ካራማራ ከዓድዋ ድል ማግስት

Views: 155

የካራማራ ጦርነት ከአድዋ በኋላ በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ እንዳትደፈር ታላቅ ጀግንነት የታየበት እና እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበት ጦርነት ነው። ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሀምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ባለው ጊዜ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት አካሂደዋል፡፡ በግምት ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ የምስራቅ ጦር ግንባሮች ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሰውተዋል። ይህን ያክል መስዋእትነት የተከፈለበትን የካራማራ ድል በዓል በመንግስት ደረጃ ብሔራዊ ቀን ሆኖ እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባ ዳዊት አስታጥቄ ባለሙያዎችን እና የታሪክ መጻህፍትን አጣቅሶ የማለዳ ዘ ሐተታ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

የካቲት 26/1970 በወራሪው የሶማሊያ ጦር ላይ ድል የተቀዳጀችበት 43ኛ ዓመት ተዘክሯል።የካራማራው ድል ከአድዋ ጦርነት በኋላ ከወራሪው የሶማሊያ ሰራዊት ጋር የተደረገ ታላቅ ጦርነት ነው። በከፍተኛ ወታደራዊ ብቃትና ጀግንነት መስዋእትነት የተገኘ ድል በመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ በከፍተኛ ሥነሥርዓት ሊከበር እንደሚገባ ይታመናል።

በግምት ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ የምስራቅ ጦር ግንባሮች ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሰውተዋል። ብዙ ሺዎች በጦርነቱ ቆስለዋል።ሶማሊያ በየቦታው ያገኘቻቸውን ዜጎች ሴት ወንድ አዛውንት ወደ 20 ሺ የሚገመቱ ከአቅም በላይ በሆነ ውጊያ እጃቸው የገቡ የኢትዮጵያ ወታደሮችንም ጭምር በምርኮኛነት ወስዳ 11 ዓመት በእስር ቤት አስራለች። በጦርነቱ ላይ እያለ ጀቱ ተመቶበት የተማረከው ጀግናው ብርጋድየር ጀነራል ለገሰ ተፈራና ሌሎችም ነበሩበት።

ይሄ ጦርነት ከአድዋ በኋላ በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ እንዳትደፈር ታላቅ ጀግንነት የታየበት እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበት ጦርነት ነው። መንግስት ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። አሁንም ቢሆን የተለወጠ ነገር የለም። የካራማራ ድል በዓል በመንግስት ደረጃ ብሔራዊ ቀን ሆኖ እንዲከበር የተወካዮች ምክር ቤት ትኩረት ሰጥቶ፣የታሪክ ምሁራንም ተወያይተውበት ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚገባ የታሪክ ባለሙያዎች እና የቀድም ጦር ሰራዊት አባላት በተለያዩ መድረኮች ያነሳሉ።

ለመግቢያ ያህል ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሀምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ባለው ጊዜ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት አካሂደዋል። የጦርነቱ መከሰት የኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪቃ ቀንድን ጂኦ-ፖለቲካ ከስረ መሰረቱ ቀይሮታል። ይሁንና በሁለቱም ወገን ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የዚያ ታላቅ ጦርነት ታሪክ በአግባቡ ተመዝግቧል የሚል እምነት የለም። በወጉም መዘከርም እንኳን አልቻልንም ።

ቅድመ-ታሪክ
የእንግሊዝ ሶማሊላንድ የምትባለው ግዛት በ1952 ነጻነቷን ተቀዳጀች። ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ የ“ኢጣሊያ ሶማሊያ” የምትባለው ምድር ነጻ ሆነች። በወቅቱ “የተበታተኑትን የሶማሊ ግዛቶች አንድ ላይ ሰብስቦ ታላቋ ሶማሊያን መፍጠር” ህልም ያነገቡት የሶማሊያ ፖለቲከኞች ሁለቱ የሶማሊ ግዛቶች ከስድስት ወራት በኋላ በመቀላቀል “የሶማሊ ሪፐብሊክ”ን መሰረቱ ፣እያንዳንዱ የሶማሊ መሬት በአዲሲቷ ሶማሊያ ስር መግባት አለበት የሚል አቋም ያዙ።
በመሆኑም “ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የያዙትን መሬቶቻችንን እንፈልጋለን” የሚል ሰበካ ጀመሩ። በዚያ ወቅት ጅቡቲና ኬኒያ ነጻነታቸውን አልተጎናጸፉም፡

