ደሃ ሉዓላዊነት የለውም ወይ?

Views: 87

ኢትዮጵያ አንድ ነገር በገጠማት እና ችግሯ ዘለግ ላለ ጊዜ በቆየ ሰዓት ከኢትዮጵያ ጎን ከመቆም እና ኢትዮጵያ ከችግሯ ተላቃ በተስተካከለ ቁመና ላይ እንድትቆም ከመደገፍ ይልቅ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በሚመስል አኳኋን ተጨማሪ ጫና ሲፈጥሩ እና ሌላ ራስ ምታት የሚሰጡ አገራት ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። ያኔ በ‹ሊግ ኦፍ ኔሽን› ብቻቸውን ቆመው ሲናገሩ በብዙኀኑ የተጮኸባቸው የኢትዮጵያ ንጉሥ ዛሬም በቤት ሥራችሁ ውስጥ ገብተን ካልፈተፈትን በሚሉ አካላት ጫናዎች አላባሩም። ድህነታችን የማይደበቅ እና ዕሙን ቢሆንም ነገር ግን ድሃ የራሱ ሆነ ሉዓላዊነት እንዳለው ግን ሊታወቅ እንደሚገባ የረሱትን ማንቂያ ጽሑፍ ቀርቧል። ይህም የታሪክ ድርሳናት እና የቅርብ ክስተቶችንም ለማጣቀስ የተሞከረ ሲሆን በተለይም ደግሞ የአገርን ሉዓላዊነት በገንዘብ እና በእራፊ ጨርቅ ለመድፈር የሚሞክሩትን በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንዴት መባል እንዳለባቸውም ተቀምጧል።

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የዓለም አቀፍ አገራት እና ታላላቅ እርዳታ ሰጪዎ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየገቡ ሲያስጨንቁ እና መላ ቅጥ ያጣ መንግሥታዊ አስተዳደራቸውን በውዥንብር የተሞላ በጫና የተወሳሰበ ሲያደርግባቸው ከባድ ማስጠንቀቂያ እና ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን አስታውሳለሁ። እንዲያውም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ‹‹ለጋሽ አገራት ወዳጅነታቸውን አክብረን መቆየታችን በራሱ ሚያስመሰግነን ጉዳይ ሆኖ ሳለ በውስጥ ጉዳያችን ላይ ገብተው ለመፈትፈት የሚያደርጉት እንቅስቃሴን በተመለከተ ግን ገንዘባቸውን በኪሳቸው አድርገው ከፊታችን ዞር እንዲሉ እንነግራቸዋለን›› ሲሉም ተደመጡበት ወቅትን ዛሬ የተደረገ ያህል በዕዝነ ሕሊና ለማስታወስ ሕያው ነኝ።

ድህነት ድምጻችንን የነጠቀን፣ ችግር ወኔያችንን የሰለበን መስለን ኮስሰን የታየን ሕዝቦች አይደለንም። እውነት ነው በአገር ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት እና የስራ አጥነት ቁጥር መንግስት ከሚለው በእጅጉ የተለየ መልክ ይዞ ነው የሚገኘው። እዚህ ላይ አንድ ነገር እናንሳ። ባለፈው በጀት ዓመት ላይ የቀድሞው (መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዘመን የቀድሞ በመባል የሚጠራ የመንግስት ሹም ያለ አይመስለኝም) ታዲያ የቀድሞው ስራ ፈጠራ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ አገራችን ሦስት ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሏን ይፋ አደረጉ።

አቤት በወቅቱ የነበረው ሽሙጥ እና የጎራ ልዮነት መቼም ለጉድ ነበር። እንዲያው ያው ባለአዕምሮም አይደለን፤ መቼስ መጠየቃችን አይቀርም ለመሆኑ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ስራ ዕድል ያውም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አገርን እና ዓለምን ዘቅዝቆ ባራገፈበት ወቅት እንዴት ነው ስራ ፈጠራው የተሳካው የሚል ጥያቄ ብንጠይቅም ምላሽ የሚሰጠን ሳይሆን ጥግ ይዞ ስድብ የሚተኩስብን ሰው ነበር የታዘዘልን።

