ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባና ተያያዥ ኹነቶችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቀረበ

Views: 147

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛውን አገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ እና ተያያዥ የምርጫ ሁነቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቀረበ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 16/2013፣ የ6ተኛው አገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ እና ተያያዥ የምርጫ ሁነቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶች ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት አቅርቧል። ሪፖርቱ ሦስት አጀንዳዎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን በቅድመ ምርጫ ጊዜ፣ በምርጫው ጊዜና በድኅረ-ምርጫ ጊዜ የሚኖረውን የመረጃ አሰጣጥ ሂደት የተመለከተ ሪፖርት በቦርዱ የመራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረባ አማካኝነት ሲቀርብ፣ ቦርዱ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች በሚከፈትበት ወቅት ያጋጠሙትን የኦፕሬሽን እና የሎጂስቲክ ፍሰትን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች በቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባ ቀርቧል።

አጠቃላይ ሂደቱ ምን እንደሚመስልና ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል የሚለውን ደግሞ በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አቅርበዋል። ሰብሳቢዋ በንግግራቸው በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የሎጀስቲክ እንቅስቃሴና አስፈጻሚዎች በተገቢው ሰዓት ከምርጫ ጽህፈት ቤት ወደ ምርጫ ጽህፈት ቤት እየተንቀሳቀሱ ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመጓጓዣ መኪኖች ከክልል መንግሥት በሚፈለገው መጠን እንዳልቀረበና ይኽም አጠቃላይ የአፈጻጸም ሂደቱ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ ገልጸዋል።
መንግሥትም ሆነ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚጠየቁትን ትብብር በተገቢው ሰዓት መፈጸማቸው አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ላይ እንዲሁም የጊዜ ሠሌዳውን ተከትሎ ከመሥራት አንጻር ትልቅ ትርጉም ስላለው ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል። የባለድርሻ አካላት ኃላፊነትን መወጣት ላይ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ ምርጫው በቦርዱ ትከሻ ላይ እንደወደቀ አድርጎ መታሰብ እንደሌለበት ሊሠመርበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሠሩ ካሉት ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ቦርዱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ አንዱ ሲሆን፣ በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የነበረውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ያጋጠሙ ሁነቶችን የተመለከቱ ገለጻዎች በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ባልደረባ ቀርቧል።

የቀረቡትን ሪፖርቶች ተከትሎ መድረኩ ለተሣታፊዎች ክፍት የተደረገ ሲሆን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቦርዱ በጊዜ ሠሌዳው መሠረት እየከወነ ያላቸውን ተግባራት ላይ እንደየ ቅደም ተከተላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብና አስተያየት እየጠየቀ በማገናዘብ መሄዱን አበረታትው፤ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት አጋጠሙን ያሉትን ዕክሎች በዝርዝር አቅርበዋል።

በኹለት ዙር ለተሰበሰበው የተሣታፊዎች አስተያየት ዋና ሰብሳቢዋ መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ አጋጠመን ያሉትን እክሎች መግለጻቸው ለቦርዱ የሥራ ሂደትና ቦርዱ ያሉበትን ክፍተቶች በማወቅ በጊዜ መልሰ እየሰጡ ከመሄድ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ በመድረኩ ሊመለሱ የሚችሉትን ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ከዚሀ በፊት እንደተናገሩት ጥያቄዎች በመድረክ ብቻ ሊወሠኑ እንደማይገባ ገልጸው መሠል መድረኮች ምርጫው እንደመቅረቡ መጠን በአጭር የጊዜ ርቀትና በተከታታይ እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል።

በመተከል ዞን በሁሉም ወረዳዎች የምርጫ ጣቢያዎች መክፈቱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
የፀጥታ ችግር በነበረበት የቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ላይ በሁሉም ወረዳዎች የምርጫ ጣቢያ መክፈቱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በመተከል ዞን በሚገኙት ሰባት ወረዳዎች የምርጫ ጣቢያ መከፈቱን ያስታወቁት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ናቸው።
ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው ዋና ሰብሳቢዋ በመተከል የምርጫ ጣቢያዎች መከፈታቸውን የተናገሩት። በዚሁ ውይይት ላይም በስድስት ክልልሎች ላይ የእጩ ምዝገባ መጀመሩን ዋና ሰብሳቢ አስታውቀዋል ተናግረዋል።

የእጩ ምዝገባው ቀደም ብሎ የተጀመረባቸው ክልሎች አዲስ አበባ ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሲሆኑበተቀሩት ክልሎች ደግሞ ካሳለፍነው የካቲት 16/2013 ጀምሮ የእጩ ምዝገባ ሂደቱን ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለምርጫ 2013 ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አገራዊ ምርጫው ሰብአዊ መብቶች የተከበሩበት፣ ተዓማኒ እና ሰላማዊ የምርጫ ሂደት መሆኑን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሆኑ መሰረታዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲያስችል፣ ሁሉም የምርጫው ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት ቢያንስ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ለማክበር፣ ለመፈጸምና ለማስፈጸም በይፋ ቃል እንዲገቡና እና በገቡት ቃል መሰረት እንዲተገብሩት ለአዲስ ማለዳ በላከው በግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

1 ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች እርምጃዎች ቃል ኪዳን (Pledge for Concrete Human Rights Actions)
በምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች በሙሉ ምርጫውን ካሸነፉ ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር፣ ለማስከበር እና ለማሟላት የሚወስዷቸውን ተጨባጭ እርምጃዎች በምርጫ መወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው (ማኒፌስቶ) ውስጥ በግልጽ እንዲያስቀምጡ እና በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ሕዳጣንን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳወቁና ቃል እንዲገቡ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

