የእለት ዜና

በገና በዐብይ ጾም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ለኹለት ወራት ገደማ የሚጾመው ታላቁ ጾም ወይም ዐብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንቱን ይዟል። ምዕመኑም በዚህ ሰሞነ ጾም፣ ከመጾም እና ከመጸለይ በተጨማሪም የበገና መዝሙራትን አብልጠው የሚያዳምጡበት ወቅት ነው።

ቤተክርስትያኒቱ ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች ከምትጠቀምባቸው የመዝሙር መሣሪያዎች መካከልም ከበሮ፣ ጸናጽል፣ ክራር፣ መሰንቆ እና በገና ይጠቀሳሉ። አዲስ ማለዳም ‹በገና› እና ‹ዐብይ ጾም› ምን የተለየ ቁርኝት አላቸው? ስትል በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን የስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘን ጠይቃ ተከታዩን ጽሑፍ አሰናድታለች።

ጥቂት ስለ በገና
በገና ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ዕድሜ ጠገብ መሣሪያ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራዕይ ድረስ ቢነበብ የበገናን ታላቅነት የሚመሰክሩ ብዙ መረጃዎች መኖራቸውንም ሊቃውንቱ ምስክርነት ይሰጣሉ።
‹‹በገና ከዘመነ አበው ጀምሮ ነበር። በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ስናነብም በገና በብዙ ቦታ ላይ ይጠቀሳል።›› በማለት ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን ይናገራሉ። ከብቶቻቸውን እየጠበቁ፣ ሰብላቸውን ሲሰበስቡ፣ ደስታ ወይም ሃዘን ሲገጥማቸው፣ የውስጣቸውን ስሜት የሚገልጹበት፣ የሚረጋጉበትም ይሁን ደስታቸውን የሚያንጸባርቁበት በገናን እየደረደሩ እንደሆነ ነው የሚያወሱት።

በተለይም በብሉይ ኪዳን ዘመንም በነብየ እግዚአብሔር ዳዊት ጊዜ በገና የበለጠ ሰፍቶ ይገኝ እንደነበር ይገልጻሉ። ነብየ እግዚአብሔር ዳዊትም በገና ደርዳሪ እንደነበር ጠቅሰዋል። ‹‹ሲከፋውም፣ ሲደሰትም በገናን ይደረድራል። ከዚህ አልፎ ተርፎም በዘመኑ ንጉሥ የነበረው ሳኦል በዳዊት ላይ የምቀኝነትና እና የቀናተኝነት ክፉ መንፈስ ይዞት የነበረ በመሆኑ ከበሽታው የሚያገግመውና ወደ ቀልቡ የሚመለሰው ዳዊት በገና ሲደረድርለት ነበር። ክፉ መንፈስ የሚርቅለትና ከበሽታውም የሚፈወሰው በዚህ መሣሪያ ነበር።›› በማለት አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቤተክርስትያኒቱ የመዝሙር መሣሪያ ብላ ከምትጠቀምባቸው መካከል አንዱ በገና እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የመዝምረ ዳዊት ክፍል ላይ ተጽፎ ይገኛል። ይኸው በገና በዘመን ብሉይ ብቻ ሳያበቃ በዘመነ ሀዲስም በቅዱሱ መጽሐፍ የዮሐንስ ራዕይ ላይ ተጠቅሶም ይገኛል።

ይኸው በዐብይ ጾም በስፋት አገልግሎት የሚሰጥበት በገና 10 አውታሮች ወይም ገመዶች አሉት። ይህም የራሱ የሆነ ትርጓሜ አለው። ሊቀጠበብት ሐረገወይንም ሲናገሩም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ዐስር ፍጹም ቁጥር እንደሆነ ጠቅሰዋል። ነብዩ ዳዊት 10 አውታር ባለው በገና አመሠግንሃለሁ ማለቱ፤ እንዲሁም ለሙሴ የተሰጡት አስርቱ ትዕዛዛትም ቢሆኑ ፍጹም ናቸው ብለዋል።

ወደ ቅድስና የሚደረስበትን 10 ማዕረግም በምሳሌነት በማንሳት፤ አንድ የቅድስና ሕይወትን መኖር የመረጠ ሰው ከአንድ ጀምሮ ዐስር ላይ ሲደርስ ፍጹም ሆነ ወይም በቃ ይባላል በማለትም የቁጥሩን ፍጽምና በምሳሌነት ያነሳሉ። በገናም የቤተክርስትያን ፍጹም መሣሪያ በመሆኑ ዐስር አውታር አለው።

የበገና ጸባይ እና ዐብይ ጾም
በገና የራሱ የሆነ መገለጫዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል ለጭብጨባ (ለቸብቸቦ) አይመችም። ወደ ሥጋ ባህርያት ለሚወስዱ ስሜቶች አመቺ አይደለም። ምቱ ወይም ቅኝቱ ዝግ ያለ እና እጅግ የተረጋጋ፤ በዛው ልክ መንፈስን የሚያረጋጋና ነፍስን የሚያናግር ዜማ ያለው ነው።

