‹‹ዋና ዓላማችን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረግ ነው›› መስዑድ ገበየሁ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር

Views: 58

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት(ኢሰመድኅ) ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው መጋቢት 2010 ነበር። ኅብረቱ በሰብዓዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሠሩ 12 የሲቪክ ማኀበራት ድርጅቶች በስሩ ያቀፈ ነው። ኅብረቱ በ2013 የኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማከራከር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ካገኙ 11 ድርጅቶች ውስጥ ተሰይሟል። ይህን ተከትሎም የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ከኅብረቱ ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር ለማካሄድ ፈቃድ ከሰጣቸው 11 ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት እንዴት ተመረጠ?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት በሰብዓዊ መብት፣ ዴሞክራሲ እና ግጭት አፈታት ላይ የሚሠሩ 12 ሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ስብስብ ነው። በዋናነት ኅብረቱ ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ እንደመሆኑ በ2013 በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ሂደቶች ላይ በአንዳንድ ሥራዎች ይሳተፋል።

ከሚሳተፍባቸው ተግባራት ውስጥ የምርጫ ትምህርት አንዱ ሲሆን፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና አዲስ አበባ ላይ እንሠራለን። ኹለተኛው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ክርክር አካሂደን በምርጫው ሕዝቡ የትኛው ፓርቲ ምን ዓይነት አስተሳሰብ፣ ምን ዓይነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አለው የሚለውን መራጩ እንዲያውቅ የምናደርግበት ነው።

ሌላው ደግሞ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ መታዘብ ሥራ ይሠራል። እንደውም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ባለበት የምርጫ ጣቢያ ብቸኛው የአገር ውስጥ ታዛቢ የእኛ ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር ለማካሄድ ጥያቄ ስናስገባ የሚጠይቃቸው መስፈርቶች አሉ። ክርክሩ የሚደረግባቸው አጀንዳዎች፣ ክርክሩን የሚያካሂደው አካል ገለልተኛነትና ብቃት እንዲሁም ክርክር ለማካሄድ መሟላት ያለባቸውን መርሆችን አሟልተን ነው።

ድርጅታችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር የሚያዘጋጅበት ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
የእኛ ድርጅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር የሚያካሂድበት ዋና ዓላማ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰብዓዊ ጉዳዮች ምን ዓይነት ፖሊሲዎች፣ ርዕዮት ዓለምና ስትራቴጂ እንዳላቸው መራጩ ሕዝብ እንዲያውቅ ነው። የእኛ ዋና ዓላማችን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረግ ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ የሰብዓዊ ጉዳዮችን አጀንዳቸው አድርገው እንዲሠሩ ትኩረት አድርገን ነው የምንሠራው።

የተያዙት የምርጫ ክርክር አጀንዳዎች ምን ምን ናቸው?
የመከራከሪያ አጀንዳዎቹ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የሴቶች ጉዳይ፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች ጉዳይና በምርጫው በተሟላ ሁኔታ የሚሳተፉበትን ሁኔታ፣ እንዲሁም ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳትን በተመለከት ምን ምን ጉዳዮችን ይዘዋል የሚለውን የምንፈትንበት ነው።

ሌላው የአገር ውስጥ ግጭቶችና መፈናቀሎች ተበራክተዋል። ይህንን ለማስቆም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አስበዋል የሚለውን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ፓርቲ ያለውን አመለካከት እንጠይቃልን ብለን ነው ያሰብነው። ለምርጫ ቦርድ ያስገባነው ጥያቄ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ክርክር እንድናካሂድ ነው።

ከሴቶች፣ ከሰብዓዊ መብቶች ተጠያቂነት፣ ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ከአካል ጉዳተኞች በተጨማሪ በሦስት ተጨማሪ አጀንዳዎች ላይ ጥናቶችን አካሂደን በጥናቶቹ ግኝት መሠረት ክርክሮችን እናካሂዳለን። ተጨማሪ ክርክር እናደርግባቸዋለን ብለን ያሰብናቸው ሦስት አጀንዳዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የሚሉት ናቸው። በአጠቃላይ በሰባት አጀንዳዎች ላይ ክርክር እናካሂዳለን ብለን ነው እየሠራን ያለነው።