ከአንድ ዓመት በኋላም አነስተኛ የሰርጎ ገብ ሃይል በማደራጀት በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን ቆላማውን የኦጋዴንን ክልል ለመውረር ሞከሩ። ነገር ግን በጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የሚመራው ሶስተኛ ክፍለ ጦር በአስር ቀናት ውስጥ ሶማሊዎቹን አባረራቸው። ከዚያ በኋላ ሶማሊዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አፋፋሙ።

በ1957 ደግሞ ሶማሊያ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀች። ይሁንና ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ሳይቆይ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
ጄኔራል ሙሐመድ ዚያድ ባሬ ጥቅምት 1962 በመንፈቅለ መንግሥት ስልጣን ሲይዙ ደግሞ ሁሉም ነገር ከመሰረቱ ተቀየረ። “ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የምትፈልገው ኦጋዴንን ብቻ አይደለም” ተባለ። “በኢትዮጵያ የተወሰደብን መሬት የሀረርጌ፣ ባሌ እና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራትን የሚያጠቃልል ነው” የሚል አዋጅ ታወጀ።

ይህ ብቻ አይደለም። ይህ የትልቋ ሶማሊያ ህልም የዋቤና የገናሌ ወንዞች መነሻ የሆኑትን የአርሲ፣ የባሌና የሀረርጌ ተራሮችን በመቆጣጠር ለሶማሊያ በተለይም ለመቀደሾ የመጠጥና የመስኖ ውሃ አቅርቦትን አስተማማኝ ማድረግ ነው። ግብፀ የኣባይ ተፈሰስን ለመቆጠጠር የምታደርገው አይነት ህልም መሆኑ ነው።

ይህ ሰፊ ግዛት በጥቅሉ “ሶማሊ ገልቤድ” (ምዕራብ ሶማሊያ) ተብሎ ተሰየመ። “በውስጡ የሚኖሩት ሶማሊ ያልሆኑ ህዝቦችም ከጊዜ ብዛት ቋንቋቸው ቢቀየርም ጥንተ ማንነታቸው ሶማሊ ነው” ተብሎ ተነገረ።
ከዚህ በተጨማሪም በባሌና በሲዳሞ ክፍለ ሀገራት የሚደረገውን ውጊያ የሚያስተባብር “የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር” (ሶ.አ.ነ.ግ) የተባለ ድርጅት ተመሰረተ። በጥቅሉ የሶማሊያ መንግሥት “ከአዋሽ ወንዝ በታች ያለው መሬት በሙሉ የኔ ነው” የሚል አቋም ማራመድ ጀመረ።

የሶማሊያ መንግሥት የሶሻሊዝም ተከታይ መሆኑን በይፋ በማወጁ ከሶቪየት ህብረት ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት ተፈራራመ። በስምምነቱ መሰረት ከሶቪየት ህብረት አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ አገኘ።
ለሰባት ዓመታት ያህልም ሰራዊቱን ሲያሰለጥንና ሲያደራጅ ሰነበተ። በውጤቱም የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ከ70 የማያንሱ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን የታጠቀ አየር ሀይል እና አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮችን ያቀፈ ግዙፍ የጦር ሰራዊት ባለቤት ለመሆን ቻለች። እንግዲህ የሶማሊያ መንግሥት ይህንን ሁሉ ካደረገ በኋላ ነው በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸመው።

