ቀለም ፋብሪካዎች የመሸጫ ዋጋ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል

Views: 175

በኢትዮጵያ በቀለም ምርት ላይ የተሰማሩ የቀለም ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቀለም የመሸጫ ዋጋ ከ20 በመቶ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ። አዲስ ማለዳ የቀለም መሸጫ ዋጋ መጨመሩን ለማረጋጋጥና የጨመረበትን ምክንያት ለማጣራት በኢትዮጵያ ውስጥ በቀለም ምርት የተሰማሩ አምራቾችን አነጋግራ የዋጋ ጭማሪው ቀለም ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ በመጨመሩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችላለች። በንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ እንዳሉት ቀድሞውንም እየጨመረ የነበረው የቀለም ዋጋ በቅርቡ በነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ተባብሷል ብለዋል።

ባለሙያው አንደሚሉት በአንድ ጋሎን እስከ 300 ብር ድረስ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል። በዚህም የተነሳ ቀድሞ 400 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ጋሎን ቀለም እስከ 700 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑንም ተመላክቷል። አዲስ ማለዳም በአዲስ አበባ በሚገኙት መሸጫዎች ያገኘችው መረጃ እንደሚሳየው የቀለም የመሸጫ ዋጋ ጭማሪው መኖሩን አረጋግጠዋል። አዲስ ማለዳ በስልክ ደውላ ለማረጋገጥ አንደቻለችው የዋጋ ጭማሪው በክልሎች በተለይም በሀዋሳ እና በደሴ የሚገኙ የቀለም መሸጫ መደብሮችም የዋጋ ጭማሪ መደረጉን አረጋግጠዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው ሌላኛው የቀለም ፋብሪካ ብራይት የቀለም ፋብሪካ ሲሆን የጥሬ እቃ መግዣ መጨመሩ በመሸጫ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲኖር አድርጎታል ሲሉ የብራይት ቀለም ፋብሪካ የምርትና ቴክኒክ ኃላፊ አብርሃም ብርሃኔ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አብርሃም አንደሚሉት በቀለም ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንድጋነን ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የመጀሪያው የቀለም ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ በአብዛኛው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው ብለዋል። በኹለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጡት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መጨመር ሲሆን፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ግን ዋነኛ ምክንያት እንደማይሆን እና ጭማሪውን ለማባባስ ግን አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

የቀለም ፋብሪካዎች የሚጠቀሟቸው ግብዓቶች የአገር ውስጥ የሚመረቱት ጥሬ እቃዎች ጭምር ከ20 በመቶ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ማድረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት አብርሃም አምራቾች ተጽኖውን መቋቋም ሲያቅታቸው የመጣ ጭማሪ ነው ብለውታል።
የጥሬ እቃ መግዣ ዋጋ መጨመሩ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በተለይ በትንንሽ ፋብሪካዎች ላይ ተጽኖው የከፋ ነው ብለዋል አብርሃም። ድርጅታቸውም ትርፍ ሳይሆን በገበያው ላይ ለመቆየት ተጽኖውን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አብርሃም ተናግረዋል።
በቀለም አምራቾች ላይ የሚያሳርፈው ተጽእኖ ከጥሬ እቃ መወደድና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተጨማሪ በኮቪድ-19 የግንባታ ሥራዎች ተቋርጠው በመቆየታቸው ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደ ከተታቸው አብርሃም አስታውሰዋል። በወቅቱ ገበያ በሌለበት ሁኔታ ለሰራተኞች ደሞዝ እየከፈሉ የቆዩ አምራቾች ኪሳራ ውስጥ እንደገቡን ተጠቁሟል።

የቀለም አምራች ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያስከተለው የቀለም መሸጫ ዋጋ ጭማሪ ተጎጂ የሚያደርገው በብዛት ተጠቃሚዎችን መሆኑን አብርሃም አመላክተዋል። አንዳንድ የቀለም ፋብሪካዎች የጥሬ እቃ መግዣ ዋጋ የተጋነነ ጭማሪ በማሳየቱ የምርት መጠናቸውን መለቀነስ መገደዳቸውንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com