የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት በድኅረ 1983

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም ላያንጸባርቅ ይችላል።

በሶለን ገመቹ (አምቦ ዩንቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
1. መንደርደሪያ
የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ዲሞክራሲ በዳበረባቸው የምዕራባዊ ሃገራት የበለጠ አሳታፊ ዲሞክራሲ ሥር እንዲሰድ እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው ሃገራት ደግሞ ከተማከለ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ አሳታፊ ዲሞክራሲ የሚሸጋገሩበት መንገድ ተደርገው ይታሰባሉ። በዚህ አስተሳሰብ መሰረት በአንድ ሃገር ውስጥ ጠንካራ አቅም ያለው የሲቪል ማኅበር ዘርፍ መኖር የዲሞክራሲ ሥርዓቱ አካል እና ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የኻያኛው ክፍለ ዘመን ኹለተኛ አጋማሽ የሲቪል ማኅበራት በደቡብ የዓለማችን ክፍል በሰፊው መታየት የጀመሩበት ወቅት ነው። ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱት የሰብኣዊ ኪሳራዎች መከሰት፣ የዓለማችን ፖለቲካ መዋዠቅ፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ያለ የባህል ልዩነት የሚፈጥረው አለመረጋጋት፣ ሉላዊነት (globalization) በፍጥነት መጨመር እና መንግሥታት ለዜጎቻቸው ቅቡልነት ያለው አስተዳደር ማቅረብ አለመቻላቸው ናቸው። የሲቪል ማኅበራት በእነዚህ ሃገራት ውስጥ የሰብኣዊ እርዳታ፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶች፣ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የሰብዓዊ መብት እና የፖሊሲ ቅስቀሳ (policy advocacy)፣ እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥት እና ከግሉ ዘርፍ በመቀጠል የማኅበረሰቡ ሦስተኛ ዘርፍ የመሆን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በደቡብ የዓለማችን ክፍል የብዙ ሃገራት መንግሥታት የዘርፉን ነጻነት የሚያግድ ጠንካራ መቆጣጠሪያ ሕግጋትም ማውጣት ጀምረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ተሳትፎ፤ ብዝኀነትን ለማዳበር፣ ውጤታማ የመንግሥት ፖሊሲ እንዲቀረጽ ለማድረግ እንዲሁም ፍትሐዊ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያስችላሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ዘርፉ የዜጎችን ፍላጎት ወደ አደባባይ በማውጣት የበለጠ አሳታፊ ዲሞክራሲን የማነሳሳት ሚና እንዳለው ይታመናል። በዚህም የሲቪል ማኅበራት የመንግሥትን ተጠያቂነት በማጉላት ቅቡልነት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላሉ። ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት መኖር ተፈላጊነቱ እያደገ የመጣው የመንግሥት ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ከማረጋገጥ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ነው። ልማት እና ዲሞክራሲን የማስፈን ኃላፊነት በዋነኛነት የመንግሥት ቢሆንም በመንግሥት እና በሲቪል ማኅበራት መካከል የሚፈጠር ቅንጅት እንደ ድህነት ቅነሳ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጠት፣ የመገለል ችግርን ለመቅረፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ያስችላል።

ከኹለት ሳምንታት በፊት በዚሁ ዓምድ ሥር የኢትዮጵያን ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ታሪክ በሚል ርዕስ ሥር ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራትን አመጣጥ እና ዘርፉ የነበረውን ሚና አስነብቤያለሁ። የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ሚና እስከ 1983 የደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ የሰብኣዊ እርዳታ ማቅረብ ላይ ያተኮረ ስለነበር ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተጽዕኖ ሥር እንደነበር ከታሪኩ መረዳት እንደሚቻልም ሞግቻለሁ።
በዚህ ጽሑፍ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የነበረውን ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ታሪክ በማስቃኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ያለውን ግንዛቤ፤ ዘርፉ የሚሰራበትን የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሁም የሲቪል ማኅበራቱ ተልዕኳቸውን የሚያስፈፀሙበት አቅም ለመገምገም እሞክራለሁ።

2) የሲቪል ማኅበራት በኢሕአዴግ ዘመን መንግሥት
1983 የደርግ መንግሥት በትጥቅ ትግል ተሸንፎ አሸናፊው ቡድን የሽግግር መንግሥት አቋቋመ። አዲሱ መንግሥት ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ልማታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ርዕዮተ ዓለም ይዞ ወደ ሥልጣን መጣ። በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ የዓለምን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሕገ መንግሥት ተቀርጾ በ1987 ጸደቀ። የመጀመሪያው ምርጫ ተካሂዶም ኢሕአዴግ በይፋ ሥልጣን ያዘ። በዚህ ሕገ መንግሥት የተቋቋመው የኢፌዴሪ መንግሥት ተልዕኮውን ለማስፈጸም በፌደራል እና በክልል ደረጃ የልማት ስትራቴጂዎችን ቅርጾ ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚህ ሕገ መንግሥት የዜጎችን የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብት እውቅና ተሰጥቶታል።

ከደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተለያየ ዓላማ የተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪል ማኅበራት እና ድርጅቶች መታየት ጀመሩ። ይህ ለመሆኑ እንደምክንያት የሚጠቀሱት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሲቪል ማኅበራት ልማትና ዲሞክራሲን ለማስፈን ትልቅ አስተዋጾዖ እንዳላቸው ስለታመነ እና ትልቅ ትኩረት ስላገኙ፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ መንግሥት ዘርፉ የመንግሥትን ዓላማ ለማስፈጸም አጋዥ መሆኑን ስላመነ ነው።

ይሁን እንጂ በደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት የነበሩት የሲቪል ማኅበራት በቀላሉ ከእርዳታ ሰጪነት ሚናቸው አልፈው ዘላቂ ልማት እና ዲሞክራሲ ለማምጣት የሚያስችል ቁመና ላይ አልነበሩም። ለተለያየ ዓላማ የተቋቋሙ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበራት የነበሩ ቢሆንም የነበራቸው ውስን የኢኮኖሚ አቅም፣ ያልሰለጠነ የሰው ኀይል እና ለዘርፉ ያላቸው ልምድ ውስንነት ማኅበራቱ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ቁመና ላይ ላለመሆናችው እንደ ምክንያት ይጠቀስ ነበር። ብዙዎቹ ድርጅቶች እና ማኅበራት የዘርፉን ዓላማ እና ተግባር በአግባቡ ያልተረዱበት ሁኔታ ነበር። በተጨማሪም የሃገር በቀል ድርጅቶች አቅም ውስንነት፣ የስትራቴጂ እውቀት ማነስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና ተጠያቂነት ያለው የሒሳብ አያያዝ አለመኖር ችግሩን አባብሰውታል። በዚህ ችግር ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ዓለም ዐቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች (International NGOs) ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር መሥራት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሀገር በቀል ድርጅት አመራሮች ይህን ችግር ተረድተው የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ድጋፍ መጠየቅ ጀምረው ነበር። 1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ከሃገር በቀል ድርጅት አመራሮች በተጨማሪ ችግሩ በመንግሥትና ዓለማቀፍ ድርጅቶች መስተጋባት ጀመረ። በምላሹም የዘርፉን አቅም ለመገንባት ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲሰጥ ቆየ።

ሥልጠናዎቹን በማመቻቸት ረገድ የክርስቲያን በጎ አድራጎት እና ልማት ማኅበር (CCRDA) በመባል የሚታወቀው የድርጅቶች ሕብረት፣ ኢንተር አፍሪካን ግሩፕ (Inter African Group) በመባል የሚታወቀው የቀጠናው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረት እና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ትልቅ አስተዋጾዖ አድርገዋል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ብዙ የአገር በቀል ድርጅት ኃላፊዎችን በዚምቧቤ፣ ፊሊፒንስ እና ደቡብ አፍሪካ ልኮ በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ግንዛቤ እንዲወስዱ አድርጓል። በሒደትም ምንም እንኳን በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ድርቅና እርዳታ ታሪክ ሆነው ያልቀሩ ቢሆንም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በረጅም ጊዜ ልማት ላይ ያላቸው አስተዋጽዖ በመንግሥት ዐይን ዋጋ ተሰጥቶታል። ከዚህ ጊዜ በኋላ የሲቪል ማኅበራት ተልእኮ ሰብኣዊ እርዳታ ማከፋፈል ብቻ መሆኑ ቀርቶ አቅም ግንባታ፣ የአገልግሎት ማቅረብ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን መተግበር እና የፖሊሲ ቅስቀሳ (Policy advocacy) በሒደት መጨመር ጀመር። ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ከእርዳታ ማከፋፈል ወደ አገልግሎት ሰጪነት የተሸጋገሩት በ1980ዎቹ ውስጥ ነው። በ1990ዎቹ ውስጥ ደግሞ የሰብኣዊ መብት ተከራካሪ የሲቪል ማኅበራት መታየት ጀመሩ።

በ1987 መንግሥት የሲቪል ማኅበራት መመሪያ አውጥቶ ነበር። ይህ መመሪያ የ1952 የሲቪል ማኅበራትን የሚያስተዳደረው የፍትሐ ብሔር ሕግ ክፍል በማሻሻል፤ ዘርፉን በዓይነት ከፋፈለ። በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ማኅበራት እና ድርጅቶች የሚሰማሩበትን መስክ ወሰነ። ዘርፉን የሚቀላቀሉ ድርጅቶችን የመመዝገብ ሥልጣን የእርዳታ ማስተባበሪያ እና ማቋቋሚያ ኮሚሽን መሆኑ ቀርቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር ተሰጠ። ፍቃድ ያወጡ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥልጣን ለፌደራል እና ለክልል የእርዳታ ማስተባበሪያ እና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ተሰጠ።

