የእለት ዜና

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አወጣጥ አሳታፊነት

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም ላያንጸባርቅ ይችላል።

ክፍል 1
በሚኪያስ በቀለ (አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1) በሕገ መንግስት ማውጣጥ ውስጥ የሚኖር ተሳትፎ አስፈላጊት እና ሒደት
የአንድ ሃገር ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው። ሕዝብ ይህንን ሉዓላዊ ስልጣኑን በዋነኛነት የሚተገብረው መንግስት በሚባል እና በሚወክለው ተቋም አማካኝነት ነው። ይህ መንግስት የሚባል ተቋም በሕዝብ በውክልና የተሰጠውን ኃላፊነት የሚተገብረው ደግሞ በሕገ መንግስት ውስጥ በተሠፈረለት ልክ ነው። ስለዚህ ሕዝብ የሉአላዊነት ሰልጣኑን እንዴት በውክልና እንደሚሰጥ፣ እና ሰልጣኑንም እንዴት እንደሚተገበር መወሰን እና መቅረጽ መቻል አለበት።
ሕዝብ በሚመሰረተው የመንግስት አወቃቀርም ሆነ ሊኖር ስለሚሻበት ማህበረሰብ ሃሳቡን ካልሰጠ ስለ ሕዝብ ሉአላዊነት ማውራቱ ዋጋ እንደሌለው አሎክ ፓካርል የተባሉ ጸሃፍትን በመጥቀስ አቶ ተጓዳ አለባቸው የተባሉ የሕገ መንግስት ተማሪ በሁለተኛ ዲግሪ ሟሟያቸው ላይ ያስረዳሉ።

አሳታፊ ሕገ መንግስት የማውጣት ሒደት፤ የሰነዱን ቅቡልነት እና ውጤታማ ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን የማህብረሰብ ፍላጎትም ግምት ውስጥ ለመክተት ያስችላል።
እንዲሁም እውቅና ከተቸረው ዋነኛ የዴሞክራሲ ሞሰሶ ብሎም “የዜጎች በሃገራዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ” የሰብዓዊ መብትም ማረጋገጥ ነው።
በሕገ መንግስት ውሰጥ የሚኖር ተሳትፎ አንድም በሒደቱ ውስጥ በሚሳተፉ ሃይሎች እና ተቋማት ወኪልነት ሌላም ማህበረሰቡ በቀጥታ በሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች ይገለጻል።
አዲስ ሕገ መንግስት የሚወጣው መሠረታዊ የሆነ ሃገራዊ ለውጥን ተከትሎ፣ አዲስ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ስርዓት ለመዘርጋት ነው። በዚህም ምክንያት አዲስ ሕገ መንግስት የማውጣትም ሆነ የነበረውን የማሻሻል ስራዎች ከሌሎች ሕጎች በተለየ፣ ጠልቅ እና ዘለግ ያለ ሒደት ይኖረዋል።

ሕገ መንግስት የማውጣጥ አካሔድ በአራት ሒደቶች ተለይቶ ሊቀመጥ ይችላል – ማርቀቅ (drafting)፣ ውይይት (deliberation)፣ ማውጣት (adoption) እና ማጽደቅ (ratification)።
የፖለቲካ ለውጥን ተከትሎ በሕገ መንግስት ላይ ድርድር የሚያደረግ ሁሉን ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ዋነኛው ቅድመ ሁኔታ ነው። የሽግግር መንግስት የመመስረት ሃሳብ ብሎም ተግባር ከአንድ የፖለቲካ ሃይል የመነጨ ቢሆንም ሁሉን ማሳተፍ እና እኩል የድርድር አቅም መሰጠት ይኖርበታል። በየአቅጣጫው ያሉ የማህበረሰብ ተወካዮች የወደፊት ሀገራዊ እጣ ፈንታ ላይ ብቻ ሳይሆን እጣ ፈንታው በሚወሰንበት አካሄድም ላይ ሊሳተፉ ያሻል።

