የዘውግ ፓርቲዎች እና ቅራኔ

Views: 542

በታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) የዘውግ ፓርቲዎች ለሰላም አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ከዴሞክራሲ ጋር ተፃራሪዎች ናቸው በማለት የአገራትን ተመክሮ በማጣቀስ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ሕግ በዘውግ መደራጀትን አይከለክልም፤ እንዲያውም የመንግሥት አወቃቀሩ ለዘውግ ፓርቲዎች መበራከት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል የሚሉት ታደሰ፥ ይህ ለኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚበጅ አይደለም ሲሉ ደምድመዋል።

ትርጓሜ
የዘውግ (ethnic) ፓርቲ ማለት በአንድ አገር ካሉ በርካታ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለይቶ የአንዱ ማኅበረሰብ ጥቅም ተከራካሪና አስጠባቂ አድርጎ ራሱን የሚያቀርብና ይህንንም በአባላት ምልመላ፣ በሀብት አሰባሰብ፣ በምረጡኝ ዘመቻው፣ ፓርቲው ሥልጣን ብይዝ እፈጽማቸዋለሁ ብሎ ለደጋፊዎቹ በሚሰጣቸው ተስፋዎች የሚያመላክት ፓርቲ ማለት ነው።በዚህ ትርጓሜ ውስጥ ቁልፍ ቃል ‹‹ለይቶ›› የሚለው ነው።

አንድ የዘውግ ፓርቲ ከአንድ በላይ ለሆኑ ማኅበረሰቦች ጥቅም ተከራካሪ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፤ ሆኖም ይኸንንም ለመፈፀም የሚገለል የጋራ ጠላት መኖር አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ባህርያት ያሏቸው ፓርቲዎች ዘር ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትም፣ በአንድ አገር ውስጥ ያለ መልክዓ ምድራዊ ክልልንም መሠረት አድርገው ሊነሱ ስለሚችሉ በርካታ ፀሐፍት ከዘውግ ባሻገር ያሉትንም ለማጠቃለል “particularistic parties” ማለትን ይመርጣሉ። “particularistic parties” ዋና መለያቸው ከአገር ሕዝብ ለይተው “አንድ የተለየ” ማኅበረሰብ ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ነው። “particularistic parties” የአማርኛ አቻ ለጊዜው ስላላገኘሁለት እና ችግራችንም በአብዛኛው ዘር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ‹‹የዘውግ ፓርቲዎች›› በሚለው መወሰን መርጫለሁ።

የዘውግ ፓርቲዎችን ባህርይ ይበልጥ ለመረዳት ተነፃፃሪዎቸውን ማጤን ይጠቅማል። የዘውግ ፓርቲ ተነፃፃሪ (ተቃራኒ) “Civic Party” ይሰኛል። ሲቪክ ፓርቲ የዜጎች ሁሉ ፓርቲ ነው። ሲቪክ ፓርቲ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ነገድ፣ ሃይማኖት፣ ወይም ክልል ለመጥቀም ሲል የተቋቋመ ሳይሆን የአገሩ ዜጋ የሆነ ማንኛውም ሰው አባል ሊሆን የሚችልበት፤ ፖሊሲዎቹም አገሩ ሁሉ የሚያዳርሱ ናቸው። የሲቪክ ፓርቲ የድጋፍ መሠረቱ አንድ የተለየ ማኅበረሰብ ብቻ አይደለም። እርግጥ ነው ‹‹ሲቪክነት›› ይበልጥ የሚጠቅመው ማኅበረሰብ ሊኖር ስለሚችል የሲቪክ ፓርቲም በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦችን በእኩል ላይዝ፤ በእነሱም እኩል ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ለምሳሌ ሲቪክ ፓርቲዎች በአብዛኛው በከተሜዎች እና በተማሩ ሰዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው፤ ይሁን እንጂ በአባላት ምልመላቸው፣ በድጋፍ አሰባሰባቸውም ሆነ በጥብቅናቸው ማንንም አያገሉም።

