ማንነትዎ፤ ‹ዲጂታል› ወይስ ‹አናሎግ›?

Views: 52

የቡድን እና የግል ማንነት ጽንሰ ሐሳብ በማኅበረሰብ ጥናት ዓውድ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ከመቶ ዓመታት በላይ ተሸግሯል የሚሉት አዲሱ ደረሰ፥ ጥራዝ ነጠቅ የማንነት ትንተና ያስከተለው አላልቅ ያለ የማንነት ፍለጋን በተመለከተ ጽሁፋቸው ዳስሳ ያደርጋል።

የቡድን እና የግል ማንነት የማኅበረሰብንም የግለሰብንም ባህሪ ለመተንተን የሚያስችል የጽንሰ ሐሳብ መዋቅር ሆኖ አገልግሏል። የማኅበረሰብን ባህሪ ለመረዳት ስናውለው ግለሰብነት ወይም ቡድናዊነት የተንሰራፋበት ማኅበረሰብ እያልን እንገለገልበታለን። የግለሰቦችን ባህሪ ለመረዳት ስናውለው ደግሞ በግሉ ሐሳብ የሚመራ አሊያም በቡድን ሐሳብ የሚመራ ግለሰብ እንላለን። በሚሼል ጄልፋንድ እና በሌሎች ተሰርቶ ግለሰባዊነት እና ቡድናዊነት በሚል በ2004 (እ.አ.አ.) በ‹‹ሪሰርችጌት›› ላይ የታተመ አንድ ጥናት እንደማስረጃ እየተጠቀምን የቡድን እና የግል ማንነቶችን እንደማኅበረሰብ መገለጫነታቸው ይዘን እንቀጥላለን።

ግለሰባዊነት እና ቡድናዊነት
ግለሰባዊነት እና ቡድናዊነት የተንሰራፋባቸውን ማኅበረሰቦች በዋንኛነት አራት መገለጫዎች እንደሏቸው ጥናቱ ያነሳል። የግለሰብ ማንነት ባለቤቶች፤ ማንነታቸው ገለልተኛ እና እራሱን የቻለ ነው ብለው የሚያስቡ፤ በግላቸው ማሳካት የሚያስቡት ዓላማ ያላቸው፤ ማኅበራዊ ባህሪያቸው በግል እምነት ወይም አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ እና ከሌሎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በምክንያታዊነት ላይ ብቻ ተመስርተው የሚያጤኑ ናቸው ይሏቸዋል። እኔ እራሴን የቻልኩኝ ገለልተኛ ፍጡር ነኝ በሚለው አመለካከታቸውም፤ ግለሰብነት የተንሰራፋበት ማንነት ‹ዲጂታል› ነው ይባልለታል።

በአንጻሩ ቡድናዊነት የተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች ማንነታችን ከቡድናችን የተቀዳ ነው ብለው የሚያስቡ፤ የግል የሚሉትና ማሳካት የሚሹት ዓላማ የሌላቸው ወይም ዓላማቸው ከቡድናቸው የተቀዳ እንዲሆን የሚሹ፤ ማኅበራዊ ባህሪያቶቻቸውን ቡድናቸው እስኪያጸድቀው ለመተግበር የሚቸገሩ፤ እና ከሌሎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ለቡድናቸው ከሚያመጣው ጥቅምና ጉዳት አንጻር ብቻ የሚመዝኑ ናቸው ይሏቸዋል። ማንነታቸው ምሉዕ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ሌሎች ላይ በመመስረቱም እነዚህኛዎቹ ‹አናሎግ› ማንነት ያላቸው ናቸው ይባልላቸዋል።

