የእለት ዜና

የሲሚንቶ ጅምላ አከፋፋዮች ከአንድ የሲሚንቶ ምርት ውጭ እንዳያከፋፍሉ ተወሰነ

የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋው በእጥፍ የጨመረውን ሲሚንቶ ዋጋ ለማረጋጋት ጅምላ አከፋፋዮች ከአንድ ፋብሪካ የሲሚንቶ ምርት ውጭ እንዳያከፋፍሉ መወሰኑን ንግድ ሚኒስቴር የጥራትና ንግድ አሠራር ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሚኒስተር ዴኤታው ይህ ማለት አንድ ደርባ ሲሚንቶ የሚያከፋፍል የሲሚንቶ ጅምላ አከፋፋይ ዳንጎቴ አይወስድም ዳንጎቴ የሚያከፍፍል አከፋፋያ ደግሞ ሞሰቦ አያከፋፍልም ማለት እንደሆነ ነው በምሳሌ ያብራሩት። አያይዘውም አንድ አከፋፋይ አንድ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲያከፋፍል መደረጉን ገልጸው ይህ የተደረገው ለቁጥጥር እንዲያመች ነው ብለዋል።

አከፋፋዮች የሚታወቁ በመሆናቸው በሚያከፋፍሉበት ክልል እና ከተማ አስተዳደር ከየትኛው ፋብሪካ ሲሚንቶውን በምን ያህል ብር እንደገዙ በምን ያህል ብር እንደሸጡ ለማን እንደ ሸጡ ቁጥጥር በማድረግ የሲሚንቶ ዋጋውን ለማረጋጋት እየተሠራ ነው በማለት ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል።

እሸቴ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲጨምር የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ገልጸው በትግራይ ክልል የሚገኘው የሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ ማቆም ለዋጋ መጨመሩ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።ሞሰቦ ሲሚንቶ አሁን የሙከራ ምርት በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአዲስአበባ የተለያዩ ስፍራዎች አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ሲሚንቶ እስከ 750 ብር ድረስ እየጠሸጠ መሆኑን አረጋግጣለች። ሲሚንቶ ገዥዎች ደግሞ 340 ብር ከወራት በፊት መግዛታቸውን ገልጸው አሁን በእጥፍ ዋጋው መጨመሩ ግንባታቸውን እንዳስተጓጎለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሲሚንቶ ዋጋ መጨመር የጀመረው በ2010 በነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት አማካኝነት በተደረገው የኤሌክትሪክ ፈረቃ ምክንያት እንደሆነ እና የሲሚንቶ ምርት ምንም አይነት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የማይፈልግ በመሆኑ እንደነበር የሲሚንቶ እና ተዛማጅ ኢንደስትሪ ምርምርና ቴክኖሎጅ ልማት ዳይሬክተር ስመኝ ደጉ አስታውሰዋል።

ከዚያ በተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማሽኖች ሲበላሹ ከውጭ አገራት የሚገቡ በመሆናው እና ማሽኖቹ በየኹለት እና ሦስት ዓመት መጠገን ስለሚኖርባቸው ምርታቸው እንዲቀንስ እንዲሁም ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻቅብ አድርጎታል ብለዋል።
መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ለሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 85 ሚሊየን ዶላር መድቦ ፋሪካዎቹ ያለባቸውን ችግር እንዲፈቱ ተደርጎ እንደነበር እና ፋብሪካዎቹ ልምድ ያለው የሠው ኃይል ከውጭ አገራት ማስመጣታቸውን ስመኝ ገልጸዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሌሎች ዘርፉ ከሚመለከታቸው የመንግስት መሥሪያቤቶች እና የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትንና የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ክፍተት በመለየት የችግሩን ጥልቀት በመረዳትና የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዲቻል ለ15 ቀናት ፋብሪካ ውስጥ ሆነው ችግሩን በጥልቀት የሚያጠኑ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን በመመደብ የዳሰሳዊ ጥናት አድርጓል።

በጥናቱ ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ውስጥ አሉ ከተባሉ ችግሮች መካከል በተደረገላቸው ድጋፍ ልክ ቃላቸውን አክብረው መሥራት ባለመቻላቸው፣ማሽኖች ቶሎ አለማስገባታቸው፣ ዘርፉ በደላሎች ሸፍጥ የተሞላ መሆኑ፣የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ችግሮች ፋብሪካዎቹ እንዳሉባቸው በዳሰሳ ጥናቱ አረጋግጧል።

የሲሚንቶ ምርት የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ከ233 እስከ 290 መሆኑ ተገልጿል። አብዛኛዎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለአንድ ኩንታል ለማጓጓዝ የመጫኛ ዋጋ እስከ 50 ብር ድረስ ቢሆን በደላች አማካኝነት ከ60 እስከ 120 ብር ድረስ ጭማሪ እንደሚደረግበት ስመኝ ገልጸዋል።

የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ምርቶችን ከዚህ በፊት በነበረው ዋጋ ማትረፍ የሚገባቸውን የንግድ ሕጉ የሚፈቅደውን ትርፉ ብቻ አስበው መሥራትና አገርንና ህዝብን የማገልገል ግዴታቸውን በአንድ ወር ውስጥ የማይወጡ ከሆነ የህብረተሰቡን የኑሮ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል መንግሥት አዋጭ ያለውን የዘርፉን ችግር ሊፈታ የሚችል ውሳኔ የሚወስን መሆኑን አስታውቋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!