አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

Views: 119

አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‹የሩሲያ-አፍሪካ፣ ባህልን መልሶ መገንባት› በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ዓለም ዐቀፍ የፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በበይነ መረብ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ‹ባህላዊ ትስስርን መልሶ በመገንባትና ወዳጅነታችን በማጠናከር እንዲሁም በጊዜ ሂደት የተፈተነውን አብሮነት በማጽናት የሕዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አካላትን መመከት ያስፈልጋል›› ብለዋል።
ጉባኤው መሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገራዊ ፖለቲካ መረጋጋትና ለዓለማቀፍ ትብብር ያላቸውን ሚና በግልጽ የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የሩሲያ ፌዴሬሽን የበርካታ ፈላስፎች መኖሪያ መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚህም ለአፍሪካ አገራት መሪዎችና ሕዝባቸው ነጻ የሆነችና በኢኮኖሚ የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር ሕልም አንግበው እንዲነሱ መነሳሳት ፈጥረውባቸዋል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን አስተዳደር የተመለከቱ የፍልስፍና አስተምሮቶችን በመከተል በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ዛሬ ላይ ለሁሉም በእውነት ላይ የተመሠረተና ግለሰባዊ ብቃትንና የጋራ የሆነ መልካም ስብዕናን ለመፍጠር የሚያስችል ውጤታማ የሆነ የፍልስፍና እሳቤ ለማራመድ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል ያሉ ሲሆን፣ አያይዘው ‹‹እኔም ይህንን እሳቤ የሚያራምደውን የብልጽግና ፓርቲ በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ እገኛለሁ›› ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን በማጠናከር የሕዝባቸውን ጥያቄ መመለስ አለባቸውም ብለዋል። የተባበሩት የሩሲያ ፓርቲ ጄኔራል ካውንስል ምክትል ፀሐፊና የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር ኪልሞቭ አንደሬይ በበኩላቸው የጉባኤው ትኩረት በዝግጅቱ ላይ በሚቀርቡ ርዕሶች፣ በሰላምና ደኅንነት፣ ጣልቃ ገብነትን በመመከት ላይ ያተኩራል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com