የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለኤሌክትሪክ አውቶቢስ ደረጃ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ

Views: 153

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ለኤሌክትሪክ አውቶቢስ ደረጃ እያዘጋጀ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ እና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በጋራ የሚዘጋጁት የኤሌክትሪክ አውቶቢስ ደረጃ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አውቶቢስ ወደ ሥራ ለማስገባት የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ እያከናወነ ያለውን ቅድመ ሥራዎችን የሚያግዝም እንደሆነ ተነግሯል።

በከተማዋ የኤሌክትሪክ አውቶቢሶችን የሙከራ ትግበራ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑ እና የዝግጅቱ አካል የሆነው የደረጃ ዝግጅት ሥራ ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን ረቂቅ ደረጃው በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ አዲስ አበባ ትራንሰፖርት ቢሮ የደረጃ ዝግጅት ኃላፊ እሱአንዳለ ሽዋንዳይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የደረጃ ዝግጅቱ በመጀመሪያ ረቂቅ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ እና ኢትዮጵያ ወደ ፊት ከውጭ አገራት የምታስገባቸው ኤሌክትሪክ አውቶቢሶች ጥራትና ደረጃ ለመወሰን የሚዘጋጅ ደረጃ እንደሆነም ተገልጻል።
በተጨማሪም ረቂቅ ደረጃው በአገር ውስጥና ከአገር ወጭ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ አውቶቢሶችን ያማከለ ነው።

የኤሌክትሪክ አውቶቢስ ደረጃ ሲዘጋጅ በቀዳሚነት መሰረት የሚደርገው መሰረታዊ የኤሌክትሪክ አውቶቢሶች ሊኖራቸው የሚገባ ዝርዝር መግለጫና የጥራት ደረጃ መሆናቸው ተመላክቷል።
የኤሌክትሪክ አውቶቢስ በዋናነት አገልግሎት የሚሰጡት ለሕዝብ ትራንስፖርት በመሆኑ የደረጃ ዝግጅቱ በተለይ ለደህንነት ዋስትና የሚሆኑ የጥራት ልኬቶች በርካታ ባለድርሻዎችን እና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ባለሙዎችን በማካተት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተመላኳቷል።
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አውቶቢስ እንደመሆኑ ከሌሎች አገራት የልምድ ተሞክሮ እንደሚወሰድና ከዓለም አቀፉ ደረጃዎች ድርጅት አስፈላጊ የቴክኒክ መረጃዎች እንደሚወሰድም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ከትራንስፖርት ቢሮው ጋር በመተባበር መሰረታዊ የሆነ የደረጃ አዘገጃጀት ስርአትን በመከተል ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ደረጃውን እያዘጋጀ ይገኛል።

በደረጃ ዝግጅቱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት መካከል ትራንሰፖርት ሚኒስቴር፣ አንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት፣ ሸገር የከተማ አውቶቢስና ደርጅት፣ በአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ማምረት የጀመረው ሀይዎንዳይ ማራቶን ሞተርስ፣ እንዲሁም በዘርፉ በርካታ ልምድ ያካበቱ ባለሙዎች እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል።

ደረጃው የኤሌክትሪክ አውቶቢሱ ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ምን አይነት ቴክኒካዊ መስፈርቶች መኖር እንዳለባቸው የሚያካትት ሲሆን ደረጃውን ተጠቅሞ ወደ ትግበራ በመግባት ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ ለመረዳት እንደሚያስችል ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ባለ ኹለትናና ባለሦስት እግር ሞተር አልባ ተሸከርካሪዎች ደረጃ እያዘጋጀ መሆኑን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፣ በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ረቂቅ በኢትዮጵያ ያልነበረ እና ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ሞተር አልባ ተሸከርካሪዎችን ደረጃ ለመወሰን ያለመ እንደሆነ ይታወቃል።

በአሁኑ ጊዜ በብዙ የዓለም ከተሞች ለህዝብ ትራንስፖርት የሚውሉ አውቶቢሶች 25 በመቶ የካርበን ልቀት መጠን እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ ይህንም አብነት በማደረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዘርፍ በአለማችን 25 የሚሆኑ የተመረጡ ከተሞች በእስያ ላቲን አሜሪካና አፍሪካ ከተሞች የኤሌክትሪክ አውቶቢሶችን ተግባራዊ በማድረግ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ይገልፃል።

ለዚህም መነሻ የሚሆነው የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ከአካባቢና አየር ንብረት ጋር ግንኙነት ባላቸው ዘርፎች ላይ በማተኮሩ ነው።
አዲስ አበባ ለኤሌክትሪክ አውቶብስ ከተመረጡት 25 ከተሞች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ሰአት ተሸከርካሪ ቁጥሯ እየጨመረና ከተሸከርካሪዎችም የሚወጣው የካርበን ልቀት እየጨመረ አንደሚገኛል መረጃዎች ያመለክታሉ።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com