የጎሳ ፖለቲካና ሃይማኖት ዴሞክራሲ ማጎናፀፍ ይችላሉን?

Views: 59

በብሔር ልዩነት ሥም መከፋፈልና መናቆር የኢትዮጵያ የየእለት ዜና ከሆነ ሰነባብቷል። አልፎም የብዙ ንጹሐን ዜጎች ሕይወት በአሳዛኝ መንገድ ተነጥቋል። በዚህ አጥፊዎች በዚህ መጠን በከፉበት ጊዜ ሰከን ብለው ማሰብ የሚገባቸው ፖለቲከኞች የወከባው አቀንቃኝና መሪ ሆነው ይታያሉ። ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደውም የጎሰኝነትን ጥላ ሥልጣን ማግኛ ያደረጉት ይመስላል። ጁዋር ሳዲቅ ደግሞ ከዚህ የባሰ በሃይማኖት ሥም የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል አስጊ እንደሆኑ አንስተዋል። የጎሳም ሆነ የሃይማኖት ፖለቲካ ዴሞክራሲን አያጎናጽፉንም ሲሉም ይሞግታሉ።

በአገራችን ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ የጎሳ ፖለቲካ እያየለ በመምጣቱ የጎሳ ፖለቲካ ለአገሪቱ እንደ ዋና ፖለቲካ አማራጭ እየተወሰደ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ማሰለፍ ችሏል። በዚህም ምክንያት በአገራችን ትልቅ የፖለቲካ እሳት እየተንቀለቀለ፣ ገና ሳይበርድ የሃይማኖት ፖለቲከኞችም የአገሪቱ ፓርላማና ጎዳናዎች በስብከት ለማጦዝ ‹‹እዛ ማዶ እንደምናችሁ! እዚህ ማዶ እንደምናችሁ! ይኸው አሁንማ መጣንላችሁ፤ በፓርላማ ስብከት ትሰማላችሁ›› እየተባልን ነው።

ወደ ሃይማኖት ፖለቲከኞች በር ማንኳኳት ከማለፋችን በፊት የጎሳ ፖለቲካ እንዴት ሊያይል ቻለ? ለመሆኑ ምንስ ቢያይል ዴሞክራሲ ማምጣትስ ይችላልን? ለዴሞክራሲ የተመረጠው የፖለቲካ አደረጃጀትስ የትኛው ነው? የሚሉትን እያፍታታን እንመልከት።

የጎሳ ፖለቲካ ለምን አየለ?
የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ በዛ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ደጋፊ የሚያፈሩት አሳማኝ አግባቢ በሆኑ በዴሞክራሲ መርሆች ዙሪያ አይደለም። ይልቁንም አንድን ብሔር በመጥላት፤ በሕዝቡን ስሱ ጎን በመግባት እንደ ተገደልክ፣ ተጨቆንክ፣ ተገፋህ ወዘተ በሚል ስሜቶችን በሚኮርኮሩ ፅንፍ በያዙ ትርክቶች የተቃኘ ስልት ነው። እነዚህ ስብስቦች ራሳቸው እንደ ዱር አራዊት በአንድ ስፍራ ክበብ የሠሩ ናቸው። ምክንያቱም የጎሳ ፖለቲከኞች እነሱ ከሚሉት ማኅበረሰብ ውጪ፣ እነሱ ከሚያወሩት ቋንቋ ውጪ፣ ከእነርሱ ዘር ውጪ ለሌላው ማኅበረሰብ፤ ነዋሪ ዝግ ስለሆነ በአንድ አጥር የተከበበ ነው።
ይሄ ደግሞ አንበሳ ግቢ እንደመግባት በሉት። እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመመሥረትም ጋር ይሁን ከአስተሳሰቡ ጋር ትልቅ ፀብ ይፈጥራል።

ዛሬ በአገራችን የምናየው የፖለቲካ ምስቅልቅል ይህ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያመጣው ወረርሽኝ በሽታ መሆኑ መካድ አይቻልም። አንዱ ጎሳ ሌላውን ጎሳ የሚያፈናቅልበት፤ የሚገድልበት፤ የሚሰድብበት፤ ዛሬ ወደለየለት ጭካኔ የገባንበት መስመር ይኸው ገና ከጋርዪሻዊ አስተሳሰብ ያልወጣ ወንዜነት፤ መንደራዊነት እና ጎሰኝነት ያመጣው የፖለቲካ ጣጣ ነው ባይ ነኝ።