የዓለም ቁጥር አንድ ምጣኔ ሀብት ከእኔ ውጪ ማንም ጋር አይደለም የምትለው ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ እንኳን የስራ ዕድል ልትፈጥር በተባለው ዓመት በኮሮና ክፉኛ ተጎሽማ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ እንኳን ፕሬዘዳንት ቀየረች እንጂ የስራ አጥ ቁጥሯን ወደ መልካም አልቀየረችም። ታዲያ የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራው ቁጥር አስደንቆን ‹‹ይህቺ ተአምረኛ አገር›› በሚል የተደነቅን እንዳለንም እዚህ ላይ ይሰመርልን። የሆነው ሆኖ ታዲያ በኢትዮጵያ ላይ የውስጥ ጉዳዮች አሁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባሳቸውን እንጂ መቀነሳቸውን አናይም። የተፈጠረው የስራ ዕድል ሰፈር ውስጥ ተቀምጦ ክፉ ክፉውን ሲያስብ የሚውለውን ወጣት ለውጦ አምራች ኃይል ካላደረገ ምኑ ላይ ነው የቁጥር ጋጋታው ጠቀሜታ ነው ዋናው። ይሁን ግድለም ብለን ብንቆይም ከታዲያቁጥሮች ድህነታችንን ለመቀነስ ጉልበት አጥተው የማንም መፈንጫ እና መጫወቻ እንድሆን ሊያቀርቡን ሲሉ እረ እባካችሁ ደሃም እኮ ሉዓላዊ ነው፤ ደሃ አገራትም ለሉዓላዊነታቸው ተከፈለላቸው ከባድ መስዋዕትነት አላቸው እያልን እንገኛለን።

በነገራችን ላይ ከፈረንጆች 1960 (የአፍሪካ ዓመት ተብሎ የሚጠራው) ጀምሮ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከቅኝ ግዛት የተላቀቁበት ዘመን ጀምሮ አፍሪካዊያን አገራት እዚህ ግባ የማይባል የራስን ጉዳይ ወይም ችግር በራስ የመፍታት ችሎታ ሲያደርጉ አይስተዋልም እንዲያውም በአመዛኙ ራሳቸውን ችግር መፍታት አይችሉም ቢባልም የሚቀል ነው። ይህ ባለመሆኑ መክንያት ደግሞ ተላቀነዋል ያሉትን የቅኝ ግዛት ሕይወት በሌላ መልክ አብሯቸው ሲኖር ወይ አልተረዱትም አልያም ደግሞ ተረድተውት የቅኝ ግዛቱ አዲሱ መልክ ተስማምቷቸዋል ነገር ግን ሉዓላዊነታቸው በማንኛውም ሰዓት እና ጊዜ ሲጣስ (ብዙ ጊዜ በአውሮፓዊያን እና በአሜሪካ ነው) ሀይ ባይ አለመኖሩ እባካችሁ ደሃስ ብንሆን ሉዓላዊነታችንን ሸጠን የምንጎርሰው ምግብ ከጉሮሮ ይወርዳል ወይ የሚስብልም ነው።

ይህ አፍካዊያንን አገራትን በተናጠል አነሳን እንጂ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረው የአፍሪካ ሕብረትስ ቢሆን በተባበረ ክንድ ድህነትን ከአህጉሪቱ ማስወገድ ቢያቅተው እንኳን የአባላት አገራቱን ሉኣላዊነት በጥቂት የምእራባዊያን አገራት ሲደፈር እንዴት ነው የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ የቆየው የሚለው ጥያቄ በእጅጉ ሊነሳ የሚገባበት ጉዳይ ነው። አፍሪካ አገራት ውስጥ መፈንቅለ መንግስት ሲካሔድ፣ ዕርስ በርስ ጦርነት ሲከሰት፣ ዜጎች ሲፈናቀሉ እና ጎራ ላይተው በሳንጃ ሲሞሸላለቁ ምዕራባዊያን ቀድመው መጮህ ሲጀምሩ አፍሪካዊው ዕድሜ ጠገብ ሕብረትም በእርጅና ምክንያት ከተጫጫነው እንቅልፍ ብንን ብሎ ቀድሞ የተጮኸውን ጩኸት ሲያስተጋባው እንመለከታለን። እንዲያው አንድ ታሪክ እናንሳ እና ከዛም ደግሞ ወደ አገራችን ጉዳይም አያይዘን አንነጉዳለን። ከቅርብ ዓመታት በፊት በእኛዋ የጥንታዊ እስላማዊ ከተማ ሐረር ዕኩል የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገርም የማሊዋ ቲምቡክቱ ግዛት እንዲሁ ዕድሜ ጠገብ እና በሐረር ዕድሜ የምትገኝ የጥንታዊ ስልጣኔ መሰረትም መሆኗን ታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ በውስጧም የያዘቻቸው ጥንታዊ አፍሪካዊ እስላማዊነትን የሚያስታውሱ ቅርሶች ሕያው ምስክር ሆነውላት ቆመዋል።

