Views: 43

በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) የፖለቲካ ሕይወታቸውን የጀመሩት በሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርነት ነው፡፡ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን በብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣በውጪ ግንኙነት ኃላፊ በአሁኑ ወቅትደግሞ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በቃሉበትምህርት ዝግጅት በሥነ ትምህርት ዘርፍ ነው የፒኤች ዲ አላቸው፡፡
በባልደራስ ፓርቲ ለመግባት መነሻ ስለሆናቸው ምክንያት ሲገልጹ <ሰው እየሞተ፣ የሚሰሩ ኢፍትሃዊ እና ኢ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችን እየተበራከቱ ቆሜ እንድመለከት አእምሮዬ አልፈቅድ ስላለኝ ነው> በማለት ያስረዳሉ፡፡
በየትኛውም ዓለም ያልተፈጸመ ጉዳይ ነው አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠረ ያለው የሚሉት በቃሉ፤በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ አሰቃቂ ጥቃቶችን ያወሳሉ። ይህንን እና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታን በተመለከተ፤ እንዲሀም የባልደራስን ምሥረታን ጨምሮ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት ከአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ወቅታዊየአገሪቱን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
በአጠቃላይ ከስልሳዎቹ ጀምሮ የነበረው የኢትየጵያ ፖለቲካ በሸፍጥ እና በተንኮል የተሞላነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ንጹህ ሳይንስ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት የብሔርተኝነት እንቅስቃሴው ጥግ ደርሶ ከሰውነት ተራ ወጥተን አውሬነትባህርይ ደረጃ ላይ መድረሳችን እንደ አንድ ዜጋ፣ ያውም ፊደል እንደቆጠረ ሰው ዝም ብሎ ማየት ጥፋት ብቻ ሳይሆን ሃጢያትምወንጀልም መስሎ ሁላእየታየኝ ነው። በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚደርስን ማንኝውንም ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ነግ በኔ ብለን ሁላችንም ልንቃወመው ይገባል ብዬ አስባላሁ።

እኔ ወደ ፖለቲካው የገባሁት ሥልጣን ገንዘብም ፈልጌ ሳይሆን እንደዚህ ያሉ ኢ- ፍትሃዊ አሰራሮችን ለመዋጋት ነው። ዝም ማለት በራሱ ከአጥፊው ጋር እንደመተባበር ስለሚቆጠር ነው ወደ ፖለቲካው ዓለም በይፋ የተቀላቀልኩት።
ባልዳራስ አውነትን የያዘ ፓርቲ ነው ብዬ አምናለሁ። በርካታ ፓርቲዎች አቋም አጣባቸዋለሁ።ከዚያ በፊት ሰማያዊ ፓርቲ ነበርኩ። እንደምታውቀው ሰልፍ ተከልክሎ እንኳን መንግሥትን ተጋፍጦ ሰልፍ ይወጣ የነበረ፣ በደፋር ወጣቶች የተሞላ ስብስብ ነበር። ባልዳራስም እንዲሁ ነው።አሁንም ያሉትን ፓርቲዎች ስናይ ከሌሎች ጋር የማጎብደድ ነገር የለውም፤ እውነትን ይዞ የቆመ ፓርቲ ነው። ለዚያ ነው መንግሥትም ይህን ያህል ጥላቻና የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂድበት።

የፓርቲውን ፕሬዝዳንት እስክንድርን ስትወስድ በዚህች አገር የፓርቲ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ግለሰብ ነው። እርሱ ደግሞ ሐቀኛ፣ የማያወላዳ አቋም ያለው ሰው ነው። ስለዚህ እንደዚህ ያሉ ሀቀኛ ሰዎች በፓርቲው ውስጥ መኖር ፣ብልጽግናም በለው ሌላ ማንኛውም አካል ውስጥ ሰርጎ ገብቶ የፓርቲውን ውስጣዊ አንድነት ለመሸርሸር ቢሞክር እንኳን፣እንዳንበረከክ ይረዳል።

አሁን ያሉት ፓርቲዎችን ስትወስዳቸው አብዛኛዎቹ በገዢው ፓርቲ ድጎማ የሚፈለፈሉ ናቸው። ሊጠቀሱ ከሚችሉ አራት እና አምስት ፓርቲዎች መካከል ግን ባልዳራስ ሊጠቀስ የሚችል ፓርቲ ነው።ባልዳራስ ለማንም የማያጎበድድ ጠንካራ ፓርቲ ነው።