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አክለው ይህን ይላሉ፤ ‹‹በገና ቅኝቱ የተረጋጋ በመሆኑ ለዐብይ ጾም አመቺ እና ተመራጭ ነው። በገናው ከድምጽ ጋር ሳይሆን ድምጹ ከበገና ጋር ነው የሚሄደው፤ የሚመራው በገና ነው። ዐብይ ጾም ደግሞ በቤተክርስትያናችን ሥርዓት ዘንድ የጭብጨባ (ቸብቸቦ) መዝሙራት፤ በከበሮ እና በእንቅስቃሴ የሚዘመሩ መዝሙራት የሚሰሙበት ወቅት አይደለም።››

በዐብይ ጾም ሰሞን በከበሮ፣ በሽብሸባ እና በጸናጽል የሚዘመሩ መዝሙራት አይዘመሩም ያሉት ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን፤ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስትያኒቱ ያሉ አገልግሎቶች በሙሉ የሚሰጡት በመቋሚያ ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹ከበሮ እና ጸናጽል የለም፤ ምክንያቱም እነዚህ የራሳቸው ጊዜያት ስላላቸው ነው።›› ብለዋልም።

ያም ብቻ አይደለም፤ በተያያዘ ይህን ሐሳብ ጨመሩ ‹‹ዐበይ ጾም የሃዘን እና የምህላ ወቅት ነው። ሰው እና እግዚአብሔር እጅግ የሚገናኙበት ወቅት ነው። ይህ ጾም የበለጠ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፣ ስንወድቅ የምንነሳበት እና የምንጠነክርበት፣ የምንረጋጋበት ወቅት በመሆኑ በገና ለዚህ አጋዥ ሆኖ ተገኝቷል። በገና ብቻም ሳይሆን መሰንቆም በዐብይ ጾም ወቅት ተመራጭ የመዝሙር መሣሪይ ነው።››
በሃዘን፣ በተመስጦ እና በጾም ውስጥ ለሚገኝ ማኅበረሰብ እና ምዕመን፤ በገናን መስማት እና በገና መደርደር የበለጠ መንፈስን ያረጋጋል ወይም ያሳድጋል ተብሎም ይታመናል።

አሁናዊ ሁኔታ
በቤተክርስቲያኒቱ ጥንታዊ የመዝሙር መሣሪዎች ከሚባሉት መካከል በገና አንዱ ይሁን እንጂ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረሳ እና የሚማረው እንዲሁም የሚያስተምረውም ሰው ጠፍቶት እንደነበር ይነገራል። ይህንን ሁኔታም የተገነዘበችው ቤተክርስትያኗ፤ በገናን ከተረሳበትና ከተደበቀበት ለማውጣትና ለማንሳት አልፎም አሁን ላለው ትውልድ ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጋለች። እንደ ጥምቀት እና መስቀልን ጨምሮ ባሉት የአደባባይ በዓላት ላይ በስፋት እየተገለገለችበት ትገኛለች።

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይንም ይህንን በተመለከተ የሚሉት አላቸው። ‹‹አሁን ያለው ትውልድ በገናን በመዝሙር እንዲጠቀም ለማድረግ ታልሞ እየተሠራ ይገኛል። ሌላው በዚህ የመዝሙር መሣሪያ ለመዝሙር አገልግሎት ብቻም ሳይሆን ኃይለ አጋንንትን ለማራቅ ያገለግላል። በቤተክርስትያናችን የምንጠቀማቸው የመዝሙር መሣሪዎች ለመዝሙር አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የሰውን ልቦና ለመሰብሰብ፣ ክፉ መንፈስን ለማባረር ይጠቅማሉ። መሣሪዎቹ መዝሙር ለማድመቅ እና ለማሳመር ብቻ ሳይሆን የሚያገለግሉት፣ የመዋጊያ መሣሪያዎቻችን ጭምር ናቸው። መንፈሳዊ ኃይል እና ብርታትም አላቸው።››

በዚህም መሠረት አሁን ያለው ትውልድ በገና የመዝሙር መሣሪያ የሆነውንና ተዘንግቶ የኖረውን በገናን እንዲያነሳ፣ እንዲጠቀምበት፣ እንዲማርና እንዲሠለጥንበት፣ እንዲሁም ክፉ መንፈስን ለማራቅ እንዲገለገልበት የቀረበለት እንደሆነ ሊቀጠበብት ያሳስባሉ። በበዓላት ላይ በገና ተይዞ መወጣቱም በገና ከእግዚአብሔር ጋር እንድትቀራረብ ይረዳሃል ብሎ ለማሳየት እና በማንኛውም ሰዓት መጠቀም እንደሚቻል ለማስረዳት የተደረገ ነው ብለዋል።

