የእለት ዜና

የዐሥር ዓመታት የትንቅንቅ ጉዞ

ዐስር ዓመታትን የኋሊት ተጉዘን መጋቢት 3/2003 ላይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ አዝማችነት ነበር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ በተባለ ስፍራ ላይ ዕውን የመደረጉ ዜና በዓለም ላይ የናኘው። ‹‹አባይ ማደሪያ የለው፤ ግንድ ይዞ ይዞራል›› መተረቻው፣ ‹‹የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ቁጭቶች ሁሉ በእርግጥም መቋጫ ሊያገኙ ነበር አገር ከዳር ዳር የተነቃነቀው።

የመሰረት ድንጋዩን በማስቀመጥ ታሪካዊ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስም ይህን አይነት ግዙፍ አገራዊ ፕሮጄክት ኢትዮጵያ በታሪኳ በራሷ ገንዘብ ለመስራት ስትነሳ መጀመሪያ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹የዚህ ግዙፍ ፕሮጄክት ሀሳብ አመንጪዎች እኛው፣ የግንባታው ወጪ ሸፋኞች እኛው እናም የግንባታው መሐንዲሶች እኛው›› ሲሉም መደመጣቸው ይህን ያህል ግዙፍ ፕሮጄክት ኢትዮጵያ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው በሙሉ ከዕመበለት መቀነት ተፈልቅቆ ተገንብቶ ዕውን እንደሚደረግ ማሳያ ነበር። ከዛሬ ዐስር ዓመታት በፊት ታዲያ ሕዝብን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያንቀሳቀሰው ይኸው አገራዊ ፕሮጄክት ታዲያ 80 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪው ሆኖ ተቀምጦለት ነበር።

ይህ ከዳር ዳር ሕዝብን ያንቀሳቀሰው አገራዊ ፕሮጄክት በኃይል ዕጥረት ምክንያት የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከድጡ ወደ ማጡ በሆነባት ኢትዮጵያ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አሻግረው የተመለከቱ አገራት አይናቸው ደም ሊለብስ ግድ ሆኖበት ነበር። በኢትዮጵያ ባህል እና ቱፊት መሰረትም ‹‹ጠላት ከሩቅ አይመጣም›› ነው እና ተረቱ ጎረቤት አገር ሱዳን እና የታችኛው የዓባይ መዳረሻ አገር ግብጽ ከማንም በላይ ቀንደኛ ተቃዋሚ እና ተገዳዳሪ ተንካራ አገራት እስከመሆን ድረስ ብቅ አሉ። ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን አገራቸው ድረስ በመሔድ በኢትዮጵያ ላይ የጀመሩትን የሕዳሴውን ግድብ ፕሮጄክት እንዲያቆሙ ከአገራት መንግስታት ጋር ያደረጉት ድርድርም ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ ግንባታው አንድም ሳይጓተት የወደፊት ግስጋሴውን ተያይዞታል።

ግንባታው ሲጀመር በስድስት ዓመታት ተጠናቆ ኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎቷን እና አቅርቦቱን የተጋነነ ክፍተት ለማጥበብ እንደሚሰራ የታሰበለት ይኸው ግድብ ታዲያ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ማይገኝለት እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ከመጀመሪዎቹ ዐስር ግዙፍ ግድቦች ተርታ የሚሰለፍ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ መንግስት ሲገልጸው ይሰማል። 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ ውሃ የመያዝ አቅም እዲኖረው ታስቦ ግንባታው ተጀመረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፐሮጄክት በስድስት ዓመታት የታሰበው የመጠናቀቂያው ቀነ ገደብ ሳይሳካ ዐስረኛ ዓመቱን ይዞ እነሆ ሊዘከር በቃ።

5150 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተባለለት ይህ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት እንደማትሰራ ያስታወቀችበት እና ምናልባትም የደመደመችበት ታሪካዊ ፕሮጄክት መሆኑም ይታወቃል። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የውሃ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጄክቶችን እንደማይገነባ አስታውቋል። የግል ዘርፉ ወደ ኃይል ማመንጫው ዘርፍ እንዲሰማሩ እና መንግስትም ይህን ጉዳይ ከመንግስት እና የግል ዘርፉ መካከል ያለውን ቅንጅት በመጠቀምም የኃይል ማመንጫ እንዲገነባ ለማድረግ እንደሚቻለውም ለማወቅ ተችሏል።