ባልዳራስ በስሜት የተመሠረተ እንጂ ታስቦበት የተመሠረተ ፓርቲ አይደለም ይባላል። እርስዎ ምን ይላሉ?
ስሜትየሚለው ሊገልጸው አይችልም፡፤ ምናልባት ከአክቲቪዝም ወደ ፓርቲነት የመጣ ነው የሚለው ግን በትክክል ይገልጸዋል።
ለውጥ መጣ በተባለ ጊዜ በርካታ ሰዎች ለዐቢይ አህምድ(ዶ/ር) ድጋፍ ነበራቸው።እርሱም ብዙም ሳይቆይ ወደ ብሔር ፖለቲካው ነው የገባው። ይባስ ብሎ በርካታ ሸፍጦች መሥራታቸውን ቀጠሉ። ለምሳሌ የዲሞግራፊ ቅየራውን ስትመለከት፣የመታወቂያ እደላውን፣ የመሬት እና የኮንዶሚንየም ዝርፊያውን እነዚህን ሁሉ ኢ- ፍትሃዊ ድርጊቶች ተፈጸሙ። አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከ15 ዓመታት በላይ ኮንዶሚንም የቆጠበ ዜጋ እያለ ምንም ለማያገባው ሰው ማደል ጤናማ አእምሮ የሚያስበው ድርጊት አይደለም። ስለዚህ እንደዚህ ያሉትን ኢፍትሃዊ ድርጊቶች በመቃወም እንደ አክቲቪዝም ሲሠራ የነበረ ድርጅት ነው። ይህን ሃሳብ ሊገዛለት፣ሊያጠነክርለት የሚችል ፓርቲ ማግኘት አልቻለም።ስለዚህ ለምን እንደ ፓርቲ አይመሰረትም ብለን ከአክቲቭዝም ወደ ፓርቲነት እንዲመሰረት ሆነ እንጂ በስሜት የተመሰረተ ነው ማለት ትክክል አይደለም።

አዲስ አበባ ላይ የተሠሩ የምትሏቸውን ኢ-ፍትሃዊ ሥራዎችን በዝርዝር ቢገልጹልን?
ባልደራስ በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራ የነበረውን አክቲቪዝም ቅርስ ማውደምላይ የተሠራውን ኢ ፍትሃዊ ሥራ፣ሕገ ወጥ የመታወቂያ እደላል፣የኮንዶሚንየም ዝርፊያን፣ የትምህርት ቤት ቅጥር ላይ የተሰራውን አድሏዊ የቅጥር ሁኔታ ማለትም ኦሮሚኛ መናገር አስካልቻልክ ድረስ መቀጠር አትችልም መባሉን ስንቱን እንጠቅሳለን።

በነገራችን ላይ እንደዚህ ያለው ጉዳይ ማግለል ነው።ኢ- ህገ መንግስታዊ ነው። በህግም ያስጠይቃል። የስራ ቋንቋ ተብሎ አዲስ አበባ የምንጠቀምበት አማርኛ ነው። ስለዚህ ኦሮሚኛ እስካላወቅክ ድረስ ሥራ አትቀጠርም ማለት ደቡብ አፍሪካ እና ሰሜን አሜሪካ ጥቁሮች እንቅስቃሴ ላይ ያየናቸው አድሎ እና መገለል መድገም ነው።ይህ በወንጀል ያስጠይቃል። በየመሥሪያ ቤቱ የኦሮሞ ተወላጆች ሆኑ ሰዎች ይቀጠራሉ።

እኔ እንደ ባልዳራስም ሆነ በግሌ ለምን ኦሮሞ ተወላጆች ተቀጠሩ እያልኩ ሳይሆን በእኩልነት እና በፍትሃዊነት መቀጠር አለባቸው ብዬ ስለማምን ነው። እንደዚህ ያሉ ኢፍትሃዊ አሰራሮች ከትህነግ ያለመማራቸውን ያሳያል። እነዚህ ጉዳዮች ነገ ዋጋ እንደማያስከፍሉ ማረጋገጫ የላቸውም።የሠራተኛ ቅጥሩንም ሆነ የኃላፊነት ቦታዎች ብንወስድ በኦሮሞ ተወላጆች እየተሞሉ ነው ያሉት።

