90 በመቶ የሚሆኑት የከረሜላ ፋሪካዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደለም ተባለ

Views: 139

በአገራችን ከሚገኙ 182 የከረሜላ ፋብሪካዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ተጠቆመ።
በኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ አምራች ተቋማት ኢንስፔክተር ህሊና ተስፋዬ እንደተናገሩት በተለያየ ጊዜ ፋብሪካዎች ላይ ድንገት ፍተሻዎችን ሲያደርጉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ፋብሪካዎች ማግኘታቸውንም አክለው ተናግረዋል።
ካለው የጥራት ችግር መካከልም የመስሪያ ቦታ ንፅህና ጉድለት ፣ የማምረቻ አካባቢ የንፅህና ጉድለት ፣ የጥሬ እቃን ከመጋዘን ውጪ ማከማቸት እና ንፅህናቸውን ያልጠበቁ የከረሜላ መቀቀያ ፣ የሎሊፖፕ እንጨቶች አያያዝ ክፍተት እንዲሁም ንፅህናውን ያልጠበቀ ማቅለጫ በፍተሻ ላይ ካስተዋሏቸው ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እንደ ህሊና ገለፃ የምግቡ ጥራት ላይ ድርድር እንደማያደርጉ ነገር ግን ከጥሬ እቃዎች እና ማምረቻ ቦታዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ክፍተት ለመሸፈን የጊዜ ቀጠሮዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
በዚህም ከፍተኛ የሆነ የጤና ጉዳት ባያደርሱም ከጊዜ ብዛት ግን ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ ምንም ድርድር የሚደረግባቸው ጉዳዮች እንደማይኖሩ እና ማሟላት ያለባቸውን ያላሟሉ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃዎችን እንደሚወስዱም አክለው ተናግረዋል።
የእኛ አገር የከረሜላ እና ጣፋጭ ምግብ አምራች ድርጅቶች በምግብ ነክ ጉዳዮች ላይ ደረጃ ስናዘጋጅ ካየናቸው ደካማዎች ናቸው፣ በደረጃ ዝግጅት ላይ ምንም ተሳትፎ አያደርጉም፤ ሲሉም በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የግብርና እና ምግብ ደረጃ ዝግጅት ቡድን መሪ ህይወት ህብስቴ ተናግረዋል። በቴክኒክ ኮሚቴው ውስጥም ልሳተፍ ብሎ የቀረበም ጥያቄም የለም ሲሉ ተናገራል።

በሌላ ባለድርሻ አካላት ተወክሎ የሚሰራው እንጂ ጣፋጭ ምግብ አምራች ድርጅቶቹ ይመለከተናል አይሉም ማህበራትም ቢኖሩም በዛ በቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ የተዋቀሩ አይደሉም። በመሆኑም ደረጃ ሲዘጋጅ ተሳታፊ ቢሆኑ የበለጠ ምርታማ ይሆናሉ ብለዋል።
እኛ አገር ምርቶች ሲመረቱ በዘፈቀደ እንጂ ሳይንሱ ላይ ተንተርሰው እና ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው የሚያመርቱበት አጋጣሚ የለም ያሉት ህይወት የከረሜላ ፋብሪካዎችም ደረጃቸውን ያልጠበቁ እየሆኑ የሚመጡት በዚሁ ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ይህንንም ለማስቀረት የቁጥጥር ስራው ላይ ያለውን ከፍተኛ ክፍተት በመድፈን የተሻለ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ነጻ የአፍሪካ የንግድ ቀጠና አባል ሆናለች ይህን ተከትሎም ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ስለሚኖሩ እነዚህ ድርጅቶች ከገበያ ውጭ ይሆናሉ ስለሆነም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በሚያስቀምጠው ደረጃ ቢሰሩ እና ደረጃ የሌለውም የስራ ዘርፍ ካለ እንዲዘጋጅ መጠየቅ ይቻላሉ ብለዋል።

የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የግንዛቤ ማሳደግና የህግ ተፈፃሚነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሰለች ወዳጁ እንደተናገሩት አላሰራ ያላቸው የንግድ ውድድርና ሸማቾችና ጥበቃ ባለስልጣን አዋጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዋጁ ቁጥር 8 13 /2006 በወጣበት ወቅት የቁጥጥር ስራዎች በተገቢው መልኩ እየተሰራ ነበር ነገር ግን ከጊዜ በኋላ 2008 ጀምሮ ሌላ አዋጅ በመውጣቱ ምክንያት ስራችንን አስተጓጉሎብናል ምክንያቱም በፊት በነበረው አዋጅ እኛ የምናስተካክለው የነበረው የህብረተሰብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ወንጀል የሚሆኑ ጉዳዮች በሚሆኑበት ጊዜ ይህንን እንዲተገብር አዋጁ ወደሌላ አካል አስተላልፎታል ብለዋል።

ስለዚህም እንደዚህ አይነት ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቁጥጥር ስራን እንዳያሳልጥ እንከን እንደሆነበት እና በርካታ ህገወጦች ለመበራከት ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አምራች ድርጅች ላይ የምርት ጥራት ችግር በከፍተኛ መጠን አለ የመንግስት ተቆጣጣሪ ባለስልጣናትም ጋር የቁጥጥር መላላት ከፍተኛ ችግር እንደሆነ የተናገሩት የምግብ እና ምግብ ነክ ጉዳዮች ጥራት አማካሪ እንዲሁም ኤል ኤም ግሩፕ መሰራችና ስራ አስኪያጅ ሙሉጌታ ይመር በዋናነት ለዚህ ችግር መበራከት ምክንያት የሆነው የተቆጣጣሪ ድርጅቶች የክትትል እና ቁጥጥር ክፍተት እንደሆነም ተናግረዋል።
ምግብ ከጤና ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፤ አምራቾቹ የሚያነሱትን የስኳር እጥረት እንዲፈታላቸው ተናግረዋል።

የቁጥጥር ስራውን በተመለከተ ደግሞ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በትክክል መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com