2 ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት መቆም (Commitment for Human Rights)
በመንግስት ሥልጣን ላይ የሚገኙም ሆነ ሌሎች እጩዎች እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፣ በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ፣ በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደማይታገሱ በይፋ እንዲያስታውቁ፤ እንዲሁም በአባሎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የውስጥ አሰራር በመዘርጋት ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

3 ምርጫው ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ማረጋገጥ(Ensuring Gender-Responsiveness of the Election Process)
ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ስልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላትም የምርጫው ሂደቶች

በሙሉ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ
መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ቃል መግባት አለባቸው ተብሏል።

4 የሕግና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ቃል ኪዳን(Pledge for legal and policy reform)
በምርጫው ያሸነፉም ሆነ የተሸነፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሁሉም ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት፣ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮችን ለመፈተሽ እና በሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስፈላጊውን የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ በይፋ ቃል እንዲገቡ።

5 የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማረጋጥ (Protecting freedom of movement, association, expression, and access to information)
የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላት በተለይም የፀጥታ አካላት ተግባራቸውን በገለልተኝነት እና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት በመወጣት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎች እንዲሁም ሚዲያ እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችንም ጨምሮ ያለ ምንም ገደብ፣ ክልከላ፣ አድልዎ፣ አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ወይም የበቀል እርምጃ በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደራጀትና ሃሳባቸውን በነጻነትየመግለጽ እንዲችሉ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው በሙሉ መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

6 ከግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎችሙሉ በሙሉ መቆጠብ (Fully Refrain from Incitement, Hate Speech and Violence)
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሁሉም የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻ እና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮች እና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም አይነት የኃይል እርምጃ ፈጽሞ እንደሚቆጠቡ ቃል መግባት አንዳለባቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የምርጫ ግብዓት ማጓጓዣ ችግር ካልተፈታ የ2013 ምርጫ ሂደት ሊስተጓጎል አንደሚችል ምርጫ ቦርድ ገለጸ
የምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዣ ችግር አፋጣኝ እልባት ካላገኘ አገር አቀፉን የምርጫ ሂደት ሊያስተጓጉል ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ያሳወቀው በመራጮች ምዝገባ መረጃ፣ በምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተወያየበት ወቅት ነው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰፊ አገርና ህዝብ ነገር ግን የመንገድ መሰረት ልማት ውስንነት ያለበት አገር ላይ ምርጫን በአግባቡ ለማካሄድ መንግስት ከፍተኛ እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። ሁሉንም የአገሪቱ አካባቢ ሊሸፍን የሚችል የትራንስፖርት አቅም ያለው መከላከያ_ሰራዊት መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ በትግራይ በነበረው ሁኔታ በተፈጠረው ጫና እገዛው መስተጓጎሉን ተናግረዋል።

ያለው የማጓጓዣ ችግር አፋጣኝ እልባት ካልተሰጠው የምርጫ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተጓጉል ይችላል በማለት ተናግረዋል ሰብሳቢዋ። ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቷ 663 የምርጫ ክልሎችን ከፍቶ የምርጫ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ ሲሆን በቀጣይ ለ50 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚያሰራጭ አስታውቋል።

ማጓጓዣው በየአካባቢው እንዳለው መሰረተ ልማት በየብስ ፣ በጀልባ እንዲሁም በበቅሎና ፈረስ ጭምር ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከቱት። ለዚህም ደግሞ በየደረጃው ያሉ የክልል አመራሮች የመጓጓዣ ችግሩን ለመፍታት ከቦርዱ ጋር መተባበር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ኦብነግ “በገዢው ፓርቲ ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው” አለ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የሶማሌ ክልልን ከሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ “ብዙ ጥቃቶች እየተፈጸሙብኝ ነው” አለ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ50 በላይ የኦብነግ አባላት መታሰራቸውን አንድ የግንባሩ አመራር ተናግረዋል።
የኦብነግ የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አህመድ መሐመድ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ ዛሬ እንደገለጹት፤ በሶማሌ ክልል በዶሎ፣ ቸረር፣ ሸበሌ እና ቆራሔይ ዞኖች በሚገኙ የድርጅታቸው አባላት ላይ የእስራት እና ሌሎችም ጥቃቶች ደርሶባቸዋል። ከታሰሩት አባላቶቻቸው ውስጥ ለመጪው ምርጫ ግንባሩን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የተላኩ ልዑካን እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

“በዶሎ ዞን በዋርዴር የእኛ ቢሮ ተዘግቷል። ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የላክናቸው ሰዎች ደግሞ ከዞኑ ወደ ጅግጅጋ አምጥተዋቸው፤ ሰሞኑን ጅግጅጋ ታስረው ነው የነበሩት” ብለዋል። በቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር የተመራና ወደ ደገሐቡር የተጓዘ ልዑክም ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ መከልከሉንም አክለዋል።

አንድ ድርጅት “መንቀሳቀስም ሆነ ዕጩ ማዘጋጀት ካልቻለ”፤ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር የስራ አስፈጻሚ አባሉ ገልጸዋል። ኦብነግ በምርጫው ለመሳተፍም ሆነ ላለመሳተፍ ገና ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰም በንግግራቸው ጠቁመዋል።
“አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ እኛ ምርጫውን ለመሳተፍ መገምገም አለብን። ሜዳው ነጻ አይደለም” ያሉት አቶ አህመድ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ሂዱና [ምርጫ] ተወዳደሩ ማለት፤ ሂዱና ተጣሉ ማለት ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለአቶ አህመድ አቤቱታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለሙ ስሜ ምላሾችን ሰጥተዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com