በተጨባጭ ልክ ወያኔ ከ1997 በኃላ የሠራቸውን ሥራዎች ነው እየሰሩ ያሉት። 27 ዓመታት ያልተደረገ ድርጊት ነው በሦስት ዓመታት ውስጥ እየተደረገ ያለው። የኮንዶሚንየም እደላ፣ መሬት ዝርፊያ፣ መታወቂያ እደላትተን በማንነት መገደል እንኳን ብንወስድ አሳፋሪ ደረጃ ላይ ነው የደረስነው። በምድር ላይ የተፈጸሙ ዘግናኝ በደሎች ሁሉ በዚህ ሶስት አመት ውስጥ ተፈጽመዋል። ያልተፈጸሙ ነገሮች የሉም። መዘርዘር እንኳን አንችልም።

መንግሥት በባልዳራስ ፓርቲ ላይ በተለየ መልኩ በደል እየፈጸመብን ነው በማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስታነሱ ይሰማል፣በዝርዝር ቢያነሱልን?
ባልዳራስ ፓርቲላይ ጫና ለማድረግያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም። ዋና መነሻውባልዳራስ አዲስ አበባ ላይ ጠንካራ ተገዳዳሪ ስለሆነ ነው። የአገሪቱ 60 በመቶ የሚሆነው ገቢ የሚገኘው ከአዲስ አበባ ከተማ ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ ለገዢውም ፓርቲ ሆነ ለየትኛው ፓርቲ ቁልፍ ከተማ ነች። አዲስ አበባን መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ብቸኛ ፓርቲ ባልዳራስ ነው። ሌሎችን ፓርቲዎች ከጨዋታ ውጪ የማድረግ ወይም ወደ እነሱ የማስጠጋት ነገር ነው የሚታየው። ሌሎች ተለጣፊ ፓርቲዎችም አሉ። ባልዳራስ ግን መሪው እንኳን ታስሮ እየተንቀሳቀሰ ያለ ፓርቲ ነው።

ባልዳራስ እንደሌሎች ሸብረክ የሚል ፓርቲም አይደለም። ዋናው ግን በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያገባኛል ብሎ የተነሳ ተገዳዳሪ ፓርቲ በመሆኑ ብዙ ጫና እና ማስፈራሪያ እየደረሰበት ነው።ነገር ግን እስከ አሁን ሸብረክ ሳይል የቀጠለ ፓርቲ ነው።
ሌላው ባልዳራስ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚደርሰው እውነትን የያዘ ፓርቲ ስለሆነ ነው። ሌሎችን በተለያዩ ጥቅሞች ልትገዛቸው ትችላለህ። የእኛ ግን እንደዛ እንዳልሆንን መንግስትም ስለሚያውቅ ነው ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ያለው። ሆቴሎችን እንዳንገለገል ጭምር እያደረጉ ነው።

በውይይት የማይፈታ ወይም የማይወለድ ነገር የለም ብለን እናምናለን። ተመሳሳይ አቋም የሌላቸው ጽንፍ የወጣ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች እንኳን በአንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ ቁጭ ብለው የራሳቸውን አቋም አርቀው ከተወያዩ የማይደርሱበት ስምምነት የለም ብለን እናምናለን።

ለምሳሌ በ የ15 ቀናት በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ታዋቂ ሰዎችን በመጋበዝ ለመወያየት አስበን ሆቴል ፈልገን መንግሥት ሊፈቅድ አልቻለም።ባለፈው ሃርመኒ ሆቴል የተከለከልነውን ብናነሳ እንኳን ከሰላም ሚኒስቴር ደብዳቤ አምጥተን ጭምር ከመንግሥት በመጣባቸው ጫና የተነሳ ቦታ አለን ብለው ካስያዝን በኋላ እንዲሰረዝ ሆኗል።

እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን በተለይም ከምርጫ ጋር የተገኛኙ ጉዳዮችን ጭምር በፍትህ ተቋማት ለመፈተሽበማሰብ ፣ ፍርድ ቤት ወስደናቸዋል። ግን ምንም መልስ የለም። አስፈጻሚው እና የፍትህ አካላቱ ‹ኦልሞስት› የተሳሰሩ ናቸው።
በፍትህሥርዓቱ ውስጥሰዎች ተቀይረዋል። ለውጥ ግን አላየንም። የእስክንድር እስር እኮ አንዱ ማሳያ ነው። በምርጫ ቦርድ ላይ የምናነሳቸው ጉዳዮች ሌላው ማሳያ ነው።ምርጫ ቦርድ ላይ በርካታ ክፍተቶች አሉ። ለምሳሌ የምርጫ ጣቢያዎች ሲወሰኑ ምርጫ ቦርድ እና ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው የወሰኑት።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዚያ ላይ ሊወያዩ ይገባ ነበር። የምርጫ ክልል ሲዋቀር ምንም ድምፅ አልበረንም። ለምሳሌ አዲስ አበባ 23 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ወንበር እና 138 ለክልል ምክር ቤት ወንበር አሉ። 138 ክልል ምክር ቤት ወንበር እንዳለ ሆኖ የምርጫ ክልሉን ቀይረውታል።የተቀየረበት ምክንያት ገዢውን ፓርቲ እንዲጠቅም ተፈልጎ ነው።