የዘውግ ፓርቲዎች፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ
የዘውግ ፓርቲዎች ከሰላምና ዴሞክራሲ ጋር አብረው ለመሄድ በጣም ይቸገራሉ፤ ከመቸገርም በላይ በብዙ ሁኔታዎችና አገሮች ተፃፃሪ ናቸው። የዘውግ ፓርቲዎች ለሰላም አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥሩ ስለመሆኑ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ አስተያየት ነው። ‹‹የዘውግ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ ተፃራሪዎች ናቸው›› ብሎ ለመደምደም ግን የማያስደፍሩ ጥቂት ምክንያቶች አሉ፤ ዋነኛዋ ምክንያት ህንድ ናት፤ ለዚህም እዚህ ብናነሳቸው የማንጨርሳቸው ሕገ መንግሥታዊ ምክንያቶች አሉ። ሆኖም የህንድ ሁኔታም ቢሆን ‹‹ተፃራሪ›› የሚለውን ቃል ከመጠቀም ያግድ ይሆናል እንጂ ችግር ፈጣሪነታቸውን አይለውጥም። የዘውግ ፓርቲዎች ችግር ፈጣሪነት ምንጭ ለቅራኔ ቅርብ መሆናቸው ነው፤ ለዚህም አራት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:-

1. አብላጫን እወክላለሁ ባይ የዘውግ ፓርቲ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ውህዳንን (minorities) ማግለሉና መጫኑ አይቀርም። የአብላጫ ነገድ ፓርቲ እወክለዋለሁ በሚለው ነገድ ውስጥ ልዩነት የሌለ ለማስመሰል የውህዳኑ ህልውና ሊክድ ይችላል፤ ህልውናቸውን ቢቀበል እንኳን ለራሱ እንዲኖረው የሚፈልጋቸው መብቶች እንዲኖራቸው በጭራሽ አይፈቅድም። በዚህም ምክንያት አብላጫን እወክላለሁ ባይ የዘውግ ፓርቲ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉት ውህዳንን ጨቋኝ ነው። በዚህም ምክንያት የአብላጫ ዘውግ ፓርቲ በማኅበረሰቡ ካሉ ውህዳን ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ይህ ግጭት ለረዥም ጊዜ ድብቅ (የተቀበረ) ቅራኔ ሆኖ ሊቆይ ስለሚችል በፈነዳ ጊዜ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ፤ አውዳሚነቱ ከፍተኛ የሆነ ቅራኔ ነው።

2. ውህዳንን እወክላለሁ የሚል የዘውግ ፓርቲ ራሱን የዘውጉ ‹‹ነፃ አውጭ›› አድርጎ ነው የሚመለከተው። የዚህ ፓርቲ ‹‹የነፃ አውጭነት›› ‹‹ተልዕኮ›› እና የሚገዳደረውን ኃይል ግዝፈት ‹‹አመጽ›› አዋጭ ስትራቴጂ የመሆኑ ዕድል ከፍተኛ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ውህዳን ሆኖ አብላጫን የሚገዳደር የዘውግ ፓርቲ ከሰላማዊ ፉክክር በመውጣት የአመፃ መንገድ ለመምረጥ በጣም ቅርብ ነው። የአመፃ መንገዱን አገዛዙን ሰላም በመንሳት ሰበብ ሕዝብን ሰላም ከመንሳት ጀምሮ እስከ ትጥቅ ትግል ሊደርስ ይችላል። በዚህም ምክንያት ውህዳንን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች መብዛት የአገር ውስጥ ሰላምን አደጋ ላይ ይጥላል።