የዓባይ ሰማዕታት
በትኛውም ዘመን የትውልድ ቅብብሎሽ ተተኪን ከማፍራት እና አገርን ከመገንባት አኳያ ያለው ጠቀሜታ ማይተካ እንደሆነ ይታወቃል። በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከባድ ተቃውሞዎችን እንዲያውም ‹‹ኢትዮጵያ እኛ በአብዮት ስንታመስ ጠብቃ ይህን ግድብ ጀመረችው›› በሚል ክስ እና ወቀሳ ስታሰማ የምትገኘው ግብጽ አንድ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላት ታሪክ አላት። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ጥሩ ቢባል መጀመሪያ ቀድሞ የሚነሳው ግብጽ ናስር ሀይቅ ነበር። ይህ ሐይቅ ሰፊ እና ረጅም አመታትን የፈጀ እንደሚባለው 12 ዓመታት ግንባታው ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ ፈጅቷል ይባላል። ታዲያ በዚህ ሒደት ውስጥ ሆኖ ሐይቁን በይፋ ያስጀመሩት እና ግብጽን በክፉ ቀን አብረው የነበሩት ታላቁ መሪያቸው ጋማል አብዱል ናስር ሐይቁን እና ግድቡን አስጀምረው ፍሬውን ሳያዩ ነበር ሞት የቀደማቸው፤ በኋላም ተተኪው አስተዳዳሪ ግብጽ ባለውለታዋን አትረሳም በሚል የሰው ሰራሽ ሐይቁን በጀማሪው ጠቅላይ ሚንስትር ናስር ሐይቅ ብሎ ሰየመላቸው።

ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ ታሪክ የላትም። ጀማሪው እና ‹‹ዓባይን የደፈረ መሪ›› ይባሉ ነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሕዳሴ ግድብን በይፋ መጀመር ካወጁበት መጋቢት 3/2003 በኋላ አንድ ዓመት ብቻ ነበር በሕይወት መቆየት የቻሉት። የተጉላትን ኢትዮጵያን እንደናፈቋት ሳይመለከቱ እና የሕዳሴውን ግድብ እርምጃ ከዳር መድረስ ሳይመለከቱ በሞት ተቀድመው አሸልበዋል። በ20 ዓመታት ወዲህም አፍሪካ ውስጥ በስልጣን ላይ እያሉ በሞት የተለዩ መሪዎች ውስጥም ቢቢሲ ስማቸውን አካቷል።
ሕዳሴው ግድብ ግን በኢትዮጵያ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፈም እንደ ልጁ ተንከባክቦ ያሳደገውን ዋናውን መሐንዲስ ስመኘው በቀለንም ከመንገድ አስቀርቷል። ሌት ተቀን በረሀ ላይ አሸዋ ለብሶ ድንጋይ ተንተርሶ እንደ አብራኩ ክፋይ እያንዳንዷን እድገቱን ለመታዘብ ከአጠገቡ የማይርቀውን ስመኘው በቀለን በአንድ መራር ማለዳ ሕልፈቱን እስክንሰማ ድረስ ሙሉ ጉልበቱን እና አትኩሮቱን ተቀብሎ የሕዳሴው ግድብ ግስጋሴውን ቀጥሏል።