ለምሳሌ አራዳ ክፍለ ከተማን ስትወስድ አራዳ ‹ኢነር ሰብሲቲ› የሆነ ቦታ ነው። ወደ ኦሮሚያ የተጠጋጉ ቦታዎችን ድምጽለማግኘት ሲባል የምርጫ ክልሉን የቀየሩት ሲያዋቅሩ ወደ ዳር ይጎትቱታል፣በዚህም መካከል ያለውን ድምጽ ለመዋጥ ያለመ ነው።
እንዳልኩህይሄ ደግሞ የትኛውንም ተፎካካሪ ፓርቲ ሳያማክሩ ምርጫ ቦርድ እና ገዢው ፓርቲ ብቻ የሰሩት ስራ ነው። እንኳን ውይይት የምርጫ ካርታውን እንኳን ስጡኝ ስትላቸው አይሰጡህም።

የምርጫ ቀኑን መወሰንን ብንወስድም ተመሳሳይ ቅሬታ ነው ያለን። የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ መስተዳደርን ምርጫ ሰኔ 5 እንዲሆን ነው የተወሰነው። የምርጫው ቀን መለያት የለበትም ብለን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ላይ አቅርበነዋል። መልስ አላገኘንም ።
ምርጫ ቦርድ ላይ አቅርበናል መልስ አላገኘንም። ፍርድ ቤት ላይ ሳይቀር ወስደነዋል መልስ አላገኘንም ። በእርግጥ ፍርድ ቤት የወሰድነው መልስ እናገኛለን ብለን ሳይሆን፣ ለአእምሮአችን ማድረግ ያለብንን ለማድረግ ብለን ነው።
የምርጫ አስፈጻሚዎችንም ብንወስድ የመንግሥት ሰራተኞችን ነው የመደቡት። እኛ ገለልተኝነታቸው ላይ ጥርጣሬ አለን። መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ማድረግ ይቻል ነበር። እነሱ ግን ከማእከላዊ ስታስቲክስ ነው የመለመሉት። ምርጫ አስፈጻሚው ከመንግስታዊ ተቋም ውጪ ቢሆን እንመርጣለን።

በምርጫ ቦርድ ላይ የምታነሷቸው በርካታ ቅሬታዎች እንዳሉ በተለያዩ መድረኮች ስታነሱ ይሰማል፣ ዋና ዋናዎቹን ቢጠቅሱልን?
በርካታ ናቸው። ለምሳሌ ፓርቲዎች ጥምረት እንዳይፈጥሩ ከፍተኛ ሴራ ነው የተሰራባቸው። የምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎቹ እውቅና ሰርተፊኬት የሰጡት ታህሳስ 6 ቀን ነው። ለውህደት ወይም ጥምረት ለመፍጠር የተሰጡት ቀናት 10 ብቻ ነበሩ። ጥምረት ወይም ቅንጅት ለመመስረት ደግሞ ውይይት ያስፈልጋል። ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህ ሆን ተብሎ የተሰራ ስራ ነው ብለን እናምናለን። ለዚህ ነው የዲሞክራሲ ተቋማት የሰው ለውጥ እንጂ የአሰራር ለውጥ የለም የምንለው።

የፍርድ ቤትን ጉዳይ ብትወስድ ተመሳሳይ ነው። በእነ እስክንድር ኬዝ ማየት ይቻላል።ፍርድ ቤቶች በዚህ ደረጃ ይወርዳሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር። ከዚህ በፊት ትህነግ መጫወቻ እንዳደረገው አሁንም መጫወቻ ነው ያደረጋቸው።ችሎት ሳይሰየም፣ የእነ አስክንድር ጠበቆች ሳይቀርቡ በመዝገብ ቤት ሰነድ ልውውጥ ብቻ የፍርድ ሂደት ይኖራል ብሎ ማሳብ በራሱ ከባድ ነው።