3. የዘውግ ፓርቲዎች ሁሉ (እንወክለዋለን የሚሉት ማኅበረሰብ አብላጫም ይሁን ውህዳን) የፖለቲካ ‹‹ጨዋታውን›› የሞትና የሕይወት ጉዳይ ያደርጉታል። ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የተሻሉ ፖሊሲዎችን በማቅረብ ፓሊሲዎቹን ማስተግበሪያ ሥልጣን መፈለጊያ በመሆን ፋንታ ‹‹በደስታ የመኖር›› ወይም ‹‹ጨርሶ የመጥፋት›› ጉዳይ አስመስለው በማቅረብ ‹‹የጨዋታውን ዋንጫ›› ዋጋ በማናር ፖለቲካን ከምክንያት ይልቅ ስሜት እንዲገዛው ያደርጋሉ። የዘውግ ፓርቲዎች የደጋፊዎቻቸውን ስሜት እንጂ ምክንያታዊነት ፈጽሞ አይፈልጉም። የዘውግ ፓርቲ ደጋፊዎች እነሱ የሚወዱት የእግር ኳስ ቡድን ጥሩ ቢጫወትም ባይጫወትም ማሸነፍ አለበት ብለው ለጠብ እንደሚጋበዙ የእግር ኳስ ቡድን አፍቃሪዎች ናቸው። በስሜት የሚነዱ ደጋፊዎቻቸው ግጭቶችን ይፈጥራሉ፤ የተፈጠሩትን ያባብሳሉ።

4. የዘውግ ፓርቲዎች ሁሉ (እንወክለዋለን የሚሉት ማኅበረሰብ አብላጫም ይሁን ውህዳን) በማኅበረሰብ መካከል ያለውን ልዩነት ያሰፋሉ፤ የአንድ አገር ማኅበረሰቦችን በማቀራረብ ፋንታ ያራርቃሉ፤ ለጋራ ችግሮቻቸው በጋራ እንዳይቆሙ ያደርጋሉ። የአንዱ ልማት በሌላው ጥፋት፤ የአንዱ መልካም እድል በሌላው ክፉ እድል፤ የአንዱ ትርፍ በሌላው ኪሳራ የተገኘ እንደሆነ አድርገው በማቅረብ በአንድ አገር ባሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ዘላቂ የጠላትነት ስሜት እንዲሰርጽ ያደርጋሉ። በዚህም ለማርገብ ረዥም ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ ሥር የሰደደ ቅራኔ እንዲፈጠር ምክንያቶች ይሆናሉ።
የዘውግ ፓርቲዎች የፖለቲካ ጽንፈኝነት በመፍጠር ለሰላምና መረጋጋት አደጋ ስለመሆናቸው ብዙ ምሁራን (ኢትዮጵያዊያን ጨምሮ) የምርምር ጽሁፎችን ያቀረቡበት ጉዳይ ነው።

ዴሞክራሲን ከዴሞክራሲ መታደግ
ዴሞክራሲ የዜጎችን የመደራጀት መብት ማክበር ስላለበት ለጠላቶቹም ሰፊ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ አንዳንድ ምሁራን ‹‹የዴሞክራሲ ዋነኛ ጠላት ራሱ ዴሞክራሲ ነው›› ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከዚህም አልፎ ተገቢው ተቋማዊ ቁጥጥር ካልተደረገ ዴሞክራሲ የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እንደሆነም ይከራከራሉ። ሂትለርና ሙሶሎም ዴሞክሲን ለማጥፋት ያስቻላቸውን ሥልጣን እጃቸውን ውስጥ ያስገቡት ዴሞክራሲያዊ በሆኑ መንገዶች ተረማምደው መሆኑ ብዙ ጊዜ በማስረጃነት ይጠቀሳሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉን ማስረጃዎች በሂትለርና በሙሶሎኒ የሚቆሙ አይደሉም።

በ1991 (እ.አ.አ.) በአልጄሪያ በ30 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ተደረገ። በዚህ ምርጫ ሥልጣን ከያዘ ዴሞክራሲን በማገድ አገሪቷን በሸሪዓ ሕግ እንድትተዳደር የማድረግ ዓላማ ያለው የእስላማዊ መድህን ግንባር (The Islamic Salvation Front) ከ231 የፓርላማ ወንበሮች 189 አሸነፈ፤ ዴሞክራሲ የራሱን አጥፊ እንዲመረጥ መሣሪያ ሆነ። ይሁን እንጂ ተመራጩ ፓርቲ ሥልጣን ሳይዝ ወታደራዊ መንግሥት የመንግሥትን ሥልጣን ተቆጣጠረው፤ ጥቂት የማይባሉ የዴሞክራሲ አጥኚዎች ወታደራዊውን መንግሥት ዴሞክሲን የታደገ አድርገው ወሰዱት።

