የኢኮኖሚያችን ነገር

Views: 55

ባለፈው ማክሰኞ 14/2013 ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ባለፉት ዓመታት የወጪ ንግድ ትልቅ ችግር ውስጥ እንደነበር እና ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሻሻል እንዳሳየ፣ ነገር ግን ኮቪድ፤ አንበጣ፣ ጎርፍና ከሁሉ በላይ ደግሞ ግጭት ማጋጠሙ የውጪ ንግዱን ለማሻሻል ጋሬጣ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ እንደ አገርም በግጭት ምክንያት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንደባከነ ገልጸዋል፡፡ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ የተሠሩ አመርቂ ሥራዎች ቢኖሩም በየጊዜው እየናረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ግን የኢኮኖሚያችን አንድ ነቀርሳ ነው በማለት ለመፍታት መቸገራቸውን አንስተዋል፡፡ በእለቱ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያነሱዋቸውን ጉዳዮች ዳዊት አስታጥቄ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኢኮኖሚያዊ መስኮች ከብድር ጫና እስከ ወጪ ንግድ፣ከገቢ አሰባሰብ እስከ ዋጋ ግሽበት ያሉትን እና ሌሎች ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ዓመታት የወጪ ንግድ ትልቅ ችግር ውስጥ እንደነበር እና ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሻሻል እንዳሳየ ነገር ግን ኮቪድ ፤ አንበጣ፣ ጎርፍና ከሁሉ በላይ ደግሞ ግጭት ማጋጠሙ የውጪ ንግዱን ለማሻሻል ተጨማሪ ጋሬጣ እንደሆነ አንስተው ፤በተለይ እንደ አገርም በግጭት ምክንያት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንደባከነ ገልጸዋል። ይህን ሀብት ለልማት ማዋል ቢቻል የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል።
እነዚህን ጫናዎች ተቋቁመን ባለፈው ዓመት 6ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማረጋገጥ መቻሉን ፤ ይህም እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ አዎንታዊ እድገት ካስመዘገቡ ጥቂት አገራት መካከል እንድንሰለፍ ማስቻሉን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህን መመስከራቸውንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ሶስት አመታት ከገቢ አንጻር የተመዘገቡ ውጤቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲገልጹ በ2010 ፣ 176 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ይህ ገቢ በ 20 ቢሊየን አድጎ በ2011 ፣196 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በ2012 ደግሞ 228.9 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ መቻሉን እንዲሁም በያዝነው ስምንት ወራት 191 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አንስተው ነገር ግን ይህ እድገት በቂ ግን አይደለም በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
ገንዘብና ገንዘብ ነክ ስራዎች በተለመከተ ባለፉት ሶስት አመታት የገንዘብ ስርጭት በ15 በመቶ ማደጉን፤ ቁጠባ በ25 በመቶ ማደጉን፤የብድር አቅርቦት 38.4 በመቶ ማሳደግ መቻሉን፤ከምንም በላይ አሁን ላይ አገሪቱ ያለባትን የውጭ እዳ ጫና ባለፉት 3 ዓመታት ከነበረበት 37.6 በመቶ ወደ 26.8 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን እንደ ትልቅ ስኬት ማንሳት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ሌላ የገንዘብ ነክ ጉዳይ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ አዲስ የብር ኖት እንዲቀየር መደረጉ ሲሆን፣ አዲስ የገንዘብ ኖት እንዲቀየር በመደረጉ ብቻ 6.2 ሚሊዮን ዜጎች አካውንት መክፈታቸውን ፣ ይህ ቁጥርም አፍሪካ አገራት ሙሉ ዜጎቻቸው አካውንት ከፍተዋል እንደማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በዚህም 98 ቢሊዮን ብር በቁጠባ መልክ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በባንኮች የተሰበሰበውን አጠቃላይ ገንዘብ በተመለከተ በ2010 የኢትዮጵያ ባንኮች በአጠቃላይ 730 ቢሊዮን ብር መሰብሰባቸውን፤በ2011 ደግሞ 899 ቢሊዮን መሰብሰቡን እንዲሁም በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነጥብ አራት ትሪሊዮን ብር በባንኮች መሰብሰቡ አንስተው በያዝነው 2013 በስድስት ወር ብቻ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር በኢትዮጵያ ባንኮች መግባቱን ተናግረዋል።