መዓዛ አሸናፊን፣ብርቱካን ሚደቅሳ እና ዳንኤን በቀለን( ዶ/ር) ብንወስድ እኔ በግለሰብ ደረጃ የማከብራቸው ሰዎች ነበሩ። ቦታው ላይ ከመጡ በኋላ ግን እንዴት ሆነው እንደሚቀየሩ አታውቅም። እኔ በጎሳ ፖለቲካ እና በዘር ማጽዳት ላይ ወረቀቶችን ጽፌያለሁ። በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ሁሉ ያሳተምኳቸው አሉ። ጀኖሳይድን በተመለከተ መሰረታዊ መስፈርቶች አሉ። የረቀቀ ሮኬት ሳይንስ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተፈጸመውን በማንነት ላይ ያተኮረ ግድያ እንዴት ጄኖሳይድ አይደልም ይባላል? ሻሸመኔ ፣ ዝዋይ፣መተከል እና አሁንም ድረስ እኔ እና አንተ እያወራና ባለንበትም ወቅት በወለጋ እየተፈጸመ ያለውን ብንመለከት አማራ፣አገው እየተባሉ አይደለም እንዴ ጥቃት እየደረሰባቸው ያለው? ድርጊቱ ከ 10 በላይ የጄኖሳይድ መስፈርቶችን ያሟላል።የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዴት እንዲህ ያለውን ተግባር ጄኖሳይድ አይደለም ይላል።

ጄኖሳይድ በባህሪው በመንግስት የሚደገፍ ነው፣ይህ መሆኑን የሻሸመኔ ላይ በደረሰው በማናነት ላይ በተፈጸመ ጥቃትየሻሸመኔ ከንቲባ ፍርድ ቤት የሰጡትን ምስክርነት ማንሳት ይቻላል።ከንቲባው ለኦሮሚያ ርእስ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ደውለው ዝም ብለህ ተኛ መባላቸውን ተናግረዋል። ይህ በመንግሥት ስፖንሰር የተደረገ መሆኑን ያመለክታል። ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት ስንመለከት ከጄኖሳይድ ውጪ ምንም ሊሆን አልቻለም። ጠቅላላ የአማራ ተወላጅ ማለቅ አለበት ጄኖሳይድ ለመባል ካልተባለ በስተቀር እንደዚህ ያለውን ተግባር ጄኖሳይድ አይደለም ማለት በጣም ነው የሚያሳፍረው።

ስለዚህ እንደ ባልዳራስ ጄኖሳይድ ተፈጽሟል ብለን አስረግጠን መናገር እንችላለን። እስክንድርም አስቀድሞ ይሄ ነገር ሊፈጸም እንደሚችል ተናግሮ ነበር። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት አሉ። ደግሞም የጄኖሳይድ ድርጊት ይርጋ እንኳን አይገድበውም። እነዚህ ሰዋች ከስልጣን ከወረዱ በኃላ ኬዙን ማንሳት ይቻላል። ያ ደግሞ መደረግ አለበት። ቀጣዩ ትውልድም ለፍርድ ማቅረብ አለበት ብለን እናምናለን ያን ደግሞ ጊዜም ይፈርዳል።

ባልዳራስ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ነው ይባላል።ይህ ወግ አጥባቂነቱ አሁን ዓለምከደረሰበትአስተሳሰብ ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል? አይቸገርም ወይ? የሚሉ ሰዎች አሉ። ምን ይላሉ?
ወግ አጥባቂነት እውነትን ማንነትን እና ባህልን ከመጠበቅአንጻር ከሆነ ተገቢ ነው። በፖለቲካውም ከሆነ እውነትን ከያዙ እና በኢትዮጵያ አንድነት ከማይደራደሩ ፓርቲዎች ጋር በወግ አጥባቂነት እንሰራለን ። ቅንጅት ፈጥሮ በአንድነት መስራት አይችልም ወይም አይፈልግም ከተባለ ግን ስህተት ነው።

ባልዳራስ እኔን ብቻ የሚል ፓርቲ አይደለም። ከማንም ጋር ተባብረን መስራት አንችላለን። ከአብን ጋር በነበረን ግንኙነት እና ተናብቦ በመስራታችን ሰው ይገረማል። ከአብን ጋር አይደለም በኢትዮጵያ አንድነት እና በሕዝብ ጥቅም ከማይደራደሩ፣በእኩልነት እና በፍትሃዊነት፣በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚያምኑ ፣ከማንኛውም ድርጅቶች ጋር አብረን መስራት እንችላለን። ሄዶ መለጠፍን፣ማጭበርበርን እና ማጎብደድን ላይ ግን ወግ አጥባቂ ነን። ፖለቲካ ማመቻመች ይፈልጋል ቢባልም አቋም ግን ሊኖር ይገባል ብለን እናምናለን።