የሶማሊያ መንግሥት ወረራውን በቀጥታ አልጀመረም። የምዕራብ ሶማሊ ነጻ አውጪ ግንባር/Western Somali Liberation Front (ም.ሶ.ነ.ግ- WSLF) እና የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር/ Somali Abo Liberation Front (ሶ.አ.ነ.ግ- SALF) አሸማቂዎችን በማስቀደም ፣በመጋቢት ወር 1968 ከሀርጌሳ መስመር እየተነሱ በኦጋዴንና በደጋማው የሀረርጌ ክፍል እንዲሁም በባሌ ክፍለ አገር ወደ ውስጥ እየሰረጉ እስከ ጊኒር እና ጎሮ አውራጃዎች እንዲገቡ ተደረገ።እነዚህ ሀይሎች ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት የደርግ መንግሥት ከኢህአፓ ፣ጀከብሃና ሻዕቢያ ወጥረው ይዘውት ነበር። ኢዲዩ የተባለው ድርጅት እንዲሁ ሌላኛው ፈተና ነበር።

የይፋ ወረራ
ሀምሌ 15/1969፣ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የታላቋ ሶማሊያ ምስረታ እውነት ለማድረግ ለዓመታት ሲያደራጁት የነበረው ሰራዊት በሙሉ ሀይሉ ማጥቃት እንዲጀምር ትዕዛዝ ሰጡ። ጥቃቱን በሁለት መስመሮች ማለትም በኦጋዴን በዶሎ አዶ መስመር ከፈተ።
በኦጋዴን መስመር የፌርፌር ከተማ ትይዩ ካለችው የበለድወይን ከተማ ነው የተነሳው። የመጨረሻ ግቡ ደግሞ መላውን የኦጋዴን ቆላማ አውራጃዎች መቆጣጠር ነው።
የዶሎ ኦዶ መስመር የተሰለፈው ጦር ከሶማሊያዋ የባይዶዋ ከተማ ተነስቶ ነው። ዶሎ ኦዶ ከምትባለው የድንበር ከተማ ከደረሰ በኋላም በሁለት በመከፈል ወደ ባሌና ሲዳሞ ክፍለ አገራት ዘምቶ የመጨረሻው ግቡን የባሌ ጎባ እና ነጌሌ ቦረና ከተሞችን ከነጌሌ ቦረና ከተማ 40 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ደረሶ ነበር።

የሶማሊያ ሀይሎች ኦጋዴንን በድብቅ በወረሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ፖለቲካ ተቀስፋ ተይዛ ነበር። አገሪቱን የሚመራው የደርግ መንግሥትም በኮሎኔል መንግሥቱ ቡድን እና በነሻምበል ዓለማየሁ ሀይሌ ቡድን ለሁለት ተከፍሎ ነበር። ሁለቱ ሀይሎች ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ በመሆናቸው የሀገሪቱን ድንበር የማስጠበቁን ጉዳይ እምብዛም አላተኮሩበትም።

በጥር 25/1969 ግን ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በእነ ሻምበል አለማየሁ ሀይሌ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ ወሰዱ። “አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል” ተባለ። ይህም ቀይ ሽብርን ወለደ። በኢህአፓ ላይ የሚደረገው የመደምሰስ እርምጃ በይፋ ተጀመረ። አንድ ወር ሙሉ ሽብሩ በከተሞች ተጧጧፈ። የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለሶማሊያ ጉዳይ ሙሉ ትኩረት መስጠት የጀመረው በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነው።
በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም አቤቱታቸውን በድንገት ወደ አዲስ አበባ ለመጡት የኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ አሰሙ። ፕሬዚዳንት ካስትሮም ሊቀመንበር መንግሥቱንና ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን የደቡብ የመን ዋና ከተማ በሆነችው አደን ላይ ሰበሰቧቸው።

በኤደን የተደረገው ውይይት ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ለመጪው ውጊያ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በመሆኑም “ስጋ ሜዳ” በሚባለው ቦታ የሚገኘውና የቀድሞ የድኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት ወላጅ አልባ ህጻናትንና ረዳት የሌላቸውን አረጋዊያን የሚንከባከብት ማዕከል ተወስዶ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ እንዲሆን ተወሰነ። ማሰልጠኛውም “ታጠቅ” በሚል ስያሜ ተጠራ።

