የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሦስት የንግድ ማስታወቂያዎችን ማገዱን ገለጸ

Views: 258

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ኅብረተሰቡን ያሳስታሉ፣ የንግድ ዕቃዉን በአሳሳች መንገድ ገልጸዋል ያላቸውን ኹለት ለታክሲ አገልግሎት ድርጅቶችን እና የአንድ የታሸገ ውሃ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ማስታወቂያ ማገዱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ከንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ጋር የማይጣጣሙ የንግድ ዕቃዎች እና የአገልግሎት ማስታወቂያዎችን 48 ጊዜ በመከታተል እና ከአዋጁ ጋር የሚፃረሩ የንግድ ማስታወቂያዎች ሲኖሩ መቶ በመቶ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ተናግሯል፡፡

ይህ እርምጃ የተወሰደው ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ሲሆን፣በዚህም ሦስት የንግድ ማስታወቂያዎችን ሲያግድ በኹለቱ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የአቤቱታ ምርመራ እና ክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጌትነት አሸናፊ ገልጸዋል።
ከንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 19 ላይ በማንኛውም መንገድ የሚገለጽ የንግድ ማስታወቂያ በማንኛውም ሁኔታ አሳሳች እና ሀሰተኛ መሆን እንደሌለበት እንዲሁም የንግድ ዕቃውን በማይገልጽ መንገድ መሆን እንደሌለበት እንዲሁም የዕቃው አምራች ወይንም አገልግሎት አቅራቢ የሆነ አካል በግልጽ መነገር እንዳለበት በግልጽ እንደሚያስቀምጥ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በዚህ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ይህንን ተላልፈው የተገኙ ሦስት የንግድ ማስታወቂያዎች መካከል ኹለቱ ለታክሲ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን አምራቾችን ከገዥዎች ጋር ለማገናኘት ፍቃድ ያወጡ ሆነው ሳለ ከቀረጥ ነጻ እንደሚያስገቡ የሚገልጽ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን በማስነገራቸው እርማት እስኪያደርጉ ድረስ መታገዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ማስታወቂያቸው ከታገዱ የድርጅቶች መካከል አንዱ “ሄሎ ታክሲ” ሲሆን ሌላኛው ታክሲዬ የተባለ ድርጅት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ማለዳ “ሄሎ ታክሲ” ጋር በመደወል ለማጣራት ብትሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

ጌትነት ምርመራ እየተደረገባቸው ስለሚገኙ ኹለት ማስታወቂያዎች ሲገልጹ ማስታወቂያዎቹ በህትመት የመገናኛ ብዙሃን ላይ ማለትም በመጽሄት ላይ የወጡ የባህል ሕክምና ማስታወቂያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ማስታወቂያዎች ላይ በባሕል ሕክምና የሚድኑ በሽታዎች ከተዘረዘሩ በኋላ በተለይም የበለጠ ሊያድኗቸው የሚችሏቸውን በሽታዎች በአራት መጽሄቶች ላይ በማስተዋወቃቸው የንግድ ፈቃድ እንዳለቸው እና ግብር ከፋይ መሆናቸውን ጨምሮ የማስታወቂያዎቹን ትክክለኛነት ከብሮድካት ባለስልጣን እና ከመድኃኒት ቁጥጥር ጋር በመሆን እያጣራን ነው ብለዋል።

ባለሥልጣኑ የ2013 አዲስ ዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ በ14 የሴትና የወንድ ልብስና ጫማ መሸጫ፣ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና ፈርኒቸር መሸጫ የንግድ መደብሮች ስለዋጋ ቅናሽ የተለጠፉት የውጭ ማስታወቂያዎች ላይ ክትትል በማድረግ በ10 የንግድ መደብሮች የተለጠፉ የንግድ ማስታወቂያዎች ግልፀኝነት የጎደላቸው እና አሳሳች በመሆናቸው በአዋጁ አንቀፅ ሰባት እና ስምንት መሠረት ማስታወቂያዎቹን እንዲያስተካክሉ ከመደረጉም በላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለወደፊቱ እንዳይፈፅሙ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ የሚለጠፉ እና በቴሌቪዥን የሚነገሩ የበዓል ቅናሽ ማስታወቂያዎች ላይ የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች በማስታወቂያቸው ቅናሹ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ እና የብር መጠን ስለማይገልጹ ከሩቅ አገር መጥተው ሊገዙ ያሰቡ ደንበኞችን ስለሚያጉላሉ ግልጸኝነት የጎደላቸው ስለሚሆኑ ማስታወቂያዎቹ እንዳይነገሩ እና እንዲስተካከሉ ማስጠንቀቂያ ጭምር ሰጥተናል በማለት ተናግረዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com