ከ1983 እስከ 2000 ድረስ የሃገሪቱን ዘርፈ ብዙ የልማት ፍላጎቶችን በሕገ መንግሥቱ እና በመንግሥት በተቀመጠው የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት አስተዋጾዖ ለማድረግ የሚቋቋሙ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር ከፍተኛ እድገት አሳየ። በ2000 መጨረሻ በሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪል ማኅበራት ተመዝግበው በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ነበር። ይሁን እንጂ የ1997 ሃገር ዐቀፍ ምርጫ ያስከትለው ችግር በመንግሥት እና በሲቪል ማኅበራት መካከል ያለውን ግንኙነት አበላሽቶታል። መንግሥት የሲቪል ማኅበራቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከውጪ ሃገር በሚመጣ ገንዘብ እየረዱ ነው በሚል ሲከስ ነበር። በዚህ ምክንያት በ2001 መንግሥት የሲቪል ማኅበራትን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚገድብ አዋጅ አወጣ። ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ዘርፉ በኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ በመፍጠር አገሪቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስገባታል የሚሉ አጥኚዎች ነበሩ።

በጣም አነጋጋሪ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2009 መታወጅ ለተመዝጋቢ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት እንዲሁም አዲስ ለተቋቋመው የሲቪል ማኅበራት አስተዳዳሪ ኤጀንሲ የራሱን ተግዳሮት እና ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። መንግሥት ይህን አዋጅ ለማውጣቱ የሚከተሉትን እንደ ምክንያት ጠቅሷል። እነሱም በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የዜጎችን የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ፣ የሲቪል ማኅበራትን ቅቡልነት ለማረጋገጥ፣ ዘርፉ የሚታማበትን የግልጽነት እና ተጠያቂነት ችግር ለመቅረፍ፣ ለሲቪል ማኅበራት ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር እና አዎንታዊ ሚና በሃገሪቱ ልማት ላይ እንዲኖራቸው ለማመቻቸት የሚሉ ናቸው።

አንዳንድ ተቺዎች በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የዜጎችን የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ እና ለሲቪል ማኅበራት ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የሚሉትን ምክንያቶች አይቀበሉትም። ይህ አዋጅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 ላይ የተጠቀሰውን የዜጎች የመደራጀት መብት የሚጥስ ነው ሲሉ ይተቻሉ። በተጨማሪም ይሄ አዋጅ በመብት ላይ በሚሰሩ ድርጅቶች ከውጪ ሃገር በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያገኙትን ገቢ ላይ ገደብ ጥሎአል። በተጨማሪም ገቢያቸውን መቶ በመቶ ከውጪ ሃገር ድርጅቶች በሚያገኙ ሃገር በቀል ማኅበራት የሚሠሩበት ዘርፍ ላይ ገደብ ጥሏል። ከዚህ አዋጅ ጋር በተያያዘ የተደረጉ ጥናቶች ዘርፉ በተለይ ሃገር በቀል ድርጅቶች ከውጭ ምንጮች የሚያገኙት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረ እና አስተዳደራዊ እና ቀጥተኛ የፕሮጀክት ወጪን የመለየት ተግዳሮት እንደገጠማቸው ይሳያሉ።

ምንም እንኳን ብዙ አጥኚዎች የዚህን አዋጅ በሲቪል ማኅበራት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የገለጹ ቢሆንም ሌሎች ደግሞ የሲቪል ማኅበራቱ በልማት እና በአገልግሎት አቅርቦት ዙሪያ ያላቸውን ስኬት ያወሳሉ። ለዚህ እንደማሳያ የሚጠቅሱት አዋጁ ከወጣ በኋላ የአገልግሎት ሰጪ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር መጨመሩን ነው።

ይሁን እንጂ ከ2006 እስከ 2010 የኢሕአዴግ መንግሥት ተከታታይ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ገጠመው። በዚህ ሕዝባዊ ግፊት ምክንያት በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ እና በ2010 በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራ የፖለቲካ ሽግግር ተካሄደ። ይሄ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ማኅበረሰቡ የነበረው መንግሥታዊ አስተዳደር እንዳልተስማማቸው ማሳያ ነው። ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጁ እና የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳይቀር ወደ ሃገራቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ተደረገ። የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስፍት ባሻገር አሳሪ እና አፋኝ የሚባሉ ሕጎችን ማሻሻል ጀመረ። እነዚህ ሕጎች አንዱ የሆነው የ2001ዱ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ ስለነበረ የካቲት 28 ቀን 2011 አዲሱ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ታወጀ። መንግሥት ይህን አዋጅ ካወጀበት ምክንያቶች አንዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ለማድረግ የተመቻቸ ምኅዳር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን በመረዳት እንደሆነ በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com