ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ ኮሮናን ለመከላከል የሚውሉ እቃዎች የግማሽ ቢሊዮን ብር ግዥ ተፈጸመ

Views: 108

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በመጭው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለኮቪድ 19 መከላከያ የሚውል የማስክ የሳኒታይዘር እና የጓንት ግዥ ከ 47 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መፈጸሙን አስታወቀ።
ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚውሉትን ቁሳቁሶች ግዢ የተፈጸመው በውሱን ጨረታ አሰራር ሂደት መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሂደት ኀላፊ መልካሙ ደፋሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ታህሳስ 7/2013 በወጣው ውሱን ጨረታ የተጋበዙት ተጫራች ድርጅቶች ማስክ ለማቅረብ 10 እንዲሁም ሳኒታይዘር ለማቅረብ ደግሞ ሌሎች 10 ድርጀቶች ግብዣውን የተቀበሉ ሲሆን ጓንት ለማቅረብ ግን ምንም ድርጅት እንዳልቀረበ ገልጸዋል።
ከተጋበዙት ድርጅቶች መካከል ማስክ ለማቅረብ አራት ድርጅቶች ፈቃደኛ ሆነው ሲቀርቡ ሳኒታይዘር ለማቅረብ ደግሞ አምስት ድርጅቶች የጨረታ ሰነዱን ሞልተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ጨረታ ታህሳስ 22/2013 ሲከፈት ውሱን ጨረታ በመሆኑ በአንድ ቀን እንደተከፈተ ገልጸው በዝቅተኛ ዋጋ ጥራት ያለው እቃ ያቀረቡ አሸናፊዎች ለማስክ Silver Spark Apparel Ethiopia የተባለ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በስምንት ሚሊየን 119 ሺሕ 376 ብር ከ 50 ሳንቲም በማቅረብ ያሸነፈ ሲሆን ለሳኒታይዘር ደግሞ Trucare pharmaceuticals Importer የተሰኘ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በ15 ሚሊየን 682 ሺሕ 568 ብር እንዲሁም Sadan pharmaceuticals የተሰኘ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በ31 ሚሊየን 761 ሺሕ 160 ብር ከ 59 ሳንቲም በማቅፈብ አሸናፊ እንደሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ለቁሳቁሶቹ በድምሩ 47 ሚሊዮን 443 ሺሕ 728 ብር ከ59 ሳንቲም በማውጣት ተቋሙ ግዥውን መፈጸሙን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በግማሽ በጀት ዓመቱ 102 ነጥብ ስምንት ሚሊየን ብር ግዥ መፈጸሙን የስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል።
ከእነዚህም ውስጥ ለፌደራል የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች እና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠቀሙባቸው የደምብ ልብስ እና የጽህፈት መሳሪያዎች ግዥዎች በተጠቀሰው ብር መከወኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።

የስንዴ ግዥን በተመለከተ ለኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ፣ ለብሄራዊ አደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ ለግብርና ሚኒስቴር 80 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ሰማንያ ሺሕ ሜትክ ቶን ስንዴ ግዥ ለመፈጸም የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ ለሦስት አሸናፊ ድርጅቶች የአሸናፊነት ደብዳቤ የተሰጠ ቢሆንም ከአቅራቢዎቹ ጋር ውል በተፈጸመበት 900 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ አሸናፊዎች የውል ማስከበሪያ ለማስያዝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የውል ማቋረጫ ማጠንቀቂያ ተሰጥቶ የግዥ ሂደቱ እንዲቋረጥ መደረጉም በሪፖርቱ ተቀምጧል።

ተቋሙ የተለያዩ ያገለገሉ ንብረቶችን በመሸጥ ደግሞ 25 ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል። የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በግማሽ በጀት ዓመቱ ከፌድራል የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች እና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተከማቹ 72 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በሽያጭ በማስወገድ እንዲሁም የተለያዩ ያገለገሉ የመኪና እቃዎች እንዲሁም የአልሙኒየም ቁርጥራጭ እና ሌሎች ያገለገሉ እቃዎችን በመሸጥ የተጠቀሰውን ገቢ እንዳገኘ በሪፖርቱ ተመላክቷል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com