በመተከል፣ በጉጂ፣ በወለጋ እና የሰሞነኛው የአጣዬ የሸዋሮቢት እና የከሚሴው ተግባር ከዚህ ከፅንፍ ጎሰኝነት ጋር የሚያያዝ ነው። የፓርላማውን ውሎ ስንከታተል የመንግሥት አካላት በራሱ የጎሳ የመንደር አስተሳሰብ ውስጥ ምን ያህል ጠልቀው እንደገቡ የሰሞኑ የ11ኛው መደበኛ የፓርላማ ስብሰባ ውሎ በራሱ ለምስክርነት በቂ ነው። በዚህ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ስለአማራና ኦሮሞ ለተነሱ የምክር ቤት አባላት የሰጡት ምላሽ ተስማምቶኛል። ‹‹ኢትዮጵያን መገንባት ከተፈለገ የመንደር አስተሳሰብ ይዞ አይቻልም››

በአንጻሩ ግን የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሰላም ማስከበሩ ቅድሚያ ሊሰጡት እንደሚገባ እና በዚህ ዙሪያ በመንግሥታቸው ያለው ንዝህላልነትም መቅረፍ እንዳለባቸው የማላልፈው ጉዳይ ነው።
ለዚህ ነው የጎሳ ፖለቲካ አመርረን መታገል አለብን የምለው። ምክንያቱም ከጎሳ አስተሳሰብ የወጣ ፖለቲካ ብንከተል ዛሬ አንድ ሰው ሲገደል ‹የኔ ጎሳ ነው! አማራ ነው! ኦሮሞ ነው!› ብለን ዘር መቁጠር ውስጥ አንገባም ነበር። ከእኛ ሊጠበቅ የሚችለው ድርጊት ፈፃሚው ከታወቀ እንዲቀጣ መገፋፋት፤ ለሞተው አካል ፍትህ እንዲያገኝ ማድረግ እና የሞተው ሰው እስከሆነ ድረስ አብሮ ማዘን ነበር።

ግን አሁን ላይ የሞተው አማራ ከሆነ፤ የተወሰነው ያዝናል ሌላው ደግሞ ‹‹ከኔ ወገን አይደለም።›› ይላል። ኦሮሞ ሲሞት የተወሰነው ያለቅሳል ሌላው ‹‹ከእኔ ወገን አይደለም።›› ብሎ ቸል ይላል። ይሄ ነው የጎሳ ፓለቲካ ጭካኔ። የጎሳ ፖለቲካችን ካልቀየርን ገና ብዙ መጥፎ ምርት መሰብሰባችን የሚቀር አይሆንም። በዛ ላይ የሃይማኖት ፓለቲካ ሲጨመር ፖለቲካው ‹እስፕሪስ› ሆኖ ለሽምግልናም፤ ለጥንቆላም የማይሆን ውስብስብ ወደሆነ ነገር እንደሚገባ መገመት ከባድ አይሆንም።

ዴሞክራሲ በባህሪው ባስቀመጠው መርህ የሚጠቀም አካታች፣ ግልፅ የፖለቲካ አካሄድን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ዘይቤ ነው። በዚህ መርህ መሠረትም የሰው ልጅን በጎሳና በመንደር አይከፈፍልም። ምክንያቱም የሚከተለው ሳይንሳዊ መንግሥት ነው። ኹለቱ የጎሳ እና የሃይማኖት ፖለቲከኞች ከዚህ የራቁ ናቸው፤ እጅግ ኋላቀር።

ለምሳሌ ኦፌኮ እና ኦነግ እንውሰድ። ኹለቱም የኦሮሞ ማኅበረሰብ የፖለቲካ መብት ለማስከበር ተብለው የተቋቋሙ ናቸው። እንዲሁም ደግሞ ሌሎች የአማራ ድርጅቶችን ትተን አብንን እንውሰድ። አብን ለአማራ ሕዝብ ፖለቲካ ተብሎ የተቋቋመ ድርጅት ነው። እንደውም ምን ይላል ‹አንድ አማራ ለሁሉ አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ›› ኦብነግንም እንውሰድ ካልን፤ ለዛውም ወርዶ ስለኦጋዴን ሕዝብ የፖለቲካ ነፃነት ነው የሚታገለው… ወዘተ ብዙ መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ ድርጅቶች ሁሉ ሲነሱ ለአንድ ለተወሰነ አካል ነው። እሱም አንድ ብሔር/ጎሳ ነው፤ አበቃ! ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሕውሃትን መመልከት በቂ ነው። ሕወሃት የጎሳ ፖለቲካ ይዞ ከመምጣቱ፣ የአንድም ጎሳ ነፃነትና መብት ሳያከብር ነው ወደግብአተ መሬቱ የወረደው።