ታዲያ ይህቺን ጥንታዊ ምእራብ አፍሪካዊት አገር የምእራብ አፍሪካ የአልቃይዳ ክንፍ ነው የሚባለው እና ቀጠናውን በከባድ ሁኔታ የሚያምሰው ቦኮሐራም የተሰኘው የአክራሪዎች ቡድን ለታሪክ ማጣቀሻነት እና ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ቲምቡክቱን የማፈራረስ ተልዕኮውን ለመፈጸም ይሰማራል፤ በርካታ ጥንታዊ የኪነ ሕንጻ ጥበቦችን የያዙ ሕንጻዎችን በአንድ አዳር ማፈራረሱም ሚታወስ ነው። ይህን ጊዜ ታዲያ ከጎረቤት አገራት እነ አልጀሪያ፣ ኒጀር፣ ኮቴዲቮር ይልቅ አውሮፓዊቷ እና ቀድሞ ማሊ ቅኝ ገዢዋ አገር ፈረንሳይ ነበረች በፍጥነት ጦሯን አዝምታ በስፍራው የተገኘችው።

የፈረንሳይ ጦርን ወደ አገሯ እንዲገባ በእርግጥ ማሊ ፍቃዷ ነበር ወይ የሚለው ጉዳይ በስፋት ሲያከራክር የቆየ መሆኑም የሚታወስ ሲሆን፤ ፈረንሳይስ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አሁንም አልተላቀቅችም ወይስ አሁንም ማሊን በይፋም ባይሆን በተዘዋዋሪ ቅኝ ገዝታ እያስተዳደረቻት ነው ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል። የወቅቱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ኒኮላስ ሳርኮዚም ጉዳዮን ይፋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አድበስብሰው ማለፋቸው እውነትም ፈረንሳይ የማሊን ሉዓላዊነት ጥሳ ወደ ግዛቷ ባሻት ሰዓት እና ጊዜ ለመግባቷ እውነትም ደሃ ሊዓላዊ አይደለም የሚስብል ነው ብንል ታዲያ ይፈረድብን ይሆን?

ገንዘብ እንሰጣችኋላን ነገር ግን የስራ ዕቅዳችሁን ስጡን እና እኛ በምናስቀምጠው መንገድ ነው የምትመሩት አይነት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ሲተገብሩ ኖሩ አገራት ዛሬም በአፍሪካ እና በአፍሪካዊያን ሕይወት ላይ አዛዥ ናዛዥ ናቸው።
በይፋ ሲያስፈልጋቸው ተራ ስድብ ሲሰድቡ፤ በል ሲላቸው ደግሞ ፊታቸውን ባጠቆሩበት አፍሪካዊ አገር ላይ መፈንቅለ መንግስት አካሂደው የራሳውን አምሳያ አመራር ሲያስቀምጡ የምናስተውለው ጉዳይም ነው። እንዲያው አንድ ጉዳይስ እንዴት ይረሳል ጎበዝ? አራቱን ዓመት ስልጣን ዘመናቸውን በውዝግብ ያሳለፉት እና በኋላም የዲሞክራሲ መብቀያ ነኝ የምትባለውን አሜሪካን ከከብሯ አውርደዋታል ተባለላቸው እና በስተመጨረሻም የስልጣን ዘመናቸው በአወዛጋቢ ሆኔታ የተጠናቀቀው ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካን እንደ አሕጉር የቆሻሻ ጉድጓድ ሲሉ መዝለፋቸውን በሰማን ጊዜ ዘራፍ ብለን ባገኘነው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ብንጽፍም ባለከዘራው አፍሪካ ሕብረት ምን ያለ ይመስላችኋል? ከብዙ ጉትጎታ በኋላ እጅ እግሩ የማይለይ የውግዘት አይሉት የመከላከል ብቻ ድብልቅልቅ ያለ መግለጫ በማውጣት ፕሬዘዳንቱን እና ንግግራቸውን አውግዘዋል ለመባል ብቻ ይስሙላውን ሞልተውት ነበር።