የባንኮች ብድር ባለፉት ሶስት አመታት
በ2010 ፣ በብድር መልክ እንዲከፋፈል ታስቦ 170 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ለግል ሴክተር የሄደው 45 በመቶ ብቻ እንደሆነ አና 55 በመቶውን ድርሻ የወሰደው መንግስት እንደሆነ ገልጸው ፤በአመቱ 2011 የግሉን ሴክተር ለማነቃቃት በማለም 236 ቢሊዮን አበድረን፤ ከዚህ ውስጥ ለግሉ ሴክተር የተሰጠው 61 በመቶ ሲሆን መንግስት 39 በመቶውን ድርሻ ወስዷል ብለዋል።
በ 2012 ደግሞ 271 ቢሊዮን ብር አበድረናል፤ከዚህም ውስጥ የግሉ ሴክተር ድርሻ 70 በመቶ እነደነበር አንስተዋል። በያዝነው 2013 ስድስት ወር ብቻ 155 ቢሊዮን ተሰጥቷል፤ በዚህም 74 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ እነደሆነ አንስተዋል።

አሃዞቹ ምን ይናገራሉ?
የዋጋ ግሽበት የፈተነው ኢኮኖሚ
“ያልፈተናው የዋጋ ግሽበትን ነው፤ የዋጋ ግሽበት የኢኮኖሚያችን አንድ ነቀርሳ ነው፤ የሚያጠቃውም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ነው።መንግስት ይሄንን ችግር የሚፈታ የተለያየ ግብረ ሃይለ አደራጅቷል፤ በከተማው ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈታ ግብረ ሃይል ጭምር ተቋቁሟል” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

የዋጋ ግሽበቱ መሰረታዊ ተጽዕኖዎች ሲገለጹም፡- ምግብ ነክ ወጪ – ከ54 እስከ 60 በመቶ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፤ የቤት ኪራይ እስከ 20 በመቶ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፤ አልባሳት ከ5 እስከ 6 ያለውን አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል ብለው ጫናን ለመቀነስ ግን ሰራዎችን እየሰሩ እንደሆነ አንስተዋል። በዚህም
ነዳጅን ወገባችንን ከሚቆርጡ ነገሮች መካከል አንዱ ነዳጅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ ለነዳጅ በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ገልጸው ፤ነገር ግን ከጎረቤት አገራት አንጻር ነዳጅን በዝቅተኛ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን አብነት አንስተው አስረድተዋል።

በጎረቤት አገራት የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ በሊትር ከ 38 ብር አንስቶ እስከ 79 ብር እየተሸጠ መሆኑን ነገር ግን እኛ አገር አንድ ሊትር ነዳጅ 25.6 ብር እየቀረበ መሆኑን ፤ ይህም መንግስት ስለሚደጉም እንደሆነ እና ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ መንግሥት የ30 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን በዚህም ፤ በያዝነው ወር ብቻ 3 ቢሊዮን ብር መንግስት እዳ ውስጥ መጨመሩን አንስተዋል።

በአንድ ወር ለነዳጅ 3 ቢሊዮን ብር ድጎማ መንግስት እንደሚያደርግ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በሚጨምርበት ወቅትም ጭማሪውን እንዳለ መልቀቅ የዋጋ ግሽበት ስለሚያስከትል መንግስት የዋጋ ግሽበቱ እንዳይባባስ በሚል ብዙ ነገሮችን መሸከም እንዳለበት ወስኖ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።