ሌላ በጎሳ የተደራጁት እነዚህን መሰል ፓርቲዎችን ስንመለከት በውስጣቸው የሚኖረው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ አልያም የሌላ ክልል ተወላጅም ሆነ ነዋሪ ምንም ሊያካትት የሚችል ነገር የላቸውም። አግላይ ናቸው። ገና ከሥም ጀምሮ አንድን ዘውግ ይዞ የተነሳ ቡድን ‹ላንተ ነው የምታገለው!› ቢል ይሄ ቀልድ/ስላቅ መሆን አለበት፤ ነውም። ምክንያቱም የፓርቲው አመሠራረት ምልክዓ ምድራዊ አይደለም። ይልቁንም ቋንቋና ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው።

ግር እንዳይለን እንለየው። በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መሠረት የተደራጀ ፓርቲ ከሆነ በዛ ስር ያሉ ሁሉ የሚወክል፤ ለሁሉም የሚታገል፤ ሁሉንም የሚያካትት ይሆናል። ሥሙም ከማኅበረሰቡ ጋር ሊቀራረብ የሚችል፣ ፖሊሲውና ወዘተ ዝረዝሩን አካታች ያደርጋል። ይሄ ዴሞክራሲን ለማስፈን ቀላሉ ከሳይንሱ ጋር የሚዛመድ መንገድ ነው።

ሆኖም ቋንቋና ዘር መርጠው ሥም አውጥተው የተደራጁ ፓርቲዎች ከዴሞክራሲ ጋር ፈፅሞ ሊስማሙ አይችሉም። ምክንያቱም የሚከተሉት ጥላቻ እና ጠርዝ ላይ የቆመ የፖለቲካ መስመር ስለሆነ፣ ከዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር መዛመድ አይችሉም።

ዴሞክራሲ በስምምነት፣ በውል፤ በድርድር፣ ሰጥቶ በመቀበል፤ በሰላም፤ በምርጫ የሚያምን አስተሳሰብ ስለሆነ ኃይል መጠቀምን እንደአማራጭ አያቀርብም። ቢሆን እንኳ ሙጥጥ ብሎ ሲያልቅ ዴሞክራሲ ለማንበር አማራጭ ከሆነ ይሆናል። እሱም በሥልጣን ያለው አካል አስቸጋሪ አምባገነን ከሆነ ከሕዝብ ጋር በመሆን መፍትሄ የማበጀት የትግል ስልትን በመቀየስ የሚሆን ነው።

በአጭሩ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተለማጭ ነው፤ እንደሃይማኖት እና የጎሳ ፖለቲካግትር አይደለም። በተቃራኒው የጎሳ እና የሃይማኖት ፓርቲዎች/ፖለቲከኞች በጣም ጠብ አጫሪ፣ እኔ ያልኩት ካልተፈፀመ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ልክ ነው የሚል ግትር የሃውልት አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ለፀብ ቅርብ በሆነ ቀረርቶና ሽለላ በሚበዛበት የፖለቲካ አካሄድ፣ ‹ዴሞክራሲ አመጣለሁ! ምረጡኝ!› ማለት ዶሮ የፈላውን ውሃ ለምኔ ስትል ለገላሽ እንደተባለችው ይሆናል።
እርግጥ ነው የጎሳ ፖለቲካ ለ27 ዓመት በተሰበከባት ኢትዮጵያ አይመረጡም አልልም። ዴሞክራሲ ግን የለም። የኦሮሞ ጎሰኛ ፓርቲ ዛሬ ያለንበትን ዘመን በማይመጥን መልኩ ‹አማራ ነው የኦሮሞ ጠላት!› እያለ፤ አማራወም ‹በማንነቴ ምክንያት በኦሮሞ እየተጠቃሁ ነው!› እያለ፤ ትግሬው ‹የነፍጠኛ ስርአት!› እያለ አማራን እንደ ቁርስ ምሳ ራት ፕሮግራም እያደረገ ሲያጥላላ እየዋለ የሚያድር አገር፤ ቢረከቡ ምን አይነት ዴሞክራሲ ነው ሊያመጡ የሚችሉት?