ቡድናውያን በዙሪያቸው ካሉ ግለሰቦች፤ ከተፈጥሮ እና ሌሎች ውጪያዊ ሁኔታዎች ጋር እጅ ከፍተኛ የስሜት እና የቁስ ጥገኝነት ይሰተዋልባቸዋል። ይህ ማንነታቸው በርግጥ ያገኙትን ለማካፈል እና አብሮ ለመጠቀም ባላቸው ባህሪ እንዲመሰገኑ ያደርጋቸዋል። በዚያው መጠን ግለሰባውያን በዙሪያቸው ካሉ ሌሎች ግለሰቦች፤ ተፈጥሮም ሆነ ሁኔታዎች ጋር ያላቸው የላላ የስሜት ጥገኝነት በእነዚህ ውጪያዊ ኀይሎች ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቁ እና ዓላማቸውን እንዲያሳኩ እድልን ያጎናጽፋቸዋል።

ቡድናውያንን ለማስደሰት ከባድ ነው። ምክንያቱም ደስታቸው ቡድናቸውን ማደሰቱን ካላረጋገጡ አይደሰቱም። ስለዚህ ለመቅረብ ከባድ ናቸው። ቀርበዋቸው፤ ትንሽ እውቅናን መስጠት ከጀመሩ ግን ውስጣቸው ሩርሩህ ዘለቂ ወዳጅነትን ሊመሰርቱባቸው የሚችሉባቸው ዓይነት ናቸው። ግለሰባውያንን ለመቅረብ ችግር የለም። ጨዋታን ከማንኛውም አካል ጋር ቀለል አድርገው መጀመርን ያውቁበታል። ይህ ማንነታቸው የሚያጎናጽፋቸው ክህሎት የትም ወስደው ቢጥሏቸው ሕይወታቸውን አቆይተው ዓላማቸውን አሳክተው መውጣትን ያውቁበታል። ነገር ግን ከተወሰነ መስመር በኋላ ወደ ውስጥ አያስገቡም፤ የማንነታቸው አስኳሉ በጠንካራ ግድግዳ የታጠረ ነው።

ቡድናውያን ከሌሎች ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት ቡድናቸውን መጥቀም አለመጥቀሙን በማረጋገጥ ይመስላል። በዚህ ረገድ ቡድናውያን ‹‹የእኔ ቡድን አባል ነው›› ብለው ለሚያስቡት ማናቸውም አካል መስዋትነትን ለመክፈል ዝግጁ ናቸው። ሆኖም ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ለቡድናቸው ጥቅም እስካመጣ ድረስ የሚተገበር አንጂ ሰብኣዊ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ላይሆን ይችላል። ይህ አመለካከታቸው በእኩልነት እና ፍትሓዊነት ላይ ባላቸው አመለካከት ፍንትው ብሎ ይታያል።

ቡድናውያን ሥልጣንን በቡድናቸው ውስጥ ሲከፋፈሉ እኩልነትን መሰረት ያደርጋሉ። ሥልጣን ለሁሉም አባላት በእኩል ይካፈል እንደማለት ነው። የእነሱ ቡድን ከሌሎች ቡድኖች ጋር ሥልጣን ሲካፈል ግን ፍትሓዊ ይሁን ይላሉ- ይህም ሥልጣን እንደብዛታችን፣ እንደስፋት እና ወርዳችን እንጂ አኩል እኩል መካፈል የለበትም እንደማለት ነው። ግለሰባውያን በዚህ ጥርት ያለ አቋም ነው ያላቸው- ማንኛውም ነገር ፍትሓዊ ይሁን የሚል።

ሌላኛው መለኪያ ደግሞ ኹለቱ ማንነቶች ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያርጉትን ግንኙነት የሚገመግም ነው። ቡድናውያን ሁሉም ማኅበራዊ ባህሪያቶቻቸው ከማኅበረሰቡ በሚያገኙት የግምገማ ውጤት መሰረት እያወጡ የሚተገብሩት ነው። የጋብቻ፣ የቀብር አሊያም ሌሎች ማኅበራዊ እቅዶቻቸው ግዴታ ከእነሱ በፊት የነበረውን ትውልድ መምሰል እንዳለበት ያስባሉ። ለእርሱም ይተጋሉ- ያንን የማኅበረሰብ ጭብጨባ ለማግኘት። ‹‹የራሴን ጋብቻ እኔ ራሴ አቅጄ ራሴ እተገብራለው›› የሚል ሐሳብ አይታሰብም።