የጦርና የሲቪል ከፍተኛ ካድሬዎች ለስልጠና በደብረ ብርሃን የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲከቱ ታዘዙ። ጡረታ ለወጡ ወታደሮች የሰርኩላር ጥሪ ተላለፈ። በየክፍለ ሀገሩ እጩ ሚሊሻዎች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ተሰጠ። ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ሚያዚያ 4/1969 በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩን እንዲያድን የሚያሳስበውን ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ አደረጉ።

ጥሪውን የሰማው የአዲስ አበባ ህዝብም ድጋፉን ሚያዚያ 6/1969 በአብዮት አደባባይ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ገለጸላቸው። በክፍለ ሀገር ከተሞችም የድጋፍ ሰልፎች ተደረጉ። በቀበሌ ደረጃ በተዋቀሩ የእናት ሀገር ጥሪ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነትም ለሰራዊቱ ስንቅ የሚሆኑ ደረቅ የምግብ ዓይነቶችን (በሶ፣ ቆሎ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ብስኩት ወዘተ..) ማዘጋጀት ተጀመረ። እንደ ኩባያ፤ ሳህን፤ ማንኪያ፤ ድስት ወዘተ.. የመሳሰሉ ቁሳቁሶችም የማብሰያና የመሰብሰቢያ እቃዎችም ከህዝቡ ተሰበሰቡ። ኢትዮጵያ የስልጠና ዝግጅቷን ካጧጧፈች በኋላ ሰኔ 19/1969 ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ አሳየች።
ይህ መዝሙር እየዘመረ ወደ ምስራቅና ኢትዮጵያ ዘመተ …
ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ
ረጅሙን ጉዞ ጥንቱን አውቄ
ተነስቻለው ትጥቄን አጥብቄ
መብት ነፃነት እስኪሆን አቻ
ተነስቻለው ለድል ዘመቻ
ልሙት ልሰዋ ደስ ብሎኝ ስቄ
ለሀገሬ ክብር እኔ ወድቄ …
ሀገሬ
መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ…

የካራማራ የድል ቀን; የሚገባውን ያህል ያልተዘመረለት ትልቅ የታሪካችን አካል ነው። ድሉን ልዮ የሚያደርገው ከአድዋ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በዘር; በሀይማኖት እና በጎሳ ሳይከፋፈሉ ከሰሯቸው ተጠቃሽ የታሪክ አጋጣሚዎች አንዱና በመሆኑም ነው።
ድሉ ላለፉት ሰላሳ አመታት በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና በቀድሞው ሰራዊት እንጂ በመንግስታት ዘንድ በጥቂቱ እንኳን ትኩረት ተሰጥቶት አያውቅም።

ከዚህ ጎን ለጎን በመገናኛ ብዙሃን የሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ተፋፍሞ ቀጠለ። የወታደራዊ ሰልፉም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ ዓላማ በሶማሊያ ላይ የስነ- ልቦና ሽብር መፍጠር ነበር። ነገር ግን ሶማሊዎች ለኢትዮጵያ የስነ-ልቦና ጦርነት ተበግረው ወረራውን ከመፈጸም አልተቆጠቡም። የዚህም ምክንያቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሰው ብዛት እንጂ ለውጊያ የሚረዱ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያልታጠቀ መሆኑን የሚያውቁ መሆናቸው ነው።

በወቅቱ የነበረው የኃይል ሚዛን
ሶማሊያ ወረራውን በጀመረችበት ወቅት በሁለቱ ሀገሮች የጦር ሰራዊቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነው የነበረው። ለምሳሌ የሶማሊያ የምድር ጦሩ አወቃቀር ይህንን ይመስል ነበር።
ሶማሊያ 8 እግረኛ ክፍለ ጦር ሲኖራት ፣ኢትዮጵያ አራት ክፍለ ጦር ብቻ ነበራት። ኮማንዶ ብርጌድም እና ሜካናየዝድ ሶማሊያ 4 የነበራት ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ምንም አልነበራትም። ታንከኛ ብርጌድ እና መድፈኛ ብርጌድ ሶማሊያ 4 ሲኖራት ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት፣ ሶማሊያ የታጠቀችው የከባድ መሳሪያ ዓይነትና ብዛትም የሚከተለው ነው። ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች 253 ፣ኢትዮጵያ 51 ነበራት ። ታንኮች ሶማሊያ 608 ፣ኢትዮጵያ 132 ፣ መድፎች ሶማሊያ 260 ኢትዮጵያ 48 ፣ ቢ.ኤም ሮኬቶች ሶማሊያ 125 ኢትዮጵያ አንድ፣ አየር መቃወሚያ ሚሳኤሎች ሶማሊያ 75 ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም።