ስለዚህ ከዴሞክራሲ የበለጠ አንግበውት፣ ሕዝቡን አሳምነው የመጡበት ብቸኛው መንገድ ሒሳብ ማወራረድ ነው። ይሄ ደግሞ ላለፉት የሕወሃት አገዛዝን መመልከት በቂ ይሆናል። አገሪቱንም ወደየትኛው አዘቅት ይዟት/እኛንም ይዞን እንደገባ ያየነው፤ የምናየውና እያየን ያለነው ሃቅ ነው።

ይገርመኛል! የዘውግ ፖለቲከኞች እናስተዳድረው የሚሉት ሕዝብ እንዲያስተዳድሩት እንኳ ቢሰጣቸው፤ እንደው ለሌላው ነዋሪ የሚሰጡት መብት፣ እኩልነትና የዴሞክራሲ እሴቶችን እንተወውና፤ በቀን እልፍ ጊዜ የሚምሉለትና እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንኳ ከማሰቃየትና መኖሪያውን ገሃነም ከማድረግ የማይመለሱ ጨካኝ መሆናቸው ነው።

ለምሳሌ ሕወሃት ላለፉት በርካታ ዓመታት ትግራይን ሲያስተዳድር ለራሱ የትግል ጓዶች እንኳን አልራራም። በክልሉ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ጋዜጠኞች፤ አክቲቪስቶች፤ የሃይማኖት አባቶች እንኳ አልተመለሰም። ክልሉን እንደፈለገ ሲያደርግ ሕዝቡን ግን በአምባገነንነት ደፍጥጦት ነበር። ሌሎች እነ ኦሕዴድ እና ብአዴንም አምባገነን የሚባሉ እንጂ ዴሞክራሲን የሚያውቁ አልነበሩም።

በአብዛኛው የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ የመናገር ነፃነት የሚገፉ፤ የመደራጀት ነፃነቱን የሚያመክኑ፤ ኮሮጆ ይቅርብኝ እስኪል እየገለበጡ ድምፁን የሚሰርቁት፤ የሥራ እድል እንኳ መፍጠር ያልቻሉ የሥልጣን ጥመኞች ሆነው ማለፋቸው የምናስታውሰው ነው።

ልብ በሉ! ሃምሳ የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉን። አብዛኞቹ የጎሳ ፓርቲዎች ናቸው። የጎሳ ፓርቲዎች ራስን በራስ ማስተዳደር ከሚሉና ከሌሎች ራሳቸው በራሳቸው ማስተዳደር ከሚፈልጉ ፓርቲዎች ጋር ግንባር/ውህደት አልያም ቅንጅት ፈጥሮ መሥራት ለምን አልቻሉም? ብቸኛው ምክንያት የጎሳ ድርጅቶች በባህሪያቸው ጩኸት መውደዳቸው ነው። ስለዚህ ጩኸታቸውን መቀማት ነው የሚመስላቸው። እንዲሁም ትኩረት የሚያደርጉት ዘላቂ ነገር ላይ ሳይሆን ጊዜያዊ ጭብጨባ ላይ ነው። በአብዛኛው በዚህ ምክንያት እርስ በእርሳቸው እንኳ አይስማሙም።

የቅርብ ጊዜው ዜና ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚን የመለኮስ ያህል አደገኛ እና አጃኢብ የሚያስብል ነገር ነው። ይኸውም ዋዜማ የተባለ ራዲዮ ባላፈው ሳምንት ባወጣው ዜና ብልፅግና ፓርቲ ለመጪው 6ተኛ ዙር አገር ዐቀፍ ምርጫ ወክለው ሊወዳደሩ የሚችሉ ታዋቂ ሰዎችን እያስመረጠ መሆኑ ነበር የገለጸው።

ችግሩ የሚታወቁ ሰዎችን በፖለቲካ መመልመሉ ላይ አልነበረም። ይልቁንም ተቀባይነት ይኖራቸዋል ያላቸው የሐይማኖት ሰዎችን ጭምር መመልመሉ ነው። በበኩሌ እምነትም እንደጎሳ ፖለቲካ ሁሉ ዴሞክራሲ ሊያመጣ አይችልም ከምለው የፖለቲካ ዘውግ አንዱ እንደሆነ እንደሆነ አምናሁ።