ግለሰባውያን ሙሉ አትኩሮቶቻቸው ግቦቻቸው ላይ ናቸው። የራሳቸውን እቅድ ይሠራሉ፤ ይተገብራሉም። ማኅበረሰቡ ካጸደቀው እሰየው፤ ካላጸደቀው የማንነታቸው አስኳል በጠንካራ ግድግዳዎች የታጠረ ነው፤ አይጎዳም። ማኅበረሰቡ ከዚህ ቀደም የተገበሩት እቅድ ትክክለኛነት ላይ ሲከራከር፤ እነሱ ሌላ እቅድ ላይ ናቸው።

ሌላኛው የማንነቶቹ መመዘኛ መለኪያ ደግሞ ማኅበራዊ መስተጋብርን ይመለከታል። ግለሰባውያን ማንኛውም መስተጋብራቸው በወጪ – ገቢ ትንተና ላይ የተመሰረተ ነው። መስተጋብሮቻቸው እነርሱን አሊያም ሌላኛውን አካል አክሳሪ ነው ብለው ካሰቡ አይተገብሩትም። ቡድናውያን የሚያደርጓቸው መስተጋብሮች በሙሉ ዘላቂ ነው የሚል የዋህነት ይነበብበታል፤ በዚህም አክሳሪ የሚባሉ መስተጋብሮች ውስጥ ሲገቡ አይታወቃቸውም፤ ቢታወቃቸውም ስህተት ነው ብለው አያስቡም።

ከላይ ከተጠቀሱት አራት መገለጫ ባህሪያት በተጨማሪ ግለሰባዊነት እና ቡድናዊነት በአግድም እና ቋሚ ግንኙነትም ይተነተናል። ቡድናዊም ሆኑ ግለሰባዊ ማንነቶች በቋሚ እና አግድም መመዘኛ ሊተነተኑ ይችላሉ። አግድም እና ቋሚ ቡድናዊ አሊያ አግድም እና ቋሚ ግለሰባዊ እንደ ማለት ነው።

ቋሚዎች (ግለሰባዊም ይሁኑ ቡድናዊ) ማንነታቸው ከሌሎች ማንነት የተለየ እንደሆነ ያስባሉ። አግድሞቹ ደግሞ (ግለሰባዊም ይሁኑ ቡድናዊ) ማንነታቸው ከሌሎች ጋር እኩል እንደሆነ ያስባሉ። አሜሪካውያን እና ፈረንሳውያን ለምሳሌ ምንም ያክል ለተቀረው የዓለም ማኅበረሰብ ግለሰባዊነት የተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች ተደርገው ቢሳሉም እነሱ ግን አንዳቸው ከሌላቸው ለይተው የሚያዩ፤ እንዲያውም በእነዚያ ልዩነቱን በፈጠሩት ማንነታቸው ላይ ተንተርሰው የሚመጻደቁም ናቸው።

ሕንዳውያን እና ቻይናውያን ምንም እንኳን ለተቀረው ዓለም ቡድናዊነት የተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች ሆነው ቢታዩም ቋሚ – ቡድናዊ ናቸው። አንዳቸውን ከሌላቸው የሚያስተሳስር ነገር እንደሌለ እና ልዩዎች ነን ብለው የሚያስቡ ናቸው። አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበትን ማንነታቸውንም አውጥተው ያስተዋውቋቸዋል፤ ሊመጻደቁባቸውም ይችላሉ።