2. የለንደን ውይይት – የአሸናፊዎች ድርድር
የኢፌድሪ ሕገ መንግስትን የማርቀቅ ሒደት ለመገንዘብ አጀማመሩን እና በሒደቱ ውስጥ የተሳተፉ ተቋማት እና የፖለቲካ ሃይሎች መመልከት ያስፈልጋል። ሒደቱ የኢሕድሪ መንግስት መሽመድመድ፣ በሀገረቷ አስተዳደር እና ግዛት ላይ ያለውን ቁጥጥር ማጣጥ ይጀምራል። ይህን የተገነዘቡት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህውሃት) የመሠረተው የኢትዮጲያ ሕዝባዊ አርነት ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር አሜሪካን ባዘጋጀችው የለንደን ጉባኤ ላይ ግንቦት 19፣ 1983 ዓ.ም ተገናኙ። ኦነግ በውይይቱ ላይ ከታዛቢ የዘለለ ተሳታፊነት እንዳልነበረው የጊዜው ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በኢሜል ማሳወቃቸውን እራሳቸው ዶ/ር ነጋሶ በቃል እንደገሯቸው አቶ ተጓዳ አለባቸው ጽፈዋል።

በአሜሪካ በኩል ሲያደራድሩ የነበሩት በጊዜው በአፍሪካ ጉዳይ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ የነበሩት ኅርማን ኮህን የተሻለ ስነ ስርዓት (discipline) የነበራቸው የኢሕአዴግ ጦሮች ስለነበሩ፣ በሀገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ እነሱ ማእከላዊ መንግስቱን መቆጣጠር እንዳለባቸው የአሜሪካን አቋም መሆኑን በጊዜው መግለጻቸው ተመዝግቧል።
ኢሕአዴግ ማእከላዊ መንግስቱን ከተቆጣጠረ በኃላ “የሰላም እና ዲሞክራሲ ጉባኤ” ከግንቦት 24 እስከ 28፣ 1983 ዓ.ም እንዲዘጋጅ ቀጠሮ የተያዘው በዚሁ የለንደን ጉባኤ ነበር። ከቀጠሮ ሌላም የሽግግር ቻርተር እንዲወጣ እና የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ከመወሰኑ ባሻገር የኤርትራም የነጻነት ጥያቄ እውቅና ተሰጥቶታል – በለንደኑ ጉባኤ።

3. የአዲስ አበባው የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤ – ያለቀለት ቻርተር ማጽደቅ እና የሽግግር ምክር ቤት ማቋቋም
ኢሕአዴግ ማእከላዊ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኃላ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት “የሰላምና ዴሞክራሲ ኮንፈረስ” ተካሄደ። ተሳታፊቹ በአብዛኛው በብሔር የተደራጁ ሃይሎች ነበሩ። በፊት የነበሩ የሽምቅ ተዋጊዎች እና ከውጪ የገቡ የፖለቲካ ሃይሎች ቢኖሩም የኢሕአዴግን ጥሪ ተከትሎ በአንድ ለሊት የተፈለፈሉ የፖለቲካ ሃይሎችም እንደነበሩ አቶ ተጓዳ አለባቸው ጽፈዋል። ሕብረ ብሔራዊ፣ ሁሉንም የኢትዮጲያ ክፍል እወክላለሁ የሚል ድርጅት አልነበረም። የአማራን የማህበረሰብ ክፍልን እወክላለሁ የሚል ድርጅት አለመምጣቱንም ከጉባኤው በኋላ በነበረ የፓናል ውይይት ላይ የጉባኤው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ (በሁለተኛው የጉባኤ ስብሰባ የተመረጡ) ገልጸዋል።
የተሳተፉት የፖለቲካ ሃይሎች 27 ሲሆኑ ከአዲስ አበባ ዮንቨርሲቲ እና ሰርቶ አደር ሕዝቡ የተወከሉ ነበሩ። 22 የውጪ መንግስታት እና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንደታዛቢ ተሳታፊዎች ሆነው ነበር።

