በኢትዮጵያ የሴቶች ምርጫ ተሳትፎ የጨረፍታ ምልከታ

Views: 126

ይህ ‹‹ማለዳ ምርጫ›› ገጽ በግንቦት 28 እና ሰኔ 5/2013 በኢትዮጵያ የሚካሄዱት አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እንዲሆን የተረጋገጡ ምርጫ ነክ መረጃዎችን፣ ትንተናዎችን፣ ቃለ ምልልሶችን እና ጠቃሚ መረጃዎች የሚቀርቡበት ሲሆን ከኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፋ አማካኝነት ይቀርባል። ኅብረቱ በሰብኣዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ በሚሠሩ 12 የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶችን በሥሩ አቅፏል።

በዚህ ገጽ ላይ የተካከተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ በእጅጉ የተገደበ ነው። ታዲያ ይህ ችግር የተጠናወታቸው የፖለቲካ ዋና ተዋናይ የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ሴቶችን በፖለቲካ አመራርነት ቀርቶ በአባልነት እንኳን ሳያካትቱ መጓዝ የተለመደ ሆኗል።
ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሴቶች የተፈቀደ ሳይሆን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የተገደበ መሆኑን ለመታዘብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለሴቶች የሰጡትን የአመራር ቦታዎች ብቻ መመልከት በቂ ነው። በዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታም ቢሆን ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ መሆኑ ዓለም የሚያቀው ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ ታዲያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማነስ የሴቶች የመፈጸም ወይም የአመራርነት አቅም ማነስ ይሆን የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ይህ ሲባል ግን በዘመናት መካከል በርግጥ የተወሰኑ ለውጦች የሉም ማለት ግን አይቻልም።

የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ጎልቶ ሲፈተሸ፣ በዓለም ዐቀፍ ም ሆነ በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ተሳትፎቸው በቅደም ተከተላቸው ተሳትፏቸው እየቀነሰ ሲመጣ እናያለን። በጣት የሚቆጠሩ ብቻ በፖለቲካ ተሳትፏቸውና በአመራር ብቃታቸው ሚዛን ደፍተው ወደ ፊት ብቅ ሲሉ ያታያሉ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ፓርቲ መሪነት ላይ የሚገኙ ብቸኛዋ ሴቷ የፖለቲካ መሪ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር ቆንጂት ብርሃኑ ናቸው። ቆንጅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳታፊ መሆን የጀመሩት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲሆን ይሁንና ባለፉት አምስት አገራዊ አጠቃላይ ምርጫዎች ላይ ግን መሳተፍ እንዳይችሉ ፓርቲያቸው አገር ውስጥ ገብቶ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በመከልከሉ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካና ሴቶች ምንና ምን?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቀደሙት ጊዜያት ሲዳሰስ የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካው ሲነሳ ‹‹የሴቶች የመሪነት ተሳትፎ ወርቃማ ዘመን›› ተብሎ የሚወሳው አንድ ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ መጓዝ ግድ ይላል። የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና መሪነት አርዓያ ሆነው ሁል ጊዜ የሚታወሱትን የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱን ነው።

ታዲያ የእነዚህ በታሪክ ሲዘከሩ የሚኖሩ ሴት መሪዎችን ላሰበ፣ ሴት ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ምድር በአሁኑ ጊዜ ለምን ማግኘት ተሳነን የሚል ጥቄያ ለማንሳት ያስገድዳል።
የኢሕአፓ ሊቀመንበሯ ቆንጅት፥ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ውስንነት በኢትዮጵያ የቀነጨረ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ቆንጅት እንደሚሉት፥ በአጠቃላይ በዓለምም ይሁን በአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆኑንም ግን አልዘነጉም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና የመሪነት ሚና ውስን የሆነው ከቀደሙት ዘመናት ጀምሮ በባህል፣ በእምነት፣ በሥነ ልቦናና ጫና ስለነበር ሴቶች የአደባባይ ሰው ከመሆን ይልቅ የቤት ሥራ ከዋኞች ተጠቃሽ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፤ ቆንጅት።

ከቀደሙት ዘመናት አሁን እሰካለንበት ዘመን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች በወንዶች የበላይነት የሚዘወሩ መሆናቸው ሴቶች የመሪነት አቅም እንዳላቸው ለማሳየት እድሉን እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ሲሉ ቆንጅት መከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል። የቀደሙትም ይሁን የአሁኖቹ የፖለቲካ መሪዎች ሴት አደባባይ ወጥታ እንድትሳተፍ ከመፍቀድ ይልቅ የቤታቸውና የእነሱ ተንከባካቢ የማድረግ አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው የሚሉት ቆንጅት፥ ምንም እንኳን ሴቶች በፖለቲካው ጎልተው አይውጡ እንጂ በትምህርታቸው ግን ከወንዶች እኩል እንደሆኑ የሚታዩበት እድል ተፈጥሮ አይተናል ብለዋል። ሴቶች አመራርነት ቀርቶ የፖለቲካ አቋማቸውን ሲያንጸባርቁ አልፎ አልፎ ብቅ ሲሉ እንኳ እምብዛም ሲደግፉ አይታዩም።