ክርክሩን ለማካሄድ ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል?
ክርክሮችን ለማካሄድ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ገንዘብ ነበር። ከአጋር ድርጅቶች ክርክሩን የምናካሂድበትን የገንዘብ ድጋፍ አግኝተናል፣ ክርክሩን ለማካሄድ ፈቃድ ካገኘን ገንዘቡ እንደሚለቀቅልን ቃል ተገብቶልናል። አሁን እጃችን ላይ ሦስት መቶ ሺሕ የሚጠጋ ገንዘብ ነው ያለው። ነገር ግን ክርክሩ በብዙ መገናኛ ብዙኀን እንዲተላለፍ ተጨማሪ ፈንዶችን እያፈላለግን ነው።

ሌላኛው ዝግጅት ክርክሩን የሚያካሂዱ ባለሙያዎችን ማዘጋጀት ነው። እኛ አከራካሪዎችን ኹለት ኹለት ሆነው እንዲያከራክሩ ነው የምናደርገው። ይህን የምናደርግበት ምክንያት ደግሞ ኹለት ሆነው የሚነሱ ሐሳቦችን በደንብ እንዲሞግቱና እንዲያከራክሩ ነው። አከራካሪዎች በሚያከራክሩበት አጀንዳ ላይ በቂ እውቅት ያላቸውና ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ናቸው። እኛ የውስጥ ዝግጅቶች አጠናቀናል።

የፓርቲዎቹ ክርክር ለሕዝብ የሚደርሰው በምን መልኩ ነው?
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ክርክር ተቀርጾ በተለያዩ የቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያዎች በኩል ለሕዝብ እንድናደርስ አብረውን ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገርን ነው። ክርክሮችን ለሕዝብ ለማድረስ እንደስምምነታችን በኹለትም ይሁን ከዚያ በላይ ሚዲያዎች እናስተላልፋለን።

ከዛ በተጨማሪ ክርክሩ በሚደረግ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ በቀጥታ እንዲሰራጭ ይደረጋል። በማኅበራዊ ገፆቻችን ቀድመን እናስተዋውቃለን።
የምናደርጋቸው ክርክሮች የሦስት ሰዓት ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ገንዘብና አቅም ካገኘን ተጨማሪ ክርክሮችን እናደርጋለን ብለን እናስባለን። የተቀረጹት ክርክሮች በተለያየ ክፍል ተከፍለው፣ ቢያንስ እስከ ስምንት ክፍል ድረስ፣ በምንመርጣቸው ሚዲያዎች ለሕዝብ ይተላለፋሉ።

ለክርክር የሚቀመጡ ፓርቲዎችን የምትመርጡት በምን መስፈርት ነው?
ድርጅቱ የሚያከራክራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለክርክር የሚመለምለው ባስመዘገቡት እጩዎች ብዛት ነው። ይህም ማለት በምርጫው ለመወዳደር በርካታ እጩ ያስመዘገበ ፓርቲ የበርካታው ሕዝብ ድምጽ በማግኘት መንግሥት ይሆናል ተብሎ ስለሚገመት ነው። ለክርክር የሚመረጡ ፓርቲዎችን በክልል ደረጃ የሚወዳደሩት በአንድ ዘርፍ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩት በሌላ ዘርፍ ሆነው ነው ክርክሩን የምናካሂደው።

እኛ ክርክሩን ለማካሄድ ከምርጫ ቦርድ ፍቃድ እንድናገኝ ጥያቄ ስናቀርብ ከክልል ፓርቲዎች አምስትና ከአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች አምስት በክርክሩ ተሳታፊ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ እንደምናገኘው የሀብት መጠን የክርክር ስፋቱን እንደየአስፈላጊነቱ ልናሰፋው እንችላለን። ሌላኛው ፓርቲዎችን የምንመርጥበት መንገድ ባዘጋጁት ፖሊሲ ላይ ለክርክር የተመረጡት አጀንዳዎች የተካተቱ መሆናቸው ከተረገገጠ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com