“ሆቴሎች አገልግሎት ለመስጠት በመፍራታቸው ተቸግሬአለሁ” ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

Views: 185

“በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ለባልደራስ አገልግሎት ለመስጠት በመፍራታቸው በተለያዩ ጊዜያት ሊደረጉ የነበሩ የፓርቲው ውይይቶችን እና መግለጫዎችን ለማካሄድ ተቸግሬአለሁ” ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ፓርቲው ባሳለፍነው ኀሙስ፣ የካቲት 18/2013 ከጠዋት ሦስት ሰዓት ጀምሮ በሀርመኒ ሆቴል “የአዲስ አበባ የራስ ገዝ ጥያቄ“ አስመልክቶ በተጋባዥ እንግዶች ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅቶነበር። ይሁን እንጅ ሀርመኒ ሆቴል ባልደራስ ዝግጅቱን ለማካሄድ ፈቃድ ማግነቱን የሚረጋግጥ ደብዳቤ ተቀብሎ ከፈቀደ ብኋላ በዝግጅቱ ዋዜማ ምሽት በሆቴሉ ዝግጅት ማካሄድ እንደማይችል እንደ ተገለጸላቸው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ ሀርመኒ ሆቴል ባልደራስ ዝግጅቱን ማድረግ እንደሚችል ይሁንታውን ካሳወቀ በኋላ በዝግጅቱ ዋዜማ ያቀረበው ምክንያት “ቦታ የለኝም” የሚል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኃላፊው አክለውም ሀርመኒ ሆቴል ባልደራስ ዝግጅቱን ማካሄድ የሚችልበትን ፈቃድ ከሰላም ሚኒስቴር ማግኘቱን ተመልክቶ የፈቀደውን “ቦታ የለኝም” ያለበት ምክንያት በመንግሥት ተጽእኖ እንደሚሆን ፓርቲው ከዚህ ቀደም ካጋጠሙት ችግሮች በመነሳት መጠርጠሩን ጠቁመዋል።
ባልደራስ ሊያካሂደው የነበረውን ዝግጅት አስመልክቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አሳውቆ ፍቃድ ማግኘቱን የካቲት 17/2013 ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰላማዊ ስልፍና ስብስባ ክፍል ኃላፊ አበራ ካሳሁን የተፈረመ ደብዳቤ ተሰጥቶት ነበር።

ባልደራስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆቴሎች ለማድረግ ያቀዳቸው ውይይቶችና መግለጫዎች በተደጋጋሚ አንደተሰረዙበት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።
እንደ ማሳያነትም ባሳለፍነው ሳምንት እንኳን የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ የውጪ አገራት አምባሳደሮች ጋር በራዲሰን ብሉ ሆቴል በወቅታዊ ጉዳዬች ላይ በተወያየበት ጊዜ በብዙ ችግር ሆቴሉን እንዳስፈቀዱ ኃላፊው ተናግረዋል።

ፓርቲው በአዲስ አበባ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ እንቅፋቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከመንግሥት በኩል በሚመጡ ተጽእኖዎች መሆኑን የሚናገሩት በቃሉ(ዶ/ር) ባልደራስ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሚምን በፓርቲ ስለሆነ መንግሥት ይፈራዋል ብለዋል።
መንግሥት ባልደራስ የሚደርጋቸውን ውይይቶን በቀጥታም ይሁን በተዋዋሪ የሚስተጓጉለው ምናልባት ባልደራስ በአዲስ አበባ ተገዳዳሪ ፓርቲ በመሆኑ ነው ብለዋል በቃሉ። ይሁን እንጅ ባልደራስ መንግሥትን የሚገዳደረው በውይይትና በሀሳብ በማሽነፍ ነው ሲሉም አክለዋል።
የአንድ አገር ችግር የሚፈታው በውይይትና በውይይት ብቻ ነው የሚሉት በቃሉ ባልደራስ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን የሚዘጋጀው የአገርና የሕዝብ ችግሮችን ለመፍታት በመሆኑ መንግሥት የሚያደርሰውን ተጽእኖ ማስቀረት እንዳለበት አሳስበዋል።
የዲሞክራሲ ስርዓት እንገነባለን የሚል መንግሥት ወይም የፓርቲዎችን ውይይት የጠላ ሥርዓት የኢትዮጵያን ችግር አይፈታም ሲሉም በቃሉ ጠቁመዋል።

በመሆኑም መንግሥት ባልደራስ የሚደርጋቸውን ውይይቶች ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ አንዳልሆኑ በመገንዘብ ሆቴሎች ከስጋትና ከመንግሥት ተጽእኖ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት ያሉት በቃሉ ሆቴሎች አገልግሎት ሰጭ እንጅ የመንግሥት አካል ስላልሆኑ የባልደራስን ዝግጅት ለማስተናገድ የሚኖራቸውን ፍላጎት ክፍት እንዳደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ባልደራስ የአዲስ አበባ የራስ ገዝ ጥያቄ “ ለማድረግ አስቦ የተሰረዘበትን የውይይት መርሃ ግብር የተሻለ አማራጭ ካላገኘ በፓርቲው ቢሮ እንደሚያካሂድ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ወደ ፊትም በተለያዩ አጀንዳዎች ፓርቲዎ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሕዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል። ፓርቲው ከዚህ በፊት በኢንተር ኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል ሊያደርግ የነበረው ስብሰባም ስብሰባው በሚካሄድበት እለት አንዲስተጓጎል መደረጉንም አስታውሷል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com