የእለት ዜና

የመጀመርያው የግብርና ባንክ ሊቋቋም ነው

የኢፌዲሪ የግብርና ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ የግብርና ባንክ እንደሚያቋቁም አስታወቀ። ባንኩን ለመመስረት የቀረበው ሀሳብ በጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) መጽደቁንም የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ማሻሻያውን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት ባቀረበበት ወቅት የግብርናው ዘርፍ ከተጋረጡበት ችግሮች ለማውጣት አንዱ መፍትሄ የግብርና ባንክ ማቋቋም መሆኑን ኤጀንሲው ገልጾ አሁን ግብርና ባንክ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሀሳብ አፍላቂነት ሊቋቋም የታሰበው የግብርና ባንክ በግብርና ሚኒስቴር ስር እንደሚተዳደርም ተገልጿል። ባንኩ ሲመሰረት አክሲዮን በመግዛት የሚያቋቁሙት በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ሠራተኞች እንደሆኑም ታውቋል። በአገራችን በርካታ ባንኮች የሚገኙ እና እየተመሰረቱ ያሉ ቢሆንም በግብርና ዘርፍ ላይ የሚሠራ አንድም ባንክ አለመኖሩን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቋል።

በግብርና ላይ ትኩረት አድጎ የሚሠራው ባንክ ሲቋቋም ከአክሲዮን ማኅበሩ አባላት ውጭ 3 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል። ባንኩ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ከመቅረፉ ባለፈ የሚፈጥረው የሥራ ዕድልም ሌላኛው ጠቀሜታ እንደሆነ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ዘርፎች ቀዳሚ የሆነው የግብርናው ዘርፍ እንደሆነ እና ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ምንዛሬ ግን ለሌሎች ዘርፎች ተመልሶ ለብድር ይውላል እንጂ ዘርፉ ተጠቃሚ አይሆንበትም፤ ይህን ችግር ይፈታል ተብሎ የሚታሰበው በተለይ ደግሞ የገንዘብ ብድር የማግኘት ችግሩን የሚፈታው አሁን ለመቋቋም የታቀደው የግብርና ባንክ ነው በማለት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዐቶች እና ግብይት ዳይሬክተር መንግሥቱ ተስፋ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች ከሚያበድሩት ዓመታዊ ብድር አምስት በመቶ የሚሆነውን በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ግለሰቦች እንዲያበድሩ የሚል መመሪያ ባለፈው ዓመት 2012 የካቲት ላይ አውጥቶ ካለፈው ከሐምሌ 2012 ጀምሮም ተግባራዊ መሆኑ ይታወሳል።

በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ከባንኮች ብድር ሲወስዱ ተንቀሳቃሽ ንብረቶቻቸውን እንደ ማስያዣ መጠቀም እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል። ይህ ማለት ተሸከርካሪዎች፣ ትራክተሮች ወይንም እንደ መጋዘን ያሉ ግንባታዎችን እና የአዝዕርት እህሎችን ጭምር ለማስያዣነት ማቅረብ እንደሚችሉ ተቀምጧል።

ከባንኮች በቀጥታ ብድር ማግኘት የማይችሉ አርሶ አደሮች እና ትንንሽ በሆኑ የግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማለትም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ከሆኑ አበዳዎች ብድር እንዲያገኙ ይደረጋል ለተቋማቱ ደግሞ ባንኮቹ ብድር በመስጠት ለተበዳሪዎቹ ገንዘቡ ተደራሽ እንዲሆን ያደርጋሉ።

ባንኮች ብድር ከሚሰጧቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የግብርናው ዘርፍ ቢሆንም ግን የሚሰጠው የብድር አቅርቦት አነስተኛ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እና የግሉ ዘርፍ አማካሪ ከሆኑት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በግብርና ዘርፍ ላይ ብቻ የሚሠራ ባንክ የመመስረት ሀሳብ ለረጅም ጊዜ የቆየ እንደሆነ እና አዲሱ የግብርና ባንክ የብድር አገልግሎት የሚሰጠው በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አምራቾች መሆኑ እና ሌሎች ባንኮች ለዘር የሚሰጡት የብድር መጠን ማነሱ ባንኩ ተመራጭ እንዲሆን እንደሚያደርገው በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እነ አርሶ አደሮች ከባንክ እና ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ብድር በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ዘመናዊ እና ኤሌክትሮኒክ የሆነ ማዕከል አቋቁሞ ወደ ሥራ እንደገባ ይታወሳል።

ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ማዕከል ማለት ከባንኮች ብድር ለመውሰድ የሚፈልጉ ሰዎች ያሏቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በማስመዝገብ እና የተለየ መለያ ቁጥር ወይንም ኮድ ለንብረቱ ከተሰጠ በኋላ ባለንብረቶቹ ለመበደር ወደ ባንኮችም ሆነ ወደ ማይክሮ ፋይናንሶች ሲሄዱ የተመዘገበበትን ቁጥር ብቻ በመያዝ ብድር ለማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል አሥራር መሆኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!