እምነቶች በባህሪያቸው መንፈሳዊ ናቸው። መንፈሳዊ ስትሆኑ ደግሞ ለመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ታደላላችሁ። ማለትም ሙስሊም የሆነ ለእስልምና ያደላል፤ ክርስትያን የሆነ ለክርስትና፤ ሌላውም እንደዛው። በግለሰብ ደረጃም ብንሄድ ሙስሊም ለሙስሊም ያደላል ክርስቲያንም እንዲሁ።

በዛ ላይ የእኛ አገር የእምነት ትርክቶች በራሳቸው ራሳቸው ከፖለቲካ ጋር እያዳቀሉ ከጎሳ በላይ የሚነታረኩ ናቸው። ይሄ የሆነው የእምነት ሰዎች የምንላቸው ግለሰቦች ከጀርባቸው ሲያራምዱት የነበረው፣ ሕዝቡንም ሲሰብኩት የነበረው፣ ለራሳቸው ዓላማ መገንቢያ አድርገው እንደተጠቀሙበት ነው እውነታው።

ስለዚህ ብልፅግና ፓርቲ የሄደበት የአግበስባሽነት ፖለቲካ ነገ ከነገ ወዲያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚሆን ሲሆን፣ አሁን ላይ አካሄዱም ምክንያታዊ አይደለም። ፖለቲከኛ ጠፍቶም አይደለ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ሰርፀ ፍሬስብሃት፤ አቡበከር አሕመድ፤ አሕመዲን ጀበል፤ ካሚል ሸምሱ፤ ሰኢድ አሕመድ የቀረቡት፣ ግልፅ የድምፅ ግዢ ንግድ ቢሆን እንጂ።

በእርግጥ መንግሥት የእጩነት ጥያቄ ያቀረበው ለተወሰኑት ቢሆንም፣ በግል ለመወዳደር ድፍረቱን አግኝተው ወደፊት የመጡት ግን መንግሥት ሃይማኖታዊ ሰዎችን መጥራቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ነው። ታዲያ ይሄ ነገር ከጎሳ እና ከሃይማኖት ፖለቲካው ሲደመር ‹በይ! ሴኩላሪዝም አፈርድሜ በላሽ!› ይሆናል።

መርህ አልባ ፖለቲካ መዘዙ ብዙ ነው። ከላይ የሃይማኖት ሰዎች ያልናቸው ፖለቲከኞች በተለያየ ዘውግ፤ መደበቂያ ምሽግ ይዘው ነው ፖለቲካን የሚቀላቀሉት። ስለዚህ በእምነትና በጎሳ መደራጀት ለአገራችን አዲስ ውጥረት ነው ባይ ነኝ። ስጋቱና አደጋውን አብረን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

አማራጭ?
እንደእኔ ለኢትዮጵያ ማስታገሻ ሳይሆን እንደ ዘላቂ ፍቱን መድኃኒት ነው ብዬ የማምነው ዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊነት/ኅብረብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲን ነው። ዘር፣ ቋንቋ፣ ጾታን መሠረት ሳያደርግ ዜግነት፤ አብሮነትን/ወንድማማችነት፤ እኩልነት፤ ፍትሃዊነትን እና ሁሉንም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደር ኢትዮጵያዊነትን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ ፓርቲ ብቻ የፖለቲካ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለመገንባት የበለጠ ቅርብ ነው።

እንዲያ ሲሆን ሌላው ቢቀር የሚነሳው አንድን ጎሳ ብሎ አይደለም። ኢትዮጵያውያንን እወክላለሁ ብሎ ሲነሳ ለጆሮም ደስ ይላል። ‹ከፍትፍቱ ፊቱ› እንደሚባለው በዜጎች መካከል መራራቅና ጥላቻ እንዳይኖር በማድረግ አንድ ያደርጋል። ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ እርስ በእርሱ እየተማመነ ሲመጣ ለጋራ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲ አብሮ ተሰልፎ አልበጀኸንም ማለት ይጀምራል። አልያም ተመካክሮ በካርዱ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል።
ስለዚህ ‹‹የጎሳ ፖለቲካ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና ወይም የኢኮኖሚ እድገት ያመጣል› ማለት ከበሬ ወተት አልያም እንቁላል መጠበቅ ነው። ኢትዮጵያችን ለዘለአለም ትኑር !!!


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com