በተመሳሳይ በ2011 (እ.አ.አ.) ግብጽ ተፈጽሞ ነበር። ከጥር 12 ቀን 2009 እስከ ጥር 12 ቀን 2013 (January 20, 2017 – January 20, 2021) ድረስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንድ የነበሩት የዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ዛሬም ዴሞክራሲ የራሱ ጠላት የመሆኑ ዕድል ሰፊ መሆኑ ጠቋሚ ነው። አብላጫ ድምጽ ባለማግኘቱ ባይሳካም መስከረም 8 ቀን 2007 (September 18, 2014) የተሰጠው የስኮትላንድ ሕዝበ ውሳኔ ዩናይትድ ኪንግደም ዛሬ ባለችበት ሁኔታ እንዳትቆይ ሊያደርጋት የተቃረበ ነበር። የሰኔ 16 ቀን 2008 (June 23 2016) ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ያሳለፈችው ሕዝበ ውሳኔ ዴሞክራሲ የገዛ ራሱን ጠልፎ ሊጥል የሚችልበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ካመላከቱ ክስተቶች አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሚ በኋላ አገሮች የሀገር አንድነትን እና ዴሞክራሲን ከራሱ ከዴሞክራሲ ለመታደግ አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ ጀምረዋል። የእነዚህ እርምጃዎች አካል የሆኑት እና በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት የተፈለገው ዴሞክራሲን የዴሞክራሲ ፀር ከሆኑ ፓርቲዎች የመከላከል እርምጃዎች ናቸው። የእነዚህ እርምጃዎች መሠረት ‹‹የመደራጀት መብት ሊከበር የሚገባው ቢሆንም እንኳን ይህንኑ መብት ለመደፍጠጥ መደራጀትን መፍቀድ አይገባም›› የሚል ነው። በዚህም መሠረት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በርካታ የአውሮፓ ፓርቲዎች ሕጋዊ ፈቃድ ተከልክለዋል፤ አንዳዶቹ ተሰጥቷቸው የነበረው ፈቃድ ተነጥቀዋል።

ለምሳሌ የጀርመኑ ሶሻሊስት ሪክ ፓርቲ (Socialist Reich Party) ከኹለተኛ የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በ1949 (እ.አ.አ.) የተቋቋመ፤ በምርጫ ተወዳድሮ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በሕዝብ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች የነበሩት ቢሆንም የናዚን አቋሞች በመደገፉ 1953 (እ.አ.አ.) በሕግ ታድጓል። የኦስትሪያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በ1967 (እ.አ.አ.) ተመስርቶ በተመሳሳይ ምክንያት በ1988 (እ.አ.አ.) በሕግ ታግዷል። የኔዘርላንዱ ማዕከላዊ ፓርቲ (The Center Party) በ1980 (እ.አ.አ.) ተቋቁሞ የቀኝ ጽንፈኛ አቋም በማራመዱ 1986 በሕግ ታግዷል። አውሮፓ ውስጥ አንድን የፖለቲካ ፓርቲ በሕግ የሚያሳግዱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

1. ሃይማኖት – የሃይማኖት ጽንፈኝነት የሚያራምዱ ፓርቲዎች በሁሉም የአውሮፓ አገሮች ክልክል ናቸው። ይህ ክልከላ በኢስላማዊ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ነው ሲፀና የሚታየው የሚል ትችት ቢቀርብበትም፤ በመሠረቱ ሐሳቡ ይህ እገዳ ሁሉን ጠቅላይ (totalitarian) ርዕዮተ ዓለሞችን ያጠቃልላል። ዋና ዓላማው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመጣው ፓርቲን ዴሞክራሲን እንዳይገል አሊያም እንያቀጭጭ መከላከል ነው።