እባካችሁ ደሃ ሉዓላዊ ነው ብንልም ባክህ ከሉዓላዊነታችሁ በፊት በቀን ሦስቴ ለመብላት ጥረት አድርጉ አይነት ምላሽ አገራችን ውስጥ ካሉትም ሆነ በውጭ አገራት ከሚገኙ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካላት ዘንድ ይመለስልናል።
በነገራችን ላይ አወዛጋቢው ፕሬዘዳንት አፍሪካን እንዲያ በጅምላ ሲወርፏት ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ወደ ቢሮ በመጥራት ያለውን ጉዳይ እንዲያስረዱ እና ፕሬዘዳንታቸው የተናገሩትን ጉዳይ እንዲያብራሩ ማድረጓን ሰምተንም ጎሽ ቢያንስ ከሕብረቱ አገራት እንደግል ጠንካራም ናቸው ብለናል። እውነት ነዋ! የአክሱምን ስልጣኔ እያወራን፣ ላሊበላን ጥበብ እየጠቀስን፤ የንጉስ ጦናን ብልጠት እየዘከርን የገዳን ዲሞክራሲያዊነት እና ቀደምትነት እያስጎበኘን አንድ ትናንት ተፈጥራ የዓለም ቁንጮ በመሆኗ ምክንያት ልትዘልፈንማ አይገባም በሚል ይመስለኛል በኢትዮጵያዊነት ወኔ የኢትዮጵያ መንግስት አንከብክቦ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን ወደ ውጭ ጉዳይ የጠራቸው።

መያዶች ያሉባቸው እና በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸው አገራት በባሰ ድኅነት ውስጥ ይኖሩ እንደሆነ እንጂ ጠቀሜታቸው የጎላ እንዳልሆነ መቼም የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመያዶች (መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) ዕርዳታ እና ድጋፍ ያደገ አገር አለመኖሩን ራሷ አሜሪካ ምስክር ናት።

ከፍተኛ የመያድ ቁጥር ያለባት አገር ብትኖር አሜሪካ ናት በውስጧም እስከ ቅርብ ጊዜ በተሰራ ጥናት መሰረት 1 ሚሊዮን መያዶች ይገኛሉ። እንገዲህ ይታያችሁ አገሪቷ ካላት ጠንካራ ምጣኔ ሀብት አቋም ጋር ተደምሮ ይህን ያህል ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች መኖራቸው በራሱ ምን አይነት ለውጥ ለዜጎች ሊመጣ እንደሚችል መቼም መገመት አይከብድም። ነገር ግን አሁንም በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ካርቶን አንጥፎ እና ደበሎ ለብሶ የሚተኛው ሕዝብ ቁጥር መሽቶ በነጋ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ይህም ደግሞ ከፈረንጆች 2007 ጀምሮ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣት በ2019 ላይ በተደረገ ጥናት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዙጎች አሜሪካ እንዳሏት ለማወቅ ተችሏል።

እንግዲህ ይታያችሁ እነዚህ መያዶች በአገራቸው እንዲህ ከአቅም በታች እየሰሩ በቆዳ ቀለም ለማንመስላቸው እና በመልክዓ ምድር ለማንዋሰናቸው ለእኛ ደግሞ በበጎ ስራ ላይ በንጹሕ አገልግሎት ይሰማራሉ ብሎ መጠበቅ ትንሽ የሚያከራክር ጉዳይ እንደሆነም እረዳለሁ። ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሕወሓት አመራሮች ላይ የተካሔደው እርምጃን በሚመለከት በርካታ የዕርዳታ ድርጅቶች ወይ በጉዳያችሁ ላይ ጣልቃ ገብተን እንፈትፍት ወይም ደግሞ ከእኛ የምታገኙትን ድጋፍ ተሰናበቱት የሚል ኹለት የማይመረጡ አማራጮችን ለማቅረባቸው መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ በፊት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ክልሉ ክፍት እንዲሆን መንግስት ላይ ጫና ሲያደርጉ ነበሩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችን ምናስታውሰው ጉዳይ ነው። ይህንንም ተከትሎ መንግስት በችኮላም ይሁን አስቦበት ለሰብኣዊ እርዳታ ክፍት ማድረጉን ተከትሎ የእርዳታ ተሸከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው ስፍራ ውጪ ለመጓዝ ጥረት ሲያደርጉ እንደተያዙ እና እንዲያውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በተባበሩት መንግስታት ተሸከርካሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ይፋ አድርጎ እንደነበር እናስታውሳለን።

