምና (ዴርማቶሎጂ) ታዋቂና ግንባር ቀደም ሐኪምና ልሂቅ ተመራማሪ፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያም ሆነው ለ50 ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

የዓለም ሎሬት ዶክትር ጥበበ የማነብርሃን በሕክምናው ዘርፍ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ ባሳተሟቸው ከስድሳ በላይ የምርምር ወረቀቶች፣ የሕክምና ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ስፔሻሊስቶች በአገናዛቢነት ይጠቀሙባቸዋል። በቆዳና በአባለዘር በሽታዎች ላይ ያደረጓቸው ጥናቶች በኢትዮጵያ ብቻ የተገደቡ ሳይሆኑ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ የታወቁ ናቸው።

የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃን በሕክምና ሞያ፣ በሀገር ሽማግሌነት፣ በዕርዳታ አስተባባሪነት እና በዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባልነት አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው ማረፋቸው ተሰምቷል ።
የተከበሩ የአለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሀን የሞቱት በኮሮና መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ሌላኛው ኮቪድ ያሳጣን ጉምቱ ሰው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ናቸው።

ከኢትዮጵያ የአደባባይ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ90 ዓመታቸው መስከረም 19/2013 ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ፕሮፌሰሩ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ሆስፒታል ለ 11 ቀናት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ነበር።

ፕሮፌሰር መስፍን ወደ ሆስፒታል ከመግባታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ጭምር፤ ለረጅም ዓመታት ጉልህ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩበትን የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎችን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ሲያስነብቡ ቆይተዋል።
አድናቂዎቻቸው “የኔታ” “ፕሮፍ” እያሉ የሚጠሯቸው ፕሮፌሰር መስፍን፤ ማህበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ በመጽሐፍት፣ በመጽሔቶች፣ በመገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቆች እና በአደባባይ ውይይቶች ትችቶችን እና ሸንቋጭ አስተያየቶችን በመሰንዘር ይታወቁ ነበር። “ዛሬም እንደትናንት” የተሰኘ የመጨረሻ መጽሐፋቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ ለንባብ ያበቋቸው መጽሐፎችም በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሂስ የተቃኙ ናቸው። እንደ ምሳሌም “ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”፣“አገቱኒ፤ ተምረን ወጣን”፣ “አዳፍኔ፤ ፍርሃትና መክሸፍ”፣ “እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ”፣ “ሥልጣን – ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ” እና “ዛሬም እንጉርጉሮ” ይጠቀሳሉ።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com