ጉባኤው አሳታፊ አለመሆኑ ለብዙዎች ግልጽ ነበር። በጉባኤው ላይ የነበረው ውክልና “የአመለካከት እንጂ የሕዝብ” እንዳልሆነ የጉባኤው ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተስተውሏል። ነገር ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነበር።
ከብሔር እና ሃይማኖታዊ ማንነቶች በዘለለ የሕብረ ብሔራዊ አመለካከት የነበራቸው ድርጅቶች ውክልና አልነበራቸውም። በደርግ ጊዜ በሰፊው ሲንቀሳሰቀሱ የነበሩ እና ጠላት ሆነው የቆዩትን ሕብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች – የኢትዮጲያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የመላው ኢትዮጲያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ጨምሮ የኢትዮጲያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዲፒ)፣ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ያካተተ የኢትዮጲያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ጥምረት በጉባኤው፣ በኃላም በሚመሰረተው የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ላይ እንዳይሳትፉ ሆነው ነበር። ለዚህ ምክንያት ብዙዎች የድርጅቶቹን ሕብረ ብሔራዊ ቅርጽ እና ከነበራቸው የረዥም ጊዜ ልምድ እና ተቀባይነት አንጻር ለኢሕአዴግ ተቀናቃኝ ሆነው ሊወጡ መቻላቸው እንደነበር ይገለጻል። ከጉባኤው በኃላ በነበረ የፓናል ውይይት ላይ የጉባኤው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ይሄ ውህድ ላለመሰተፉ እንደምክንያት ያስቀመጡት እንደ ጦርነት አዋጅ የሚቆጥሩትን የደርግ የመጨረሻ ጉባኤ መቀበላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ውህዱ እንኳን ጦርነት የማወጅ ወደ ውጊያ ለመግባት የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልነበር የብዙዎች ትዝብት ነበር።

የጉባኤው ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሰረተውን የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት መቀመጫዎች ባደላደሉበት የመጨረሻ ቀን ስብሰባ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጲያ ሠራተኛ ፓርቲ (ኢሠፓ) “ወንጀለኛ ድርጅት” ስለሆነ በጉባኤውም ሆነ በሚቋቋመው የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት እንዳይሳተፍ እግድ ተጥሎበታል። የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር በጉባኤው እንደ ታዛቢ ተሳትፎ አድርጎአል።

የሰላም እና ዴሞክራሲ ጉባኤ ዋነኛ ውጤቶች የሽግግር ጊዜ ቻርተር እና ባለ 87 አባላት የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ነበሩ። ቻርተሩ የጉባኤው ውጤት ሳይሆን መጀመሪያ በኢሕአዴግ፣ ኦነግ እና የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር የተወሰነ መሆኑን ብዙዎች በትክክል ይናገራሉ። ብዙዎች እንደሚገልጹት፤ ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ አቶ ገብሩ አስራትን በቃል በማነጋገር ብሎም “ሉአላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጲያ” የሚለውን መጽሃፋቸውን በመመርመር እንደገለጹት የሽግግር ጊዜ ቻርተሩ ቀደም ብሎ በኤርትራ ሲንዓፌ በሚባል ቦታ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ሌንጮ ለታ ተስማምተው የተፈራረሙበት ሰነድ ነው።

ቻርቱሩን ለጉባኤው ያቀረበው ኢሕአዴግ ነበር። ቻርተሩ በቀረበበት የ2ኛ ቀን የጉባኤው ስብሰባ ላይ ተሳታፊዎቹ ቻርተሩ የደረሳቸው እዛው በስብሰባው ላይ ስለነበር ከማድመጥ በዘለለ፣ ተዘጋጅተው ሃሳባቸውን እንዲሰጡ አልቻሉም ነበር። “ጊዜ ወስደን መወያየት ያስፈልጋል” በሚል የተነሱ ሃሳቦች የትንሽ አባላት ሃሳብ ነው በሚል እንዲጣሉ እና ቀጥታ ወደ ውይይት እንዲገባ ነበር የተደረገው።
ስለዚህ ቻርተሩ በተለያዩ ኃይሎች ውይይት እና የጋራ ሰምምነት የመጣ ሳይሆን ቀድመው በብሔር-ተኮር እና የመገንጠል ጥያቄ ላይ ተመስርተው የተዋጉ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ “የአሸናፊዎች የጋራ ስምምነት” መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። ከግንቦት 24 እስከ 28፣ 1983 ዓ.ም የተደረገው ጉባኤ ባለቀለት ጉዳይ ላይ እውቅና የተሰጠበት ለመሆኑ ብዙ አመላካች ኩነቶች አሉ።

4. የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት – የተለያዩ ፖለቲካ ሃይሎች ማፈግፈግ
የሽግግር ቻርተሩ ለሕገ መንግስቱ ዋነኛ ምንጭ ነበር – አንድም ይዘቱ በሕገ መንግስቱ ላይ ከነበረው ተጽህኖ፣ ሌላም ለሽግግር ምክር ቤቱ ሕገ መንግስቱን ከማርቀቅ እና ከማውጣጥ ጋር በተያያዘ የሰጠው ስልጣን።
የሽግግር ጊዜ ምክር ቤቱ አንዱ እና ዋነኛው ኃላፊነት ሕገ መንግስት የሚያረቅ የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም ነበር። በሽግግር ጊዜ ምክር ቤቱ የወጣው እና የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን የተመሠረተበት አዋጅ (24/84)፤ ኮሚሽኑ ሕገ መንግስቱን “ከቻርተሩ መንፈስ ጋር ባልተቃረነ ሁኔታ” እንዲያረቅቅ ኃላፊነት ጥሎበታል። ይሄም ሕገ መንግስቱ ቻርተሩን ካወጡት ኃይሎች ፍላጎት እንዳያፈነግጥ፣ እና ይዘቱም ቀድሞ የተወሰነ እንደነበር ያሳያል።

የሽግግር ቻርተሩ የመሠረተው የሽግግር መንግስት አወቃቀር እና ለሽግግሩ ያስቀመጣቸው ዋነኛ ምሰሶዎች – ፓርላሜንታዊ የመንግስት አወቃቀር (ክፍል 3) እና፣ እስከ መገንጠል የሚደርስ የብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር የቡድን መብት ብሎም “የብሔር አሰፋፈሮችን” መሰረት ያደረገ የፌደራላዊ አሰተዳደርያዊ ክልሎች (አንቀጽ 2 እና 13) በኃላ ላይ በጸደቀው ሕገ መንግስት፣ ብሎም በመሰረተው የኢፌድሪ መንግስትም ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል። የሕገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባል እና ሕገ መንግስቱን ያወጣው/ያጸደቀው የሕገ መንግስት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የሽግግር ቻርተሩ የሕገ መንግስቱ ዋነኛ መሠረት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
የተቋቋመው የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ተጠያቂነት ለሽግግር ምክር ቤቱ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ የሚቀርብለትን ረቂቅ ሕገ መንግስት የማጽደቅ (adopt የማድረግ) ስልጣኑ ነበረው።

የሽግግር ምክር ቤቱ ከመጀመሪያ በኢሕአዴግ ተጽህኖ ስር መሆኑ ግልጽ ነበር። የሽግግር ምክር ቤቱን መቀመጫ ያደላደሉት የኢሕአዴግ እንዲሁም የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤው ሊቀመንበር ብሎም የጊዜያዊ መንግስቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ። ከነበሩት 87 ወንበሮች አብላጫውን ያየዙት ኢሕአዴግ (32 ወንበር) እና ኦነግ (12 ወንበር) ነበሩ። ሊቀ መንበሩ ድልድሉን ባደረጉበት ጊዜ “የተለያዩ አመለካከቶች ይወከላሉ” ከሚል በዘለለ በምን መስፈርት መቀመጫዎቹ እንደተደለደሉ እዚህ ግባ የሚባል ማብራሪያ አልሰጡም። ወደ ፊት ሊመጡ ለሚችሉ እና ላልተወከሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚል 6 ወንበሮች ያለ ተወካይ ባዶ ሆነው የቆዩ ሲሆን የተያዙት ወንበሮች 81ዱ ብቻ ነበሩ።

ያም ሆኖ ምክር ቤቱ እንደአጀማመሩ አልቀጠለም። በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሰሚነት የነበራቸው ድርጅቶች ከምክር ቤቱ እና ከሽግግር አስተዳደሩ በመውጣጥ ሕገ መንግስቱን ከማርቀቅ እራሳቸውን አግልለዋል። በተለይም ኦነግ እራሳቸውን ካገለሉ ሃይሎች ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ነበር። የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች እና ልኢቃን ከሽግግር ምክር ቤቱ ለመውጣታቸው የነበራቸው ምክንያት ያደረባቸው የመገለል ስሜት ብቻ ሳይሆን ምክር ቤቱና የሕገ መንግስት የማርቀቅ ሒደቱ በኢሕአዲግ ተጽህኖ ውስጥ መውደቁ ነበር። ያለምንም ተጽህኖ በምክር ቤቱ ውስጥ በመቆየት ለሒደቱ እውቅና ላለመስጠጥ ለቀው ወጥተዋል።
ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኃላ በተለያዩ ጊዜዎች የሒደቱ ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ጥሎ መውጣጥ አንዱ የሒደቱን አሳታፊነት አጠያያቂ ካደረጉት ኩነቶች ውስጥ ነበር።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com