አግድም ቡድናውያን እና የአግድም ግለሰባውያን ትንተና ግን ከዚህ ይለያል። እነዚህ ማኅበረሰቦች ልዩነት ቢኖራቸውም በእነሱና በሌሎች ማንነቶች መካከል እኩልነት እና የአግድሞሽ ግንኙነት እንዳለ የሚያስቡ ናቸው። በዚህ ረገድ የአውስትራሊያ እና የስዊድን ማኅረሰቦች በአግድም ግለሰባዊ ማኅበረሰብነት ሲጠቀሱ፤ በእስራኤል የሚገኙት ኪቢቱስ እና ኤስኪሞ ማኅበረሰቦች ደግሞ በአግድሞሽ ቡድናዊ ማኅበረሰብነት ይጠቀሳሉ። በአንድ አገር የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ለመተንተን የአግድሞሹን የትንተና መንገድ እንደተጠቀምን ልብ ይሏል።

የታላላቆቻችን የማንነት ትንተና ስህተት እና መዘዙ
እኔ ስህተቶቹን ብቻ ለመጠቆም እሞክራለው፤ መዘዙን እርስዎ አንባቢው በዐይንዎ እያዩት እየኖሩት ስለሆነ ራስዎ እንዲመዙት እጋብዛለው። የግል እና የቡድን ማንነቶች ተቃራኒዎች አይደሉም፤ ተከታትለው የሚመጡም አይደሉም። ኹለቱም ማኅበረሰብን ለመረዳት የሚያገለግሉ እና የማይነጣጥሉ ጎኖች ናቸው። ልክ ወንድና ሴት ተቃራኒዎች እንዳልሆኑት፤ ተከታትለውም እንደማይመጡ። የሰው ዘርን ለመረዳት እኩል ድርሻ ያላቸው ማንነቶች እና ምንነቶች ናቸው።
ትልቁ የታላላቆቻችን – በተለይ የጎጥ ፖለቲካ አድናቂዎች ስህተት እዚሁ ጋር ይጀምራል። ያነበብን፤ ዲሞክራሲያዊ እና ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ሆደ ሰፊዎች ነን በሚል የሚመጻደቁ ሹማምንት ባሉበት በዚህ ዘመን የሚደረጉ ክርክሮች እንኳን የቡድን ወይስ የግል ማንነት ይቀድማል አሊያም የዚህ ማኅበረሰብ መገለጫ የቡድን ወይንስ የግል ማንነት ነው በሚል ጊዜ ያለፈባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። የማኅበረሰብ ጥናት ሳይንቲስቶች አስረግጠው የሚነግሩን ይህንኑ ነው – የቡድን እና የግል ማንነቶች ተቃራኒዎች አይደሉም፤ አይሽቀዳደሙም።

ኹለተኛው ስህተቱ ደግሞ የቋሚውን የትንተና ዓይነት የተጠቀመ መምሰሉ ነው። ቋሚው አስተሳሰብ፤ አንድ ማኅበረሰብ ግለሰባዊም ይሁን ቡድናዊ ማንነቱ ከሌሎች ጋር እኩል እንደሆነ ሳይሆን የተለየ እንደሆነ የሚያስብ፤ ልዩነቱንም አጉልቶ የሚያስተዋውቅ እንዲያውም የሚመጻደቁበት ዓይነት ነው። ከላይ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ በግለሰባዊነት፤ የስዊድን እና የአውስትራሊያን ማኅረሰቦች ደግሞ በቋሚ ቡድናዊነት እንደፈረጅናቸው ማለት ነው።