2. ክልላዊነት ወይም ተገንጣይነት በብዙ የአውሮፓ አገሮች የመገንጠል ወይም ‹‹ከዚህ ወጥተን ከዚያ ጋር እንዳበል›› የሚሉ (irredentist) ፓርቲዎችን አይፈቅዱም። መገንጠልም ሆነ ወደ ቀድሞ ግዛት መመለስ (ወይም ግዛት ማስመለስ) ሰላምንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያናጉ ሊሆኑ ይችላሉ። Euskadi Ta Askatasuna (ETA) የተሰኘው የሰሜን ስፔን እና ፈረንሳይ ተገንጣይ ፓርቲ ከ1959 (እ.አ.አ.) ራሱን እስከ አከሰመበት 2018 (እ.አ.አ.) ሕጋዊ ፈቃድ ተከልክሎ ሕገወጥ ፓርቲ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። 2017 (እ.አ.አ.) በስፔን ካታሎኒያ ግዛት የተሰጠው የመገንጠል ውሳኔ-ሕዝብና ተከትሎ የመጣው የውሳኔው መታገድና የፖለቲካ መሪዎቹ መታሰርና በድርጅቶቹም ላይ እስካዛሬ የቀጠለው ጥብቅ ቁጥጥር ማስታወስ ይጠቅማል።

3. አመጽን እንደ ትግል ስትራቴጂ የሚወስዱ ፓርቲዎች – እነዚህ ፓርቲዎች መታገድ ብቻ ሳይሆን በሽብርተኝነት ሊፈረጁም ይችላሉ። የአመጽ ትግልን አለማውገዝም በተባባሪነት የሚያስጠይቅባቸው ጊዜዓት አሉ። በ2001 (እ.አ.አ.) የተቋቋመው Batasuna (አንድነት) የተሰኘው የስፔን ፓርቲ በሕግ የታገደው ETAን በፋይናንስ መደገፉ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ነው፤ በ2013 (እ.አ.አ.) ራሱን አከሰመ።

4. ሽብርን እንደስትራቴጄ የሚጠቀሙ ፓርቲዎች – ሽብርን እንደትግል ስትራቴጄ ለመጠቀም የሚቀርቡ ማናቸውም ምክንያቶች (ለምሳሌ የበደል መብዛት) ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በአብዛኛው የአውሮፓ አገራት ስምምነት ያገኘ ጉዳይ ነው።
የአውሮፓ ልምድ የሚያሳየው የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲን ለመታደግ በጽንፈኛ እና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች ላይ የሕግ ቁጥጥር የማድረግ አስፈላጊነትን ነው።

የአፍሪቃ አገራት ልምድ
የአፍሪቃ ችግር ከአውሮፓው ይለያል፤ አገሮች በመፍትሔነት የወሰዷቸው እርምጃዎችም እንደዚሁ የተለዩ ናቸው። የአፍሪቃ አገራት በየአገሮቻቸው ሕግጋት የሚፈቀዱ እና የማይፈቀዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓይነት ላይ ወጥነት የለም፤ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገሮች በፓርቲዎች ላይ የሚያደርጓቸው ቁጥጥሮች አሏቸው። በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ወንድማችነት፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ ማኅበረሰብ፣ ዘውግ፣ እምነት/ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ቋንቋ፣ ሙያ፣ ክልል፣ ማኅበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ደረጃ መሠረት ያደረጉ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቋቋም አይቻልም። በርግጥ የክልከላዎቻቸው የሕግ መሠረቶችም የተለያዩ ናቸው፤ አንዳንድ አገሮች በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ያካቱቱ ሲሆን ብዙዎች ግን በአዋጆችና ድንጋጌ ይከለክላሉ። ሌሎችን በማግለል በአንድ ማኅበረሰብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ፓርቲዎችን በመከልከል ጋና ቀዳሚ ስትሆን ዛሬ በኻያ ኹለት አገሮች ተመሳሳይ ክልከላዎች አሉ፤ እነዚህ አገሮች ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ብሩንዲ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋና፣ ጉየና፣ ኮትዲቯር፣ ኬንያ፣ ላይቤሪያ፣ ማውሪታኒያ፣ ናሚቢያ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ እና ቶጎ ናቸው። አንጎላ፣ ካሜሮን፣ ቻድ፣ ጋቦን፣ ማዳጋስካር እና ሞዛምቢክ ከላይኞቹ ያነሰ ግልጽነት ያለው ክልከላ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በላይቤሪያ የፓርቲ አባልነት ለሁሉም ፆታዎች፣ ለሁሉም እምነቶች ተከታዮችና ለሁሉም ዘውግ አባላት ክፍት እንዲሆኑ ሕግ ያስገድዳል። የፓርቲ አርማዎች ከሃይማኖትና ዘውግ መያያዝ አይችሉም፤ የፓርቲ ሹማምንትም በተቻለ መጠን የሀገሪቱን የዘውግ ስብጥር የሚያንፀባርቅ እንዲሆን ሕግ ያስገድዳል። የኮትዲቯር ሕገ መንግሥት በዘውግ፥ በቆዳ ቀለም፣ በክልል፣ በሃይማኖት እና በነገድ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ይከለክላል፤ የፓርቲ ሕጋቸው ደግሞ በተጨማሪ ፓርቲን በፆታ፣ በቋንቋና በሙያ ማደራጀት ይከለክላል።