ይህን ተከትሎም ወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለሰብኣዊ እርዳታ አድራሽነት ወደ ክልሉ የገቡት ድርጅቶች ጥቂቶች ተፈላጊ ሰዎችን ለማሸሽ እና ደብቆ ለማውጣት ሙከራ አድርገዋል የሚሉ መረጃዎችም ወጥተው አጀብ አስብለውናል። ለዚህ እኮ ነው መጀመሪያ ላይ ስንጀምር የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር ከዓመታት በፊት ያደረጉትን ንግግር የተጠቀምነው፤ ረድኤት ድርጅቶች ኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ድህነት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም እና እርዳታዎችን እናቆማለን በሚል ማስፈራሪያ በውስጥ ጉዳይ እንግባ የሚሉትን ደሃም ቢሆን ሉዓላዊ ነው እና ገንዘባችሁን በኪሳችሁ አድርጋችሁ ከፊታችን ዞር በሉ የሚል ወኔ ነው ሚያስፈልገን።

ለመሰነባበቻ የሚሆን ሰሜን አፍሪካዊቷን የጋዳፊን አገር ሊቢያን ንስተን ጉያችንን እንቋጭ። እኔ በግሌ የሊቢያን ሕዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ምነው ሰከን ብለው ቢያስቡበት ስል ነው የከረምኩት ያኔ አፍሪካ ሕብረት አድባር የነበሩትን ኮሎኔል ሞሐመድ ጋዳፊን ከስልጣን ባስወገዱበት ወቅት። መቼም እንደምናውቀው አወዛጋቢነታቸው እና በተለይም ደግሞ ለምዕራባዊያን ያላቸው ንቀት እና ትችት የምናውቃቸው ግለሰብ ከምዕራባዊያን እንደመራቃቸው እና እንደመቃረናቸው አገራቸው ልዩ በሆነ ሁኔታ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የበርካታ አውሮፓ አገራት ምጣኔ ሀብትን የሚገዳደር እና የሚያስከነዳም ነበር።

ሊቢያ ምንም አይነት ዓለም አቀፍ ብድር ሌለባት አገርም ነበረች። የዜጎች ተጠቃሚነትን በሚመለከትም መላው አፍሪካዊ የሚቀናባቸው የዜጎች ከመንግሥት የሚበረከትላቸው በረከቶች አፍሪካ ውስጥ ብቻም ሳይሆን በበቁ አገራትም ማይተሰብ እንደነበር የጋዳፊ አረንጓዴ መጽሐፍ ማገላበጥ በቂ ነው። የሆነው ሆኖ ገና ድሮ አፍሪካ እና ድህነትን ነጣጥለው ማየት የተሳናቸው ዓለም አቀፍ አካላት ደሃ ሉዓላዊነት የለውም አካሔዳቸውን በሊቢያ በኩል ተግባራዊ አድርገው ይኸው አገሪቷን አፍርሰዋታል።

እጃችሁን ሰብስቡ ማለት ያቃተው የአፍሪካ ሕብረትም በሊቢያ ጉዳይ አንደበቱን ለማላቀቅ ረጅም ጊዜያትን አይቶ ለጋሽ አገራት በል ያሉትን እያለ አህጉሪቱን በራሷ እንዳትቆም ሆናለች። ይሁን እና የሊቢያን ጉዳይ አፍሪካዊ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ መፈንቅለ መንግስት ነው አይደለም የሚለውን ጉዳይ እንኳን አሜሪካንን አቋም አይቶ የወሰነው አፍሪካ ሕብረት አንዲት ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ያላትን አባል አገር ማጣቱን የተገነዘበ አይመስለኝም። በአሁኑ ሰዓት ሊቢያን ሚያስተዳድረው መንግስት ቢሊዮን ዶላሮችን ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች መበደር ወይም እንዲያበድሩት ሉዓላዊነቱን ለድርድር ማቅረብ ይኖርበታል ምክንያቱ ደግሞ አገር ለማቆም እና የተድበሰበሰችን አገር ለመምራት።

ደሃ ሉዓላዊ ነው፤ ደሃ አገራት ለሉዓላዊነታቸው ከፈሉት ገንዘብ ሳይሆን ውድ ዜጎቻቸውን ደም ነው እና እባካችሁ ደሃዎች ነን አውነት ነው ግን ደግሞ ሉአላዊነታችንን ለማንም የማናቀርበው እና በምንም የማንስማማበት ውዱ አንጡራ ሀብታችን ነው። እንዳልኩት ሉዓላዊነት የሚገኘው በብጣሽ ጨርቅ ወይም በፍርፋሪ ሳይሆን በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን የሰውን ሕይወት ተገብሮ ነው። በመሆኑም ድህነታችን ሉዓላዊነታችን እንዲደፈር የሐር መንገድ ሊሆን አይገባል፤ ደሃም ሉዓላዊ ነው።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com