ሰላምና ምርጫ-2013

Views: 97

የኢትዮጵያ ስደስተኛው አገራዊ ምርጫ የምታካሂድበት መደበኛ ጊዜ 2012 ቢሆንም፣ ኮቪድ 19 ባስከተለው ስጋት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማካሄድ አልችልም ማለቱን ተከትሎ ወደ 2013 ተሸጋግሮ የፊታችን ግንቦት 28/2013 እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል። ይህንኑ ተከትሎ የምርጫ ቅድም ሂደቶች በባለ ድርሻ አካላት በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌላ እየተከናወኑ ነው።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የቀራት ጊዜ አንድ ወር ከአስር ቀን ነው። በቀሪዎቹ የ40 ቀናት የምርጫ ባለድርሻ አካላት ቅድመ ሥራዎችን እየሰሩ የሚቆዩበት ጊዜ ቢሆንም በአንዳንድ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች መደበኛ የምርጫ ቅድመ ሥራዎች በሙሉ አቅም እየተሰሩ እንዳልሆነ ባለ ድርሻ አካላት ያነሳሉ።

ከባለ ድርሻ አካላት በዋናነት የሚጠቀሱት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅድመ ሂደቱ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች የገጠማቸው እንቅፋት እንደነበር አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት ባነሳቻቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ፓርቲዎቹ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች የገጠማቸው ችግር እጩዎችን ሙሉ በሙለ ማስመዝገብ አለመቻል ነበር። እጩዎችን ለማስመዝገብ የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት ሆነውብናል ካሉት ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) እና የቦሮ ድሞክራሲያዊ ፓርቲ(ቦደፓ) ይገኙበታል።

ሰላምና ምርጫ በአንድ አገር የሰላም ግንባታ ላይ ትልቁን ሚና የሚጫወቱ መሰረታዊ ቁልፎች አንደሆኑ በበርካታ ጥናቶች ላይ እናገኛለን። የኮፊ አናን ፋውንደሽን በ2009 “Elections and Peace building” በሚል ባወጣው ጽሑፍ “በሽግግር ወቅት ሰላምና መረጋጋት እንድሰፍን ምርጫ ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ይላል።

በጽሑፉ ላይ የሽግግር ምርጫ ለሰላም እና ለደህንነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። “ምርጫ ሁከትን ለማሸነፍ የሚረዳ ልዩ ዴሞክራሲያዊ ዘዴ ነው። በአገሮች መካከል ግጭት እና ሥር የሰደደ ክፍፍል፣ ነባር አለመግባባቶችን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚደረግ ምርጫ ለዜጎች ጠቃሚ ቢሆንም፣ በሽግግር ወቅት የሚደረግ ምርጫም አደጋዎችን ሊስከትል ይችላል” ይላል በጽሑፍ መደምደሚያ።

በሉላ በኩል ከምርጫ ጋር የተዛመዱ ግጭቶች ወይም ሁከቶች በማንኛውም የምርጫ ሂደት ደረጃ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚገልጸው ደግሞ አፕላይድ ናውሌጅ ሰርቪስ የተባለ ድርጅት “ምርጫና ግጥት” በሚል ባሰፈረው ጽሑፍ ነው። አፕላይድ ባወጣው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው ከቅድመ ምርጫ ምዝገባ፣ የእጩዎች ምልመላ፣ የምርጫ ቅስቀሳ እስከ የምርጫ ቀን ምርጫ ድረስ እና ምርጫው ውጤት ድረስ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ ይላል። በምርጫ ሂደት የሚከሰቱ ግጭቶች በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽኖ ሊስከትሉ እንደሚችሉም ነው ይሚጠቁመው።

ኢትዮጵያ ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉድ በምትልበት ዋዜማ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀድመው የነበሩና አዲስ የተፈጠሩ ግጭቶችን እያስተናገደች ነው። ግጭቶች በተለያዩ አከባቢዎች ቀድመው ቢኖሩም በምርጫ ዋዜማ ተባብሰው መቀጠላቸው ግጭት ባለባቸው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ላይ በነፃነት እንዳይመርጡ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል።

