ከነዳጅ የሚገኘው የትርፍ ህዳግ የተለያየ እንደሚሆን ተጠቆመ

Views: 230

ከተሞች ከነዳጅ ላይ የሚያገኙት የትርፍ ህዳግ በሚያገኙት የገበያ ብዛት ከከተማ ከተማ የተለያየ እንደሚሆን ማሰቡን የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
አሁን ያለው አንድ ዓይነት የሆነ የነዳጅ የትርፍ ህዳግ አወሳሰን ፍትሀዊ ባለመሆኑ ሕገወጥ የነዳጅ ዝውውርን ከማበርከት እንዲሁም ጥቁር ገበያን ከማስፋፋት አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አህመድ ቱሳ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በዚህም በርከት ያለ የኅብረተሰብ ክፍል የሚገኝበት ከተማ የነዳጅ ፍላጎት ከፍተኛ ስለሆነ ሽያጫቸውም በዛው መጠን ይጨምራል። ይህም የነዳጅ ማደያዎችንም ሆነ የነዳጅ አከፋፋዮች የሚያገኙት ትርፍ ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

በአንፃሩ ደግሞ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ትንንሽ የሚባሉት ከተሞች ላይ የነዳጅ ፍላጎታቸው አነስተኛ በመሆኑ የሚገኘው የትርፍ ህዳግ ዝቅተኛ ይሆናል፣ በዚህም ወደ ገጠር ከተሞች ነዳጅ ከማድረስ ይልቅ ከተሞች ላይ እንዲቀር ወይም በህገወጥ መልኩ ወደ ጎረቤት አገራት እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ተናግዋል።

ይህንንም ለማስቀረት አነስተኛ የነዳጅ ፍላጎት እና አነስተኛ ሽያጭ ባለባቸው ከተሞች የትርፍ ህዳጉን ከፍ የሚያደረግ እና እንደ አዲስ አበባ ባሉ በርካታ ሽያጭ የሚያከናውኑ ከተሞች ላይ ደግሞ የትርፍ ህዳጉ በአንፃሩ ትንሽ ሽያጭ ካለባቸው ከተሞች ያነሰ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ሰአትም የነዳጅ አከፋፋዮች ከአንድ ሊትር ነዳጅ 18 ሳንቲም እንዲሁም ነዳጅ ማደያዎች 23 ሳንቲም የትርፍ ህዳግ ያላቸው መሆኑ ይህም በተለይም አነስተኛ የነዳጅ ፍላጎት ላለባቸው አካባቢዎች አነስተኛ ትርፍ እንደሆነ ተገልÍል።

ከዚህም ጋር አያይዘው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ባለበት ልክ አለመጨመሩን እና መጨመር የነበረበት በአንድ ሊትር ነዳጅ ስምንት ብር መሆን እንዳለበት የተናገሩት አህመድ የጨመረው ግን መጨመር ከነበረበት 25 በመቶውን ብቻ ነው ብለዋል።
በቀጣይ አንድ አመት ውስጥም ነዳጅ ላይ የአምስት ብር ጭማሪ የሚደረግ መሆኑን እና ይህም የትርፍ ህዳጉን ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

የአገራችን ነዳጅ ዋጋ እንደ ሌሎች አገራት በከፍተኛ መጠን ነዳጅ ሲጨምር የማይጨምር ሲቀንስም የማይቀንስ ነው ይህም የሚሆነው ማህረሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዲሁም የአገራችንን ኢኮኖሚ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነና በዚህም 26 ቢሊየን ብር የሚሆን ኪሳራ ውሰጥ መግባቱን አክለው ተናግረዋል።

ይህንንም ለማስተካከል ምናልባትም በቀጣይ አመታት በአለም አቀፉ ገበያ የነዳጅ ሽያጭ ዋጋ ከቀነሰ የአገራችን ነዳጅ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ባለማድረግ ወይም ባለበት እንዲቆይ ተደርጎ ትርፍ ከተሰበሰበ ነው ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ለነዳጅ እጥረትም ሆነ ከነዳጅ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች ከፍተኛውን ሚና የሚወስደው ጥቁር ገበያ መበራከቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም የነዳጅ ጥቁር ገበያ ያለባቸው ቦታዎች የተለዩ ሲሆን ለአብነትም ሀዋሳ ፣ጅጅጋ፣ ሻሸመኔ እንዲሁም ጅማ ከተለዩት ቦታዎች መካከል መሆናቸው ተጠቁሟል፤ጥቁር ገበያው የጠበራከተው የጎረቤት አገራት የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያለው በመሆኑ እንዲሁም በቁጥጥር መላላት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ጅቡቲ አንድ ሊትር ናፍጣ 51 ብር ከ 42 ሳንቲም ሲሸጥ፣ ኢትዮጵያ 21 ብር ከ ሦስት ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አንድ ሊትር ቤንዚን ደግሞ ጅቡቲ 77 ብር ከ 40 ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን በተመሳሳይ በኬኒያ 38 ብር እየተሸጠ መሆኑ ነዳጅን ከአገር ውጪ በህገወጥ መንገድ እንዲሸጥ ገፊ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በገበያ ሀይል እንዲሁም የተደራጀ የቁጥጥር ስራውን በማሳለጥ በጥቁር ገበያ የሚሸጠውን የነዳጅ ንግድ እናጠፋዋለን ሲሉም ተናግዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሺሕ አንድ መቶ የሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች እንዳሉ ነገር ግን በርከት ያሉ ማደያዎች እንደማይሰሩ ለአብነትም ከ 10 ኩባንያዎች ውስጥ ካሉ ማደያዎች 114 የሚሆኑት በተለያየ ምክንያት ስራ አቋርጠው እንደሚገኙም ጠቁመዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com