እንዲህም ሆኖ እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት አስቸጋሪ መሆኑን፣ነገር ግን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚን በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ በአስር አመቱ የልማት እቅድ ላይ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው የልማት ዘርፍ አንዱ በሆነው የግብርናውን መስክ እንዲዘምን ማድረግ እንደሆነ ታምኖበት የተቀናጀ የመስኖ ልማትና ኩታ ገጠም ግብርናን ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የውጪ ንግድ ባለፉት 6 ወራት ያስገባው ግኝት በ 21 ከመቶ እድገት ማሳየቱን ፣ ይህም ካለፉት 20 ዓመታት በአማካኝ ከፍተኛው እንደሆነ አንስተዋል። በተለይም ወርቅ ከቡና በላይ ሆኖ ከፍተኛ የወጪ ንግድን ገቢን ማሳደጉን ገልጸው ይህም በታሪክ የመጀመሪያው የሆነበት ዓመት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በያዝነው አመት በ6 ወራት ውስጥ 1.54 ቢሊዮን ብር ከውጪ ንግድ ማግኘት መቻሏ ተነግሯል። የአገር ውስጥ ገቢ መጠን በ2010 ከነበረው 176.9 ቢሊዮን ብር፣ በዓመቱ በ20 ቢሊዮን ብር አድጎ በ2011ዓ.ም 196.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ በ2012ዓ.ም በ30 ቢሊዮን ብር አድጎ 228.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ 2013 በ8 ወር ብቻ 191 ቢሊዮን ብር ደርሷል (ይህ በ2010 ጠቅላላ ከተሰበሰበው 176.9 ቢሊዮን ብር ይበልጣል!)።

የንግድ ጉድለት (ወደ ውጪ የሚላከው ከውጪ ከሚገባው ሲቀነስ ማለት ነው!) በ2010ዓ.ም ከዜሮ በታች 14.7 ከመቶ የነበረ ሲሆን በ2011ዓ.ም በ1.7 ከመቶ ቀንሶ ከዜሮ በታች 13 ከመቶ ደርሷል፤ በ2012ዓ.ም በ2.9 ከመቶ ቀንሶ ከዜሮ በታች 10.1 ከመቶ ደርሷል! ይህ የሚያሳየው በ3 ዓመት ውስጥ በ4.6 ከመቶ እንዲቀንስ ሆኗል። ይህ ውጤት የውጪ ንግድ ማደግ (Export ከ3 ቢሊዮን ዶላር አልፏል) በተጨማሪም ከውጪ የሚገቡ ቁሳቁሶች ላይ ክትትል በመደረጉ ነው።

የውጪ እዳ ጫና ከጠቅላላው ሃገራዊ ምርት ያለው ልዩነት በ2010ዓ.ም የነበረው 37.6 ከመቶ የነበረ ሲሆን በ2011ዓ.ም ወደ 29.4 ከመቶ ቀንሶ በ2012ዓ.ም 26.8 ከመቶ ደርሷል። ይህ ውጤት የሚያሳየው በ3 ዓመት ውስጥ በ10 ከመቶ የውጪ እዳ ጫና ከጠቅላላው ሃገራዊ ምርት ያለው ልዩነት ቀንሷል። የዚህ ውጤት መሰረታዊ እርምጃ የብድር ስረዛ እና ሽግሽግ ድርድር፤ የመክፈል አቅምን ማሳደግ፤ ከፍተኛ ወለድ ያለው ብድርን በመቀነስ የመጣ ነው።

የገንዘብ አቅርቦት በ15 ከመቶ ሲያድግ የቁጠባ መጠን በ25 ከመቶ አድጓል! ባንኮች የነበራቸው ቁጠባ በ2010ዓ.ም የነበረው 730 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም በዓመቱ በ169 ቢሊዮን ብር አድጎ በ2011ዓ.ም 899 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ በ2012ዓ.ም በ141 ቢሊዮን ብር አድጎ 1.04 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፤ 2013 በ6 ወር ብቻ 1.2 ቢሊዮን ብር ትሪሊዮን ብር ደርሷል (ይህ በ2012 ጠቅላላ ዓመቱን በሙሉ በ2013 ዓ.ም በግማሽ ዓመት የተሰበሰበው 160 ቢሊዮን ብር ይበልጣል!)።