በአዲስ አበባ ራስ ገዝ መሆን አለባት የምትሉት ለምንድነው
አዲስ አበባ የኔ የምትላት ከተማ አይደለችም ከኢትዮጵያም ዋና ከተማነት አልፋ የአፍሪካ መዲና ሁሉ ናት ። ስለዚህ አዲስ አበባ የሁሉም ከተማ ነች ብለን ነው የምናምነው። አዲስ አበባን ለአንድ ብሄር ወይም ነገድ መስጠት ተገቢ ነው ብለን አናምንም። በዚህ ጉዳይ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠርተን እንወያይ እና የጋራ አቋም እንያዝ ብለን ከአብን በስተቀር የመጣ ፓርቲ የለም።

የህዝቡ ድምጽ እንዳይከፋፈል ምን ስትራቴጂ አሏችሁ? ምን ለማድረግ አስባችኋል?
የህዝብ ድምጽ እንዳይከፋፈል ከፓርቲዎች ጋር ብንሰራ በወደድን ነበር ግን ብዙዎቹ ፓርቲዎች እንኳን በዚህ ጉዳይ ይቅር እና በአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጥያቄ ላይ እንኳን ለመወያየት ፈቃደኛ አይደሉም። ከአብን እና ከመኢአድ ጋር ግን ፖለቲካዊ ጥምረት ፈጥረናል። ሕጋዊ ሰርተፊኬት ባይኖረንም ጋር ግን ስምምነቱ አለ። ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረትን እና ቅንጅት ፈጥረን ተገዳዳሪ ሆነን ብንወጣ እሰየው ነው።

ባልዳራስን ስንመሰርት ለአገር እና ለህዝብ ጥቅም በማሰብ የተቋቋመነው እንጅ ለግል ጥቅም ታስቦ የተመሰረተ አይደለም። የአገርን ጥቅም የሚያስቀድም ማንኛውም ፓርቲ ዛሬም ድረስ አብሮን ለመስራት ቢመጣ እኛ ዝግጁ ነን። ከምርጫ በኃላም እንኳን ቢሆን አብሮ ለመስራት ፈቃደኞች ነን። ግን ብዙዎች ገዢው ፓርቲ ጥላቻ ስለሚቀባን አብሮ እኛ ላይ ለመዝመት ይነሳሉ አንደዚህ ያለው አካሄድ ግን የትም አያደርስም።

ከመኢአድ እና ከአብን ጋር ያላችሁ ያላችሁ ግንኙነት ምንድነው?
ከመኢአድ ጋር ያለው ብዙም አልሄድንበትም። ምክንያቱም የአብን እና የመኢአድ ፍላጎት አብሮ መሄድ ስላልቻለ።አብን ግን ትልቅ ፓርቲ ነው። እሱንም ከባልዳራስ ጋር በፈጠረው ፖለቲካ አልያንስ መረዳት ትችላለህ።
አዲስ አበባን ባልዳራስ የተሻለ ብራንድ አለው ብሎ ለቀቀልን። ይሄንን ማንም ማድረግ አይችልም፣ የትኛውም የብሄር ፓርቲ ይህንን አያደርግም። ከመኢአድ ጋር ያለው ጉዳይ ሰርተፊኬት ላይ ነበር ትኩረት ያደረግነው በምርጫውም የአዲስ አበባ ላይ የራሳቸው ተወዳዳሪዎች አቅርበዋል። የአብንን ያክል ተገዳዳሪ ናቸው ብለን ስለማናምን ብዙም አያሳስበንም። አዲስ አበበ ላይ ሊገዳደር የሚችል ኢዜም እና አብን ነበር አብን ለቅቆልናል።

ስለምርጫ ዝግጅታችሁ ትንሽ እናውራ
አዲስ አበባ ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት 23 ተወዳዳሪዎችን ፣ለክልል ምክር ቤት 137 ተወዳዳሪዎችን አቅርበንል አንድ ተወዳዳሪ በመታወቂያ ችግር የተነሳ የምዝገባው ጊዜ አልፎብን ሳናቀርብ ቀርተናል። በተረፈ አዲስ አበባ ላይ ምርጫውን እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com