የእለት ዜና

የኢትዮ-ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር ሥራ ሲጀምር በወር እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል

መስመሩ ኢትዮጵያ ከኬንያ ኤሌክትሪክ እድታስመጣም የሚረዳ ነው

ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ እና ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተላለፍ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በአንድ ወር ውስጥ በአማካኝ ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይክተር ሞገስ መኮንን ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ እና ከኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተላለፍ የተዘረጋው መስመር አጠቃላይ 1 ሺሕ 68 ኪሎሜትር ያህል እርዝመት እንዳለው ገልጸው በኢትዮጵያ በኩል ያለው የመስመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል።

ኮሚኒኬሽን ዳይክተሩ ኃይል ማስተላለፊያው የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ወይንም ደግሞ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ማስተላለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል። የመስመር ዝርጋታው በኬኒያ በኩል ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ የምትልከው የኤሌክትሪክ ኃይል ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን እንደ አጋጣሚ ኢትዮጵያ በ 2011 ዓመተ ምህረት የገጠማትን አይነት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ካጋጠመን መስመሩ ከኬኒያ ኤሌክትሪክ እንድናመጣ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ 631 ኪሎ ሜትር የሚሸፍው በኬኒያ በኩል ያለው የመስመር ዝርጋታ ኬንያ ሰኔ ወር እንደምታጠናቅቅ ይገልጻል። በኢትዮጵያ በኩል ያለው 433 ኪሎ ሜትር ዝርጋታ ተጠናቆ ማለቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኬኒያ የመስመር ዝርጋታዋን አጠናቃ እንደጨረሰች ማስተላለፍ መጀመር እንደሚያችል አሳውቋል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2016 ተጀምሮ 2018 ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው ጊዜ መጠናቀቅ እንዳልተቻለ የኮሚኒኬሽን ዳይክተሩ ገልጸዋል። ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ በኩል ከዓለም ባንክ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 641 ሚሊዮኝ ዶላር የገንዘብ እርዳታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር 2 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸከም አቅም እንዳለው ሞገስ አሳውቀዋል። በአገራችን የሚገኙ ሁሉም የኃይል ማመንጫዎች የሚያመነጩት ኃይል ወደ አንድ አገር አቀፍ የኃይል ማጠራቀሚያ ቋት (National Greed) ከተጠራቀመ በኋላ ወደ ሁሉም ቦታዎች ይተላፋል ወደ ኬንያ ለመላክ የታሰበው እና ወደ ጂቡቲ እና ሱዳን እየተላከ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይልም ሆነ ለአገር ውስጥ የኢንደስትሪ ፍጆታ እና ለግለሰብ የሚተላለፈው የኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ አገራዊ የኃይል ማጠራቀሚያ ቋት እንደሆነ ገልጸዋል።

መስመሩ ተዘርግቶ ሥራ ላይ ባለመዋሉ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት የሥርቆት ወንል እንደተፈጸመበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስታወቁ ይታወሳል። የማስተላለፊያ መስመሩ 994 ምሶሶች ያሉት ሲሆን በተፈፀመው ስርቆት ጉዳት ከደረሰባቸው ምሶሶዎች መካከል አንዱን ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ድርጂቱ ገልጿል።

ከወላይታ ሶዶ የኃይል ማስተላለፊያ የሚነሳው ይህ መስመር አርባምንጭ፣ ኮንሶ፣ያቬሎ ፣እና ሜጋ ከተሞችን አቆራርጦ ያልፋል። በወላይታ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በማስተላለፊያ መስመሩ ሽቦዎች እና የምሰሶ ብረቶች ላይ በተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እየተፈፀመበት ይገኛልበዚህ ምክንያትም ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ በመዳረግ ከ34 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራም እንዳደረሰበት ታውቋል።

ኪሳራው የደረሰው በስርቆቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የማስተላለፊያ መስመሩን አካላት በአዲስ ለመተካት እና ለመቀየር፣ እንዲሁም ለመበየድ፣ ለዕቃ ግዥ እና ለምሶሶ (Tower) ቅየራ ተጨማሪ ወጪ በመውጣቱ እንደሆነም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለ4 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን 1 ሺሕ 600 ያህሉ ለኢትዮጵያዊያን ሲሆን 2 ሺሕ 400 ደግሞ ለኬኒያዊያን ነው ተብሏል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!