ፖለቲካ የሁሉንም ዜጋ ሕይወት የሚነካ እንጅ የተወሰኑ ሰዎች ወይም የጾታ ጉዳይ አይደለም የሚሉ አመለካከቶች በነቢብ ሲንጸባረቁ ቢሰሙም በተግባር ግን በመሬት ላይ ሲተገበሩ አልታየም። ታዲያ ፖለቲካ የሴቶችንም ተሳትፎ ይፈልጋል መባሉ፣ በሴትና በወንድ መካከል ያለው ልዩነት የጾታ ብቻ እንጂ፣ ሌላ አለመሆኑን እውን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሴቶች አሁን አሁን በትምህርትና በኢኮኖሚም ዘርፍ ያላቸው ሚና እያደገ እንደመጣ የሚያምኑት ቆንጅት፣ ነገር ግን ሴቶች እራሳቸውን ችለው በመሪነት ደረጃ እንዲቀመጡ የተሠራ ተጨባጭ ተግባር አናሳ ነው ብለዋል።

ምርጫ 2013 እና ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ቅስቀሳ
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 28/2013 እንዲሁም ሰኔ 5 እንደሚካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የምርጫ ቅድመ ሥራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተከወኑ ናቸው። ከቅድመ ምርጫ ተግባራት ውስጥ አንዱ የምርጫ ቅስቀሳ ሲሆን፣ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ከየካቲት 8/2013 እስከ ግንቦት 23/2013 የተገደበ ነው። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሴቶችን ያማከለና ያሳተፈ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገና ከጅምሩ ሲወተውት መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢሕአፓ’ዋ ቆንጅት ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ እየተሳተፉ ነው ለማለት የሚስደፍር ነገር እንደሌለ ያምናሉ። ይሁን እንጂ በዘንድሮው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ በብቸኛ ሴት የፖለቲካ መሪ በመሆን ቆንጅት ለምርጫ ይወዳደራሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሴቶች በመሪነት ደረጃ ባይሆንም በሌሎች ኃላፊነቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑበት ሁኔታ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል የሚሉት ቆንጅት፥ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ከብልጽግና ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች በብዛት ሴቶችን አሳትፈዋል ለማለት ይቸግረኛል ሲሉም አክለዋል።

ሴቶችን ያማከለ ምርጫ ቅስቀሳ ሲባል የስርዓተ ጾታ እኩልነትን መሰረት ያደረጉ የምርጫ ቅስቀሳ ሒደቶችን መከተል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ቆንጅት፥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወንዶችና ሴቶች በሥነ ልቦና፣ በኢኮኖሚ ይሁን በመድረክ አመራር በእኩል መደላድል ላይ ሊሆኑ ስለማይችሉ ለሴት ተፎካካሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመንግሥትም በፓርቲዎችም በኩል መፍጠር ሌላኛው ሁኔታ እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ፣ መጋቢት 6/2013 ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ማካሄዱ የሚታወስ ነው። መድረኩን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በንግግር የከፈቱት ሲሆን ምክትል ሰብሳቢው በንግግራቸው ያለፉት 30 ዓመታት የሴቶችን የፖለቲካ ተሣትፎ ምን እንደሚመስል ገልጸው ያለውን መሻሻል ጥናቶችን በመጥቀስ አብራርተዋል። ይሁንና ገና ከሚፈለገውና ሊሆን ከሚገባው አንጻር እጅግ ብዙ እንደሚቀር ግን በንግግራቸው አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶት ላይ ጥናት ያጠኑት ኤልያስ ዓሊ በፖለቲካና በምርጫ ሒደቶች የሚሣተፉ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዙሪያ ግኝታቸውን አቅርበዋል። ከስርዓተ ፆታ ኦዲት ሪፖርት በኋላ ስለተገኙ መረጃዎች እንዲሁም የሴት ፓርቲ አባላት እና ዕጩዎችን አስመልክቶ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች የተመለከተ ጽሑፍ ደግሞ የቦርዱ የስርዓተ ፆታ እና አካታችነት ኃላፊ የሆኑት መድኀኒት ለገሠ አማካኝነት ቀርቧል።

ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ሒደት እንዲኖር ለማስቻል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ያብራሩ ሲሆን፤ ማብራሪያቸውን ተከትሎ በአመራሯ አወያይነት ከተሣታፊዎች ሐሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ሴት ዕጩዎች የምርጫ ዘመቻውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል መወሰድ የሚችሉ እርምጃዎን እንዲሆም በምርጫ ወቅት ሊደርስ ስለሚችሉ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሞያ የቀረበ ሲሆን፤ በማስከተልም የሕግና የስርዓተ ፆታ ባለሙያ እና ዓለም ዐቀፍ አማካሪ በሆኑት መስከረም ገስጥ አወያይነት፤ ቆንጂት ብርሃኑ (የኢሕአፓ ሊቀመንበር)፤ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) (የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀመንበር ) እና ነቢሃ መሐመድ (የሴት ፖለቲከኞች የጋራ ምክር ቤት መሥራች አባል) የተሣተፉበት እንዲሁም ተሞክሯቸውን ያካፈሉበት የፓናል ውይይት ተደርጓል።

የሴት እጩዎች የምርጫ ቅስቀሳ ተግዳሮት
ሴት እጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ሒደቶች ውስጥ ከሚገጥማቸው እንቅፋት ውስጥ አንዱ በምርጫ ቅስቀሳ ሐሳባቸውን በመድረክ አውጥተው እንዳይሸጡ የሚኖርባቸው ዘርፈ ብዙ ውስንነት መሆኑን ቆንጅት ያምናሉ። ቆንጅት እንደሚሉት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሴት ተወዳደሪዎች በራሳቸው ፓርቲ ያሉ ወንድ ተወዳዳሪዎች ጭምር ወደ ፊት እንዳይመጡ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩባቸው ተመክሮ መኖሩን ይጠቅሳሉ።

በወንድ ተወዳዳሪዎች የሚደርሱ ተጽዕኖዎች መካከል ሴት እጩ ለምርጫ ቅስቀሳ በቂ መድረክ እንድታገኝ እድል አለመስጠት፣ ከምርጫ ቅስቀሳ የሚገኝ ገንዘብ ለሴት ተወዳዳሪ በበቂ ሁኔታ አለመመደብና በምርጫው ተገዳዳሪ ሆነው እንዳይወጡ ገፊ ንግግሮችን መሰንዘር ዋና ዋናዎቹ ናቸው ናቸው ሲሉም ቆንጅት በአንክሮ ተናግረዋል።

ቆንጅት አክለውም ከዚህ በፊት በሴቶች ላይ መሰል እንቅፋቶች እንደነበሩ በምርጫ ቦርድ በኩል በተደረጉ ውይይቶች መነሳታቸውን አስታውሰዋል። በዘንድሮውም ምርጫም ገና በእጩ ምዝገባ ወቅት ሴቶች ላይ የደረሱ ጫናዎች ይደርሱባቸው እንደነበሩ የሚያነሱት ቆንጅት፥ በዚህም ምክንያት በእጩነት የቀረቡ ሴት ተወዳዳሪዎች ከውድድር የወጡበት ብዙ አብነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ሴቶች በምርጫ ሒደት የሚገጥማቸውን ችግር ተቋቁመው ለተገዳዳሪ ሆነው ከታዩ እንደ መጨረሻ አማራጭ የማስፈራራት እንቅፋት ሊገጥማቸው እንደሚችልም ነው ቆንጅት የጠቆሙት። ከዚያም አልፎ ወሲባዊ ጥቃት ጭምር ይደርስባቸዋል ብለዋል።
ሴቶች ከእነዚህ ተጽዕኖዎች ነፃ ሆነው የፊታች ግንቦት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ሐሳባቸውን በአደባባይ ሸጠው የመሪነት ሚናቸውን እንዲያሳድጉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል። በርግጥም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ሴት ተወዳዳሪዎችን ለማገዝ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን የሚታወቅ ሲሆን ከሁሉም በላይ መንግሥት ሴቶች ሙሉ አቅማቸው በአደባባይ እንዳሳዩ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ጋሬጣዎች እና ከተጽዕኖዎች የመጠበቅ ሚናውን መወጣት እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል።

ሴቶች በምርጫው የሚኖራቸውን ድርሻ ለማጠናከር ሴቶችና ወንዶች ከጾታ ልዩነት ውጭ ሌላ ልዩነት እንደሌላቸው ማረጋገጥ፣ የገንዘብ፣ የቅስቀሳ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም በባለ ድርሻ አካላት ሴቶችን ማበረታታት በምርጫ ሒደቱ በተግባር መታየት እንዳበት ነው ቆንጅት አጽንዖት በመስጠት ሐሳባቸውን ደምድመዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com