ከሦስት ዓመት በፊት 40/60 ኮንዶሚኒየም የደረሳቸው ሰዎች እስካሁን ቁልፍ እንዳልተረከቡ ተናገሩ

Views: 2096

የካቲት /2011 አርባ ስልሳ የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ የወጣላቸው የቤት ባለቤቶች የቤቶች ልማት ቤቶቹ የማጠናቀቂያ ስራው (finishing) አላለቀለትም በሚል እስካሁን ድረስ ቤቱን እንዳላስረከባቸው ነገር ግነ የባንክ ክፍያ በመክፈል ላይ መሆናቸው ከፍተኛ ጫና ላይ መውደቃቸውን ለአዲስ ማለዳ ያላቸውን ቅሬታ ተናገሩ።

ውል የተዋዋሉት ከኢትዬጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንደሆነ የተናገሩት የቤት ባለንብረቶች ከዚህ ቀደም ለባንኩ ይከፈል የነበረው የባንክ ወለድ ዘጠኝ ነጥብ አምስት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የሚከፈለውን የወለድ ምጣኔ ከፍ እንዲል በመደረጉ ይበልጥ ችግሩን እንዳወሳሰበባቸው ገልጸዋል። ባንኩ የወለድ ምጣኔውን 10 ነጥብ አምስት ማድረጉ ይታወሳል።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የአርባ ስልሳ ኮንዶሚኒየም ቤት እጣ የወጣላቸው መልካሙ የተባሉ የመንግሥት ሰራተኛ እንደተናገሩት ቤቱ እጣ ወጥቶ ከደረሰን በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቂያ ስራው አልቆ ቁልፍ እንደምንረከብ ተነግሮን የነበረ ቢሆንም ቀሪው ሥራ ተጠናቅቆ መረከብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ቤቱ ከደረሳቸው በኋላ የቅድመ ክፍያ 25 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በዛው አመት በጊዜው ከፍለው ማጠናቀቃቸውንም አክለው ጠቁመዋል።
ቅድመ ክፍያ ከፍለው ካጠናቀቁበት ጊዜ ጀምሮም በየወሩ ሦስት ሺህ ኹለት መቶ ብር በዘጠኝ ነጥብ አምስት ወለድ ምጣኔ ለባንክ ሲከፍሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢው አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወለድ ማሻሻያ ማድረጉ ችግሩን አወሳስቦብናል ብለዋል።
“ አሁን እየኖርኩ ያለሁት የኪራይ ቤት ነው በየወሩ አራት ሺሕ አምስት መቶ ብር የቤት ኪራይ እከፍላለሁ ለኮንዶሚኒየም ቤት ደግሞ ሦስት ሺሕ ኹለት መቶ ብር በየወሩ እከፍላለሁ በዚህም የማገኘውን ደሞዝ ከቤት ኪራይ ውጪ መሰረታዊ ፍላጎቴን ለማሟላት እየበቃኝ አይደለም።” ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም መንግስት የቤት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው እንደሆነ ተረድቶ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ እና በፍጥነት አጠናቆ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሌላኛው ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያሰሙት የኮንዶሚኒየም እጣ የወጣላቸው ግለሰብ እንደተናገሩት ለማልኖርበት ቤት በየወሩ ለባንክ የምንከፍለው የገንዘብ መጠን ባለው የኑሮ ጫና ላይ ተደምሮ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል ብለዋል።
የምናገኘውን ወርሃዊ ገቢ የልጆች ትምህርት ቤት ከፍለን ፣ ምግብ እንዲሁም የተለያዩ ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ቁሳቁሶች አሟልተን ለመኖር አልቻልንም ፤ ይህ አግባብነት የሌለው አሰራር ነው ቶሎ ሊስተካከልልን ይገባል፣ ኮንዶሚኒየም የሀብታሞች ሳይሆን በቤት እጦት የተቸገሩ ድሆች የሚኖሩበት ነው ይህ ጉዳይ መፍትሄ ይሻል ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢው እንደተናገሩት የቤት ባለቤቶች ኮሚቴ አዋቅረው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በመሄድ ጥያቄያቸውን በተደጋጋሚ እንዳቀረቡም ጭምር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፤በዚህም ጥያቄያቸውን ሊያቀርቡ ሲሄዱ በቅርብ እንደሚፈታ እና መፍትሄ እንደሚሰጠን ይነገረናል ነገር ግን በተግባር ምንም የተሰራ ነገር አላየንም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ተረፈ (ኢንጂነር) ያነጋገረች ሲሆን ከቤት ባለቤቶቹ ጋር በቀጣይ ሳምንት ኮሚቴዎቹን ለማግኘት እንደታቀደ ከመግለጽ ውጪ ለምን እስከ አሁን ማስረከብ እንዳልቻሉ ያሉት ነገር የለም ።
ይልቁንም ያልተጠናቀቁበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፣ ችግሩ ያለው የተወሰኑ ሳይቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በ 2011 እጣ በወጣባቸው 14ቱም ሳይቶች ወደ 18 ሺሕ አምስት መቶ አካባቢ ቤቶች ገደማ መሆናቸውንም ግን አስታውቀዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com