የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

Views: 139

የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔን ለመመስረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ተጠሪነቱ ለጤና ሚኒስቴር የሆነ እና ሁሉም የጤና ሙያ ማኅበራትን የሚያሣትፍ የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔን ለመመስረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በረቂቁ ላይ ውይይት መደረጉን በጤና ሚኒስትር የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አሰግድ ሳሙዔል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ ሲመሰረት የጤና ሙያ ማኅበራት ሚናቸው ምን እንደሆነ ከጤና ሚኒስትር ጋር እና ከሌሎች የጤና ሙያ ማኅበራት ጋር እንዴት እንደሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ሥነ-ምግባር እና ኀላፊነታቸው ምን መሆን እንዳለበት የጤና ሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ሊያሟላቸው ስለሚገቡ ነገሮች እንዲሁም የጤና ሙያ ትምህርት አሰጣጥን በተመለከተ እና ባጠቃላይ የጤናው ዘርፍ ላይ እንደሚሰራ አሰግድ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ ከዚህ በፊት እንደነበረ አሰግድ አስታውሰው ነገር ግን ጠንካራ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ስላልነበር መቀጠል አልቻለም ብለዋል። እየተዘጋጀ የሚገኘው ረቂቅ ጉባዔውን እንደገና ለመመስረት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ በአዋጅ መመስረቱ እና አዋጁ መኖሩ ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች አንዱ ለሚሠሩ ሥራዎች የተፈጻሚነት ወሰን ለማስፋት እንደሚረዳ አሰግድ ገልጸዋል። ጉባዔው በፌድራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ሥራዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ይሠራል ብለዋል። ከዚህ በፊት ተቋቁሞ መቀጠል ያልቻለው የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ ያልሠራቸው ሥራዎችን እንደሚሠራ አሳውቀዋል።

የጤና ሚኒስቴር እና የጤና ሙያ ማህበራት የዘርፉን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ በዚህ ሳምንት ውይይት አካሂደዋል። በዚህ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ የጤና ማኅበራቶች ፕሬዝዳንቶች ምክትል ፕሬዝዳንቶች እና ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በቀረበላቸው የዘርፉ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምና በጋራ የትብብር ሥራዎች ረቂቅ ማለትም የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ የመመስረቻ ረቂቅ አዋጅ ሰነድ ላይ ሀሳቦችና ጥያቄዎችን አንስተው ከጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና ከሚኒስቴር ዴኤታዋ አለምፀሐይ ጳውሎስ ጋር ውይይት አድርገዋል።
የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ በእናቶች ጤና በኤ. አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት እና ምርመራ እንዲሁም በቲቪ እና በሌሎች የጤና ዘርፎች ላይ ጤና ጣቢያዎች ጤና ኬላዎች እና ሆስፒታሎች ያስመዘገቡት የስድስት ወር እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ወይይቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤናው ሴክተር ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ያሳደረበት ዓመት ነው በማለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ሙያ ተማሪዎች ማኅበር (ኢጤሙተማ) ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ አበበ የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ መመስረቱ የጤና ሚኒስትርን ሥራ ያቀላል በማለት ገልጸዋል። አክለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ የሚሠራቸውን ሥራዎች እኛ አገር ላይ ጤና ሚኒስቴር ነው የሚሠራቸው ብለዋል።

እንደ ምሳሌም ሥራን የመፍጠር ፣ሐኪሞችን የመመደብ ፣በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ማካሄድ፣ ለሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የጤና ሥርዓተ ትምህርቶችን መቅረጽ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለዳኞች ሹመት እንደሚሰጠው ሁሉ የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔም ሐኪሞችን የመሾም ሥራ ይሠራል ብለዋል። የጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ እነዚህን ሥራዎች ካከናወነ የጤና ሚኒስቴር ሌሎች የአስተዳደር እና የቁጥጥር ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለዋል በማለት ገልጸዋል። ረቂቁ አሁን የሕግ አስተያየት ለማግኘት የሚያስችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com