ተዋጊ አውሮፕላኖች ሶማሊያ 65 ኢትዮጵያ 8 ብቻ ነው የነበራት። ኢትዮጵያ ያኔ የታጠቀችው አሜሪካ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የሰራቻቸውን T-2 ታንኮችን ናቸው። የሰራዊቱ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችም “ካርባይን” እና “ኤ.ም. ዋን” የሚባሉ አሮጌ ጠመንጃዎች ነበሩ። በመሆኑም የሶማሊያ ሰራዊት በመሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም ብልጫ ነበረው።

የኢትዮጵያ ሰራዊትን ለማስታጠቅ የገጠሙ ፈተናዎች
ሊቀመንበር መንግሥቱ በየመን ከተደረገው ውይይት በኋላ ለመሳሪያ ጥየቃ ወደ ሶቪየት ህብረት ተጓዙ። ሆኖም የክሬምሊን መንግሥት በቀላሉ ፊት አልሰጣቸውም። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው ምክንያት ሶቪየት ህብረት ከሶሻሊስቷ ሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት የነበራት መሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሶቪየቶች በኢትዮጵያ በመካሄድ በነበረው ለውጥ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው መሆኑ ነው።
በ1968 መጨረሻ ሊቀመንበር መንግሥቱ ቻይና በሚሥጥር ጎብኝተው ሲያመሩ ግን ያላሰቡት እድል ገጠማቸው። ቻይናም ለሁለት ክፍለ ጦር የሚበቃ ቀላል መሳሪያ በእርዳታ መልክ እንደሰጠች ጓድ ፍቅረሥላሴ አብዮቱ እና ትዝታዬ በሚለው መጽሃፋቸው ላይ አስፍለዋል።

እንደ ቻይና ሁሉ ከሶቪየት መሪዎች ጋር የማይጣጣሙት የዩጎዝላቪያው መሪ ጆሲፍ ብሮዝ ቲቶም የኢትዮጵያ አርበኞች ከዩጉዝላቪያ ጓዶች ጋር የነበራቸውን የጋራ የትግል ወኔ በማስታወስ 70 አሜሪካ ሰራሽ ታንኮችንና እጅግ በርካታ ቀላል መሳሪያዎችን ከበቂ ጥይቶች ጋር አበረከቱ።

የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት የዓለም አቀፍ ሀይሎች አሰላለፍ መቀየር
በ1967 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤን ከስልጣን ያወረደው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በታህሳስ ወር 1967 ኢትዮጵያ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ስርዓት ተከታይ ሀገር መሆኗን ቢያውጅም የሶቪየቶችን ሙሉ ይሁንታ ለማግኘት ቸግሮት ቆይቷል።
የሶቪየት ሀይሎች ከሶማሊያ መባረራቸው ለኢትዮጵያ ሰርግና ምላሽ ነው የሆነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ የጦር ሀይል ለመጀመሪያ ጊዜ ሶቪየት ሰራሽ T-34 ታንኮችን፣ መድፎችን ቢ.ኤም ሮኬቶችን የሚታጠቅበት ሁኔታ ተመቻችቶለታል። አሮጌ የነፍስ ወከፍ መሳሪያቹ በክላሽኒኮቭ (AK-47) እና ኤስ.ኤስ. እንደሚተኩም ቃል ተገብቶለታል። የግርኖቭ መትረየሶችና ላውንቸሮችም ከሶቪየት ህብረት እንደሚመጡ ተነግሯል። የአየር ሀይሉም የሚግ ጄቶችና ለወታደራዊ አቪየሽን የሚያገለግሉ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን ሊታጠቅ ተዘጋጅቷል።