ይህ ትንተና ብዙ ጊዜ ለኹለት አገር ሕዝቦች የምንጠቀመው መሆኑን ልብ ይሏል። ይህንን ትንተና ለአማራ፣ ለኦሮሞ፣ ለትግሬ፣ ለአፋር፣ ለሱማሌ እና ለሌሎች ማኅበረሰቦች መጠቀማችን ትልቁ ስህተት ነው። የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ አሊያም የጋሞ ማኅበረሰቦች የጎንዮሽ ግንኙነት ያላቸው እና አንዳቸው ማንነታቸውን ከሌላኛው ጋር እኩል እንደሆነ የሚያስቡ ተደርገው የሚያስቡ ሳይሆን ራሳቸውን የቻሉ፤ ከሌላኛው ማኅበረሰብ ጋር ፍጹም የተለዩ ናቸው በሚል እንዲሳሉ የተደረጉበት መንገድ ሌላኛው እና ትልቁ ስህተቱ ነው። የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እንደ አውስትራያና ስዊድን ሳይሆኑ በእስራኤል እንደሚገኙት ኪቢቱስ እና ኤስኪሞ ማኅበረሰቦች ናቸው የሚል ግንዛቤ እጥረት የተንሰራፋበት ይመስላል።
ሌላኛው በርግጥ ከማኅበረሰብ ጥናቱ ውስንነት የሚመነጭ ቢሆንም ተጽዕኖው ግን አልቀረልንም። ለመሆኑ አንድ ማኅበረሰብ እንደልቡ እንዳይንቀሳቀስ ባልተፈቀደለት ሁኔታ እንዴት ነው ቡድናዊ፤ አሊያም ግለሰባዊ ነው የምንለው።

በትክክል ለዳኝነት የሚበቁት በአሁን ምርጫ የተሳተፉ አሜሪካውያን ይመስሉኛል። በ2020 (እ.አ.አ.) የአሜሪካ ምርጫ የነጭ የበላይነትን፤ የአሜሪካን እና አሜሪካውያንን የበላይነትን እንደሚያስቀድም በግላጭ የተናገረን ፕሬዝዳንት፤ 71 ሚሊዮን የሚሆኑ ነጭ አሜሪካውያን በግላጭ ወጥተው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ሌሎች ከ80 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ ያለምንም ፍራቻ እና ተጽዕኖ ወጥተው ኅብረ ብሔራዊት አሜሪካ ትሻለናለች ብለዋል።

ሕንዳውያንን ለመዳኘት የሚያስችል በቂ ነጻነት ያላቸው ይመስለኛል። ከቻይና ወይም ከሰሜን ኮሪያ የሚሰበሰበው መረጃ (‹ዳታ›) ግን የኮሚኒስት ፓርቲው ስለፈለገ ይሁን ግለሰቦች ስለፈለጉ ቡድናዊ የሆኑት ግልጽ ማድረግ የሚችል አይመስለኝም። በእኛስ አገር ቢሆን በቅርጫት መታጠሩን አሽቀንጥረው ጥለው እንደ ነጻ ወፍ ያለ ወሰን ስለመብረር ማታ ማታ ብርድ ልብሳቸው ውስጥ ሆነው የሚያስቡ ምን ያክል ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ አሊያም ሲዳምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በምን እናውቃለን።

ለጠቅላላ ግንዛቤ ያክል የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በአንድ አግድም መስመር ላይ በእኩልነት ያለን እና እጅግ በጣም የተሳሰረ ማንነት ያለን ነን። ጠቅላዩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንኳን ለመፍረስ የሚያበቃ ያንን ሁሉ ድብደባ አገሪቱ የተቋቋመችው በማኅበረሰቦች መካከል ባለ ጠንካራ የአግድሞሽ ግንኙነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ለማንኛውም ‹‹እኔ ዲጂታል ነኝ። (ምጽ!)›› ግለሰባዊ መሆን አንገትን በሚያስደፋበት ዘመን፤ ቡድናዊ መሆን ብዙ ማበረታቻ በሚያሰጥበት ዘመን ወድጄ ፈቅጄ ነው የሆንኩት። ማንነቴን በጥቂቱ ለመረዳት አማራ፣ ኦሮሞ እንድልዎ አይጠብቁ፤ ወደዚሁ ጽሁፍ ተመልሰው ግለሰባዊ የሚሉትን አንቀጾች መልሰው ያንብቡ።
አዲሱ ደረሰን በኢሜል አድራሻቸው addisuderesse@gmail.com ማግኘት ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com