‹‹እነዚህ ሕግጋት ምን ውጤት አመጡ?›› የሚለው ጥያቄ ሰፋ ያለ ምርምር የሚሻ ቢሆንም የሕግ ማዕቀቡ መኖሩ በራሱ እንደ አንድ መልካም ነገር መታየት ይኖርበታል። በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እነዚህ ሕግጋት ሦስት ጥቅሞች አሏቸው:- (1) እነዚህ ሕጎች በትክክል በሥራ ላይ ከዋሉ ጽንፈኛ ፓርቲዎች እንዳፈጠሩ ይከላከላሉ፤ (2) ከተፈጠሩም በሰላማዊ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ ቢያንስ ሰላማዊውና ሕጋዊው ፖለቲካ እንዳይቆሽሽ ይከላከላሉ፤ እና (3) በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ጽንፍ የረገጡ፤ ወይም የመረረ ብሶት ያላቸው ወገኖች ጥያቄያቸውን አቀዝቅዘውና አለዝበው እንዲያቀርቡ ያስገድዳቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ በነጻነት የመደራጀት መብቴን ተነጠቅሁ የሚል ወገን እንዲኖር ሊያደርጉ እንደሚችሉ መጤን ይኖርበታል።

የሕግጋቱ ተግባራዊ ፋይዳ በተመለከተ ወደፊት ልንመለስበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ለጊዜው ለአብነት ያህል ጥቂት ነገሮችን በዚህ ጽሑፍ ማንሳት ይቻላል። በ1991 (እ.አ.አ.) የተቋቋመው ለሁቱዎች ያደላ የነበረው የሩዋንዳው ሪፐብሊካን ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከፋፋይ ነው በሚል በ2003 በሕግ እንዲታገድ ተወስኗል። በ1990ዎቹ የኬንያ እስላማዊ ፓርቲ ምዝገባ በመከልከሉ የአገሪቱ ሙስሊም ፓለቲከኞች በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በሞውሪታኒያ ቀድሞ በባርነት የተገዙ ሕዝቦች የፖለቲካ ንቅናቄ ለመፍጠር በዘውግ ፓርቲዎች ላይ የተጣለው እገዳ ስለከለከላቸው ማዕከላዊ መንገድ ላይ ያለውን ”Parti du Centre Démocratique Mauritienin“ እንዲቀላቀሉ አደረጋቸው።በሶስቱም ምሳሌዎች ጽንፍ ሊሄዱ ይችሉ የነበሩ ፓርቲዎች ወይ ከፖለቲካ መድረግ እንዲወጡ ተደርጓል፤ አሊያም ከጽንፍ ወደ መሀል እንዲመጡ ተገደዋል።