ከሶቪየትና የሌሎች ሶሻሊስት አገራት መሳሪያዎቹን ቢመጡም ስለ አጠቃቀማቸው ማወቁ ፣መደበኛ ሰራዊቱም ሆነ የአየር ሀይል ከፍተኛ የውጊያ ስልጠና ያስፈልገው ነበር። የውጊያ ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላም ከሶቪየት ሰራሽ መሳሪያዎች ጋር እስኪተዋወቅ ድረስ በቂ ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል። በተለይ የከባድ መሳሪያ ተኳሾችንና የአውሮፕላን አብራሪዎችን በአጭር ጊዜ ለውጤት ማብቃት አይቻልም።

ወረራውን የመከላከል ሂደቱ እንዴት ነበር?
ነሐሴ 28/1969 በሶማሊያ ላይ ከፍተኛ ውጊያ አደረግን። በጣም ከባድ ውጊያ። ክረምት ነው። የሶማሊያ ታንኮች ማሽላ ውስጥ ሁሉ ገብተው ነበር። የአየር ኃይል ተዋጊ ጀቶቻችን እየተምዘገዘጉ እየተወነጨፉ እየተመላለሱ ወቁት በማለት ያስታውሳሉ።
በካራማራው ጦርነት የኢትዮጵያን ሰራዊት ተጋድሎ ሜ/ጀነራል መርዳሳ በሁለት ቦታ የተከፈለ ነው በማለት ያስታውሳሉ። አንደኛ በፕሮፓጋንዳ ሌላኛው በተግባር የተመሰከረለት ውጊያ በማድረግ ሲሉ ይገልጻሉ። በፕሮፓጋንዳ ጦሩ እንዳይዋጋ ሲያደርጉ የነበሩ ቡድኖች ተፈጥረው ነበር። የአዛዦች አመራር ተግባራዊ እንዳይሆን ጦሩ ድል እንዳያደርግ ተቃራኒ ስራ ሲሰሩ የነበሩ እንደነበሩ ያነሳሉ።

በሌላ በኩል 11ኛ ብርጌድ ደገሀቡር ላይ በአዛዡ ብ/ጀነራል እሸቱ መኮንን አማካኝነት፣ ጅግጅጋ ላይ ደግሞ በጣም የተማረም ስለሆነ ፣10ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ በአዛዡ ኃይሌ ተስፋ ሚካኤል እንዲሁም ፣የሶስተኛ ታንከኛ ሻለቃ አዛዥ ደግሞ ጠና ጋሻው፣ በእነ ብ/ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ፣ እና በእስራኤል የሰለጠኑት ሜካናይዝድ የሚባሉት በሙሉ በጣም ተዋግተዋል። ሰራዊታችን ለትውልድ የሚያኮራ ወገንንና አገርን ያስከበረ ታላቅ ተጋድሎ አድርጓል።
በዚያን ግዜ የነበረውን የሠራዊቱ አገራዊ መንፈስ ሜ/ጀነራል መርዳሳ ሲገልጹ፣ ሁሉም ሰው በጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ እንደ ወታደር ለሀገራችን ዳር ድንበር መከበር በየተመደብንበት ቦታ በሀገር ፍቅርና መስዋእትነት የጀግንነት ስሜትና መንፈስ ከመስራት ውጭ እከሌ ከዚህ ዘር እከሌ ከዛ የሚል ነገር ስላልነበረ እንደሆነ ያነሳሉ። አዲስ ስለ ካራ ማራ መሬት ሲያወሩም፣ ካራ ማራ እኮ ዐሥር ዓመት ብቻውን ያዋጋል። በጣም ስትራቴጂክ መሬት ነው። ካራማራ ላይ የተጠመደው ራዳር፣ ገና ከሀርጌሳ አውሮፕላን ስትነሳ የሚቆጣጠር ነው። ካራማራ ምንግዜም ለወታደራዊ ስራ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሚባል መሬት ነው። ወደላይ ያደገና በጣም ረዥም በጣም ሰፊ ተራራ ነው። አንድ መንገድ ብቻ ናት የምታሳልፈው በማለት ጀነራሉ ያስታውሳሉ። ካራማራ በመስከረም ሁለት ተለቀቀ። ከ 5 ወራት ውጊያ በኋላ ካራማራን የካቲት 26 ረፋዱ ላይ ነው 1970 ነው።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ግዛታችንን ጥሳ በገባችበት ግዜ ያደረገውን እጅግ ከፍተኛ ተጋድሎ በመዘከር ብሔራዊ በአል ሆኖ እንዲከበር ለማሳሰብና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ እንዳለ ይነገራል።