በተጨማሪም ገንዘብ ለውጡን ተከትሎ 6.2 ሚሊዮን ሰዎች አዳዲስ የባንክ አካውንት በመክፈታቸው ተጨማሪ 98 ቢሊዮን ብር ተቆጥቧል።
የኢንቨስትመንት ብድር አቅርቦት በ2010ዓ.ም የነበረው 170 ቢሊዮን ብር ብድር የቀረበ ሲሆን (ከጠቅላላ ብድሩ ውስጥ 45 ከመቶ ብቻ ነበር ለግል ሴክተሩ ቀርቦ የነበረው) ይህም በዓመቱ በ66 ቢሊዮን ብር አድጎ በ2011ዓ.ም 236 ቢሊዮን ብር ብድር ቀርቧል (ከጠቅላላ ብድሩ ውስጥ 61 ከመቶ ነበር ለግል ሴክተሩ ቀርቧል)፤ በ2012ዓ.ም በ35 ቢሊዮን ብር አድጎ 271 ቢሊዮን ብር ብድር ቀርቧል (ከጠቅላላ ብድሩ ውስጥ 70 ከመቶ ለግል ሴክተሩ ቀርቧል)፤ በ2013 በ6 ወር ብቻ 155 ቢሊዮን ብር ብድር ቀርቧል የግል ሴክተሩ ከ74 ከመቶ በላይ ድርሻ።

ይህ የሚያሳየው ቁጠባ አድጓል፤ የግል ሴክተሩ የሚያነሳው የኢንቨስትምንት አቅም በብድር አቅርቦት አድጓል፤ የካፒታል ወጪ በ3 ዓመት ውስጥ ከ97 ቢሊዮን ብር ወደ 160 ቢሊዮን ብር አድጓል፤ የሚታረስ መሬት መጠን እና በበጋ የግብርና ምርት መጠን አድጓል።

አንበጣ፤ ጎርፍ፤ ኮሮና እና ተደጋጋሚ ግጭት በመኖሩ የኢኮኖሚው እድገቱ በፈታናዎች ውስጥ ነው! ዜጎች ከውጪ የሚልኩት የውጪ ምንዛሬ ቀንሷል፤ የግጭት መብዛት የምርት መጠናችንን ቀንሷል፤ ከውጪ የሚገቡ ቁሶች ዋጋ መናር፤ የሎጀስቲክ እጥረት እንዲሁም የገበያው ሁኔታው ችግር ውስጥ በመሆኑ ከዋጋ ግሽበት በሚነሳው የኑሮ ውድነት ጨምሯል።

በቀጣይ የሃይል አቅርቦትን በማሻሻል፤ የምርታማነት ሁኔታን በማሻሻል፤ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን በማሻሻል፤ የገበያ ቁጥጥር በማድረግ፤ የፖለቲካ ሁኔታን በማሻሻል፤ ከውጪ የሚገቡ ቁሳቁሶችን በመተካት፤ ሙስናን በመቀነስ፤ ወዘተ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲኖር ማድረግ ይገባል እላለሁ።

የዋጋ ግሽበት ላለፉት 15 ዓመታት እየተደማመረ የመጣ ችግር ሲሆን ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኗል። ይህም የሚጎዳው ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለውን ሕብረተሰብ ነው። በአማካይ የምግብ ወጪ 54 በመቶ፣ የቤት ኪራይ 16-20 በመቶ፣ አልባሳት 5-6 በመቶ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሕብረተሰብ ክፍሎች ወጪ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ቢሰራባቸው 80 በመቶ ጫና እናቀላለን ብለን እናምናለን፣ ያንን የተመለከተ ሥራ እያከናወንን ነው። የግብይት ሰንሰለትን ለማሻሻል መንግሥት ከግሉ ዘርፍ እየገዛ ማሰራጨት ጀምሯል። ነገር ግን ገና በቂ አይደለም። ግሽበቱን ለመቆጣጠር በሺህ የሚቆጠሩ ስግብግብ ነጋዴዎችን የመቆጣጥር እና ርምጃ የመውሰድ ሥራ እየተሰራ ሲሆን፣ የጋራ ጥረትን ይሻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com