የአገርን ጥቅም የማስጠበቅ ትንቅንቆች
በዐስረኛ ዓመት ዕድሜው ሌት ተቀን በሚተጉ ኢትዮጵያዊያን ዕጆች 78.8 በመቶ የግንባታው ደረጃ ደርሷል። በዚህ ሁሉ ግን ታዲያ የሚደረገው የዕለት ተዕለት ተጋድሎ ከባድ እና ዕልህ አስጨራሽ ነው። የኋላ የጀግንነት ታሪኮችን በዲፕሎማሲው ዘርፍም ለመድገም የሚደረገውን ትንቅንቅ በማሳለጥ ረገድ ቆራጥ ትውልድን ማፍራት ምትችለው ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ጥቅሞቿን እንዳስጠበቀች አሁንም ቀጥላለች። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በታላቅ ወኔ እና በከፍተኛ ሞራል ጀመሩትን የሕዳሴው ግድብ ሳይቋጩት በሞት ቢለዩም ነገር ግን ተከታዩ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም ያለባቸውን የአገር ውስጥም ሆነ የተቀረውን ዓለም ጫና ተቋቁመው የግድቡን እንቅስቃሴ በትኩረት እና በቁርጠኝነት በመምራት በግድቡ ግንባታ ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የውሃውን የፍሰት አቅጣጫ ማስቀየር ተግባር ሲከናወን በኃላፊነት ኢትዮጵያን ሲመሩ ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የማስተዳደር ታሪካዊ አደራ የተጣለባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም ከመጀመሪዎቹ ስልጣን ዘመናቸው ጀምረው የሕዳሴው ግድብን ከአትኩሮታቸው እንደማያወጡት በሚያሳብቅ ሁኔታ ትላልቅ ሂደቶችን ሲመሩ እና እልህ አስቸራሽ ድርድሮችን አንድ ጊዜ ካይሮ፣ ሌላ ጊዜ ካርቱም በል ሲልም አዲስ አበባ ላይ በማካሔድ የአገርን ጥቅም በኢትዮጵያዊ ወኔ አላስነካም በሚል የአንገት ለአንገት ትንቅንቁን ተያይዘውታል።

የአገርን አንድት ከመስበክ አንጻር ከፍተኛ ሚና ሚጫወተው ይኸው ፕሮጄክት አስር ዓመት ዕድሜ እስኪሞላው ድረስ 14 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለግንባታው ከሕዝብ ተሰብስቧል። ታዲያ ይህ ገንዘብ በገንዘብ ይተመን እንጂ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ወክለው የተቀመጡ እና የሕዳሴው ግድብን በአንድም ሆነ በሌላ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በገንዘብ የማይለካ ተጋድሏቸውን አገር እና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ሲጥሩ እናስተውላለን።

ከጠቅላይ ሚንስት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፤ ከውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እስከ ቴክኒካል ኮሚቴዎች ድረስ ሕዳሴው ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ትንቅንቅ እንዲህ ተብሎ ሚገመት አይደለም። ከሦስትዮሹ የድርድር ውጣ ውረድ ባለፈ በዓለም አቀፍ አገራ የሚታየው ጣልቃ ገብነት ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን የድርድር አካሔድ እጅግ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ያደርገዋል። እንዳንድ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ሰፊ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁ ግለሰቦች እና ውሃ ፖለቲካውን በሚገባ የሚረዱት ግለሰቦች እንደሚሉት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከተቀረው አገር ጋር ያደረገችው ግብግብ ነው ሲሉ ይደመድማሉ። ከዚህ ሁሉ ድርድር እና ትንቅንቅ ፣ ከባድ ጫናዎች በተቃራኒው የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሊት ለማካሔድ ተችሏል። ይህም ደግሞ በአራት ዙሮች ለመሙላት የተቃደ ቢሆንም ኢትዮጵያ ያሉባትን ጫናዎች ተቋቁማ በመጀመሪያ ዙር 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንዲሞላ ሆኗል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ያለውን ጠቀሜታ እና የኢትዮጵያን በሕዳሴው ግድብ ላይ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ለዓለም ያስገነዘበ እና ሊደረግ ከታሰበው ወደ ኋላ መቅረት የማይታሰብ መሆኑን ማሳያ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ታዲያ ከግብጽ እና ከአሜሪካ በኩል ሲሰነዘር የነበረው ጫናን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሕዝብ በመቅረብ ‹‹ግድቡን ከመሙላት የሚያስቀረን አንዳች ምድራዊ ኃይል የለም›› ሲሉም ተደምጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ኹለተኛ ዙር ውሃ ማለትም 13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ተጨማሪ ውሃ ወደ ግድቡ ለመሙላት በዝግጅት ላይ እንደሆነም የሚታወቅ ነው። በዚህም መሰረት በዚህ ዓመት ላይ የውሃ ሙሊቱ ሒደት በድል ከተጠናቀቀ የውሃ መጠኑ ከመጨመሩ ባለፈም በሕዳሴው ግድብ ላይ ኢትዮጵያ የሚኖራት በላይነት እና ዲፖሎማሲ ልህቀት ከፍ እደሚልም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከጊዜያት በፊት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለቻ ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com