ያልጠፋው የባሬ ህልም
የኢትዮጵያ ህዝብና መከላከያ ሰራዊት (እንደ ኩባ በመሰሉ ወዳጅ አገሮች በመታገዝ) ወራሪውን የሱማሌ ኃይል ዳግማኛ እንዳይነሳ አደርጎ ድባቅ ቢመታውም፣ የሰይድ ባሬ ህልምን ከአዋሽ ማዶ ያሉትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን ወርሮ ትልቋን ሱማሌ የመመስረት ህልም ግን አሁንም አልሞተም፣ ጥስሱም አልተደፋም። እንደማሳያነት Union of Islamic courts ይባል የነበረው ቡድን አላማ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ልክ ሰይድ ባሬ ኢትዮጵያ በ1974 አብዮትና አብዮቱን ተከትሎ በተከሰተው የነጭና የቀይ ሽብር መዳከሟን በመየት የግዛት ማስፋፋት ወረራውን እንደፈፀመ ሁሉ ሱዳን ጦርም ዛሬ ኢትዮጵያ ወስጣዊ ሰላሟ እና አንድነቷ የላላ መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብተው የግብጽ እና የሱዳን መንግስታት በጋራ በመሆን ከእጅ አዙር ጦርነት በዘለለ የቀጥታ ወረራ ፈጽመውብናል። በሰሜኑ በኩል ለሶስት ዓመታት አብጦ የነበረው ጎማ ሲተነፍስ ፣በምእራብ ደግሞ ሌላ ከባድ ፈተና ተደቅኖብን የምናከብረው ድል ነው የካራ ማራ ድል።
የሱማሌ ፓለቲከኞች እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሱማልኛ ተናጋሪ አከባቢዎችን በመውረር ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት ህልም ይዘው ነው የሚኖሩት እንደ አገር ውስጣዊ ጥንካሬን መፍጠር የሚገባ ወቅት ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ የነበራቸው ሜ/ጀነራል መርዳሳ የሶማሊያ ጦር በምስራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር፤ በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር ድንብር ጥሶ ገብቶ እንደነበር አንስተዋል።
ድሉን ትውልዱ ምን ያክል ተረድቶታል የሚለው ጥልቅ ጥያቄን የሚፈጥር መሆኑ እንዳለ ሆኖ መነቃቃቶች ግን እንዳሉ አይካድም። ለአብነትም የወጣቶቹን ሰሞነኛ ዘፈን ማንሳት ይቻላል።
እንደ አሊ በርኬ
ታሪኬን ማርኬ
መስዋእት ነው ልኬ
ትውልዱ ታሪክን ማየት መጀመሩን የሚያሳይ መሆኑን እንደ ማጣቀሻ ያነሳሉ። በስደት ያሉት የቀድሞው መሪ ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ዘፈኑን ሰምተው እንደወደዱት የበኧር ልጃቸው ዶ/ር ትእግስት መንግሥቱ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።
ዘፈኑን ሰምቶ ወዶታል “በጦርነቱ ጊዜ ያልነበረ ወጣት ይህንን አስቦ ታሪክን አጥንቶ ይህንን ዘፈን በማዘጋጀቱ የሚያስደስት ነው” ብሏል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com