ግጭቶች በብዛት ቀድሞውንም የማያጣቸው በተከና ወለጋ እስካሁንም ድረስ ዜጎች ያላቸው ሰላም አስተማማኝ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት ያነጋገረቻቸው ኗሪዎች መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ታዲያ ግጭትና መፈናቀል ባለባቸው አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ምርጫን በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለማድረግ እንደትስ ይቻለናል ይላሉ።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢ ዜጎች ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ባሉበት ጫና ውስጥ ሆነው ችግራቸውን ለማስወገድ መምረጥ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ የኢዜማ ኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዘላለም ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር። ይሁን እጅል በስጋት ውስጥ የሚኖሩና የተፈናቀሉ ዜጎች ጊዜው የምንመርጥበት ሳይሆን ለሕይወታችን ዋስትና የምንሻበተት ጊዜ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት(ኢሰመድኅ) ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሑ ምርጫ በተለይ በሰላም እጦት ውስጥ ለሚኖር ዜጋ የተሻለ ሊመራው የሚችለውን ፓርቲ የሚወስንበት ነው ይላሉ። ይሁን እንጅ የጸጥታ ችግርና መፈናቀል ባለባቸው አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በምርጫው በተረጋጋ ሁኔታ ምርጫን ለመምረጭ የሚስችላው እድል ላያገኙ ይችላሉ የሚል ሀሳብ አንስተው የሚሞግቱም አሉ።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፎካካሪ የሆነው ቦዴፓ ባሳለፍነው ሳምንት መጋቢት 12/2013 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ሳይረጋገጥ ለምርጫ መሯሯጥ ተገቢ አይደለም ብሏል።
በክልሉ መተከል ዞን ቀድሞ የነበረው የጸጥታ ችግር ከሰሞኑ እየተባባሰ መሆኑን የተቂመው ቦዴፓ፣ የክልሉ መንግሥትም ለዜጎች ሠላምና ደህንነት ቅድሚያ ሊሠጥ ሲገባው በማን አለብኝነት በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ብቻ ተወጥሮ ይገኛል ነው ያለው። “የዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ሳይረጋገጥ ለምርጫ መሯሯጥ ተገቢ ነው ብሎ ፓርቲያችን አያምንም። ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ሳይመለሱና የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምሩ የክልሉ መንግሥት የምርጡኝ ቅስቀሳ ውስጥ መግባቱ ፍጽም ተቀባይነት የለለው ተግባር ነው።” ብሏል ቦዴፓ።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት፣ የክልሉ መንግሥት እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ቅድምያ ለሰብዓዊ ድጋፍ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። በሰላም ማርጋጋት ስም የሚድርግ የምርጫ ዘመቻ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ያለው ቦዴፓ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በተረጋጋ ሁኔታ ይወክለኛል ብለው የሚስቡትን ፓርቲ እንድመርጡ በአትኩሮት መሥራት ይገባል ብሏል።

በዚህ የምርጫ ዋዜማ የጸጥታ ችግር ያለባቸው ዋና ዋና ቦታዎች በኢሮሚያ ክልል ወለጋ፣ በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞንና በቅርቡ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተፈጠረው ግጭት ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በቀጣዩ ምርጫ የሚወክላቸውን መምረጥ እንድችሉ ከባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቁ ቅድመ ሥራዎች እንዳሉ መስዑድ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የጽጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች የሚኖሩና የተፈናቀሉ ዜጎች ስለምርጫው መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች በበቂ ሁኔታ ግንዛቤና እድል ሊገኙ እንደሚገባቸው የጠቆሙት መሰዑድ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና የጸጥታ አካላት የተፈናቀሉ ዜጎች ባሉበት ሁኔታ በሙሉ አቅም እንድመርጡ ከወዲሁ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“በጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚወክላቸውን ባሉበት ሁኔታ መምረጥ ለችግሩ አንዱ መፍትሔ ነው፡” የሚሉት መስዑድ፣ ድርጅታቸው ተፈናቃዮች በሚገኙበት አከባቢ የምርጫ ቅስቀሳና ግንዛቤ ሥራዎችን እየሰራ መሆን ጠቁመዋል። ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት የተፈናቀሉ ዜጎች ጫናውን ተቋቁመው እንድመርጡ ግንዛቤ የመፍጠርና የማገዝ ሥራ የመሥራት ኃላፊነትውን እንድወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com