በገናን ማን ይደርድር?
ማንኛውንም መንፈሳዊ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እና አካሄዳቸውን በመንፈሳዊ መንገድ ያደረጉና በመዝሙር አገልግሎት ውስጥ ያሉ፤ ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ፣ ንስሃ የገቡ እና ራሳቸውን ለፈጣሪ የሰጡ፣ ይቅርታን የሚያደርጉ እና የሚጠይቁ ሰዎች በገና ቢደረድሩ ይመረጣል።

‹‹በመጀመሪያ የእኛ ሕይወት መስተካከል ይኖርበታል። እንደ ሰው ንስሃ ገብተን ማስተካከል ይገባል። በዚህ ጾምም ቢሆን ራሳችንን ወደ እግዚአብሔር ያቀረብን መሆናችንን ማረጋገጥ እና ከዚህ በኋላ በበገናም ይሁን በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ውስጥ ብንሳተፍ አጋንንትን፣ የመለያየትንና የክፋትን ኃይል ማሸነፍ እንችላለን። ይህም ሕይወታችንን ማስተካከልና ራስን ለእግዚአብሔር መስጥትን ይጠይቃል›› ያሉት የስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን ናቸው ።

ለቤተክርስትያን ምን ጠቀመ?
የእምነት ተቋማት አንዱና ቀዳሚው ዓላማ ምዕመናንን በሥጋም ይሁን በነፍስ የማዳን ሥራ ነው። ሊቀጠበብት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳነሱት፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም ይህን ዓላማ ለማሳካት ትተጋለች።
‹‹የቤተክርስትያን በሥርዓት መሠራት፣ የካህናቱ አገልግሎትም ይሁኑ የመንፈሳዊ መሣሪያዎች ጥቅም ማሰሪያው ምዕመናን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ነው። በገናም ምዕመናንን ወደ እግዚአብሔር ከሚያቀርቡ የመዝሙር መሣሪዎች መካከል አንዱ ነው። ይህም ማለት ምዕመናን የሠሩትን ኃጥያት አስበው፣ መውደቃቸውን፣ በደላቸውን አስበው ወደ ልባቸው ተመልሰው ንስሃ እንዲገቡ በገናን በተረጋጋ መንፈስ መስማት ያስፈልጋል። የበገና ድርደራ የነፍስ ደስታን ነው የሚያመጣው። የነፍስ ደስታ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ ርስት ለመውረስ እንዲቻል የሚያደርግ አጋዥ መሣሪያ ነው›› በማለትም ያብራራሉ።

በገና በኢትዮጰያ
በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ሥማቸው ገንኖ ከሚጠሩ ጥንታዊ አገራት መካከል ቀድማ የምትጠራ አገር እንደሆነች ሲነገር ይሰማል። ይህንን የሚያስረዱት ሊቀጠበብት ሐረገወይን፤ ‹‹ኢትዮጵያ ከዘፍጥረት ጀምሮ በእግዚአብሔር የምታምን፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ አገር ናት። በዚህም በገና በዚህ ጊዜ ገባ ብለን የምንናገርላት አገር አይደለችም። ከጥንት ጀምሮም በገናን የምትገለገል አገር ነች።›› ሲሉም ይደመጣሉ።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ለበገና አዲስ አይደለችም የሚሉት ሊቀጠበብቱ፤ በተለይም ነብየ እግዚአብሔር ተብሎ በሚጠራው በዳዊት ዘመነ መንግሥት ጊዜ በገና የበለጠ እና እጅግ ተስፋፍቶ እንደነበር ይናገራሉ።
‹‹የሰለሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ታቦታቱን መጽሐፍቱን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሲገባ የመዝሙር መሣሪያዎችን በስፋት ይዞ ገብቷል። ይህ ማለት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ገብተዋል ማለት አይደለም›› በማለትም አጽንኦት በመስጠት ይናገራሉ። በገና ከሦስት ሺሕ ዘመን በፊት ግን መስፋፋቱን እና ማደጉንም ጠቅሰዋል።

ሊቀጠበብት በመጨረሻ ይድረስልኝ ያሉትን መልዕክት ሲያስተላልፉ፤ ‹‹አባቶቻችን ያወረሱንን፣ መጽሐፍ ቅዱስም ያጸደቀልንን በበገና እግዚአብሔርን ለማመስገን ራስንም ወደ መንፈሳዊነት ለማሳደግ፣ ቤተክርስትያንን ለማገልገል የበገና መሣሪያን ብናከብረው፤ ብንማረው ልጆቻችንም ይህን መሣሪያ ቢጠቀሙ ከኃጢያት እና ከአልባሌ ቦታ ይጠበቃሉ።›› ያሉ ሲሆን፣ መልካምና የበረከት ሰሞነ ጾም እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com