የአገራችን የኢትዮጵያ ልምድ
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው እና አንዱ በሌላው ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ይደነግጋል። በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በፓርቲ አማካይነት በመሆኑ ይህ አንቀጽ 11 በተዘዋዋሪ የፖለቲካ ፓርቲ እና ሃይማኖት የተለያዩ አድርጎ እንደሚደነግግ ተደርጎ ሊተረጎም ይችል ይሆናል፤ ግልጽነት ግን ይጓለዋል፤ አሻሚ ነው።

ከዚህ የተዘዋዋሪ እገዳ ውጭ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በፓርቲዎች ላይ የጣለው አንዳችም እገዳ የለም። በዚህ ረገድ የ2012 ‹‹የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ›› ቁጥር 1162 ጥቂት እርምጃዎችን ወደፊት የተራመደ ነው። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1(ሐ) መሠረት አንድ ፓርቲ ‹‹የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ሥም፣ ዓርማ፣ የመለያ ምልክት፣ የመመስረቻ ጽሑፍ ወይም የመተዳደሪያ ደንብ በዘር፣ በሃይማኖት እና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ጠላትነት በዜጎች፣ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና በሕዝቦች መካከል በማስፋፋት ጦርነትና ግጭት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ወይም ሰዎችን በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በማንነት ላይ ተመስረቶ ከአባልነት ወይም ከደጋፊነት የሚያገል ከሆነ›› ቦርዱ በፓርቲነት አይመዘግበውም። ይህ ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ሲታይ አንድ እርምጃ ወደፊት ቢሆንም ከሌሎች አገሮች ሕግጋት ጋር ሲወዳደር ብዙ ይቀረዋል።

አዋጁ ምዝገባ የሚከለክለው ‹‹ጦርነትና ግጭትመፍጠርን ዓላማ ያደረገ›› ወይም ‹‹በማንነት ላይ ተመስረቶ ከአባልነት ወይም ከደጋፊነት የሚያገል›› መሆኑ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ጽፎ ሲገኝ ነው፤ ይህን ሳይጽፍ ተግባራዊ በሚያደርግ ፓርቲ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ግልጽ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ በማንነት ላይ ተመሥርቶ ፓርቲ ማቋቋም ተፈቅዶ እያለ በማንነት ላይ ተመስረቶ ከአባልነት ወይም ከደጋፊነት ማግለልን ሕገወጥ ማድረግ እንዴት ተጣጥመው እንደሚሄዱ ግልጽ አይደለም። ሕጉ ራሱ ከፀቀደ አጭር ጊዜ በመሆኑ አፈፃፀሙን መከታተል ያስፈልጋል።

ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ሕግ በዘውግ መደራጀትን አይከለክልም፤ እንዲያውም የመንግሥት አወቃቀሩ ለዘውግ ፓርቲዎች መበራከት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በአሁኑ ሰዓት ፈቃድ እንዳላቸው በምርጫ ቦርድ ድረገጽ ላይ ከተዘረዘሩ 51 ፓርቲዎች ውስጥ 18ቱ ብቻ ሀገራዊ ፓርቲዎች ናቸው፤ ከእነሱ ውስጥ 6ቱ በማያሻማ ሁኔታ የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው። ስለሆነም ሲቪክ ፓርቲዎች ይሆኑ ይሆናል ብለን ተስፋ ማድረግ የምንችለው በ12ቱ ብቻ ነው፤ የተቀሩት 39 ፓርቲዎች (76.5 በመቶ) የዘውግ ፓርቲዎች እንደሆኑ እንገነዘባለን። በዚህ ጽሁፍ በቀረበው ትንታኔ መሠረት ይህ ለሀገራችን ሰላምና ዴሞክራሲ የሚበጅ አይደለም።

ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ የምጣኔ ሀብት፣ የሰላም፣ ቅራኔዎችና ዲፕሎማሲ ጥናቶች ባለሙያ ሲሆኑ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ አገር፣ ለንደን ከተማ ነው። ታደሰን በኢሜል አድራሻቸው tkersmo@gmail.com ማግኘት ይቻላል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com