የእለት ዜና

ፊልምና የፊልም ባለሞያዎች – በ7ኛው ጉማ ሽልማት

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካስታጎላቸው ጥበባዊ መሰናዶዎች አንደኛው ጉማ ሽልማት ነው። ይህ ሽልማት አዳዲስ ብቅ ያሉ የሥነ- ራዕይ ወይም የፊልም ባለሙያዎች የሚበረታቱበት፣ ነባሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና ምርጥ የተባሉ ሥራዎች ምስጋናን የሚያገኙበት መሰናዶ ነው። ይኸው ሽልማት ታድያ ግማሽ እድሜውን በጨረሰው ባለንበት 2013 ሊካሄድ ጉድ ጉዱ ተጠናቋል። በዛሬው እለት ማለትም መጋቢት 18 ቀን/2013 ማምሻውን በስካይላይት ሆቴል ይካሄዳልም ተብሏል።

ጉማ የፊልም ሽልማት ‹ጉማ› የሚለውን መጠሪያውን ያገኘው ከአርባ ሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በሚሼል ፓፓታኪስ ከተሰራው ‹ጉማ› የተሰኘ ፊልም ነው። ሽልማቱ ታድያ አስቀድሞ ሲወጠን ሙያው ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እውቅና መስጠትን ታስቢ ያደረገ ነበር። በሽልማቱ የመጀመሪያ ዝግጅት ላይ ለውድድር የቀረቡት በ2004 ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የቀረቡ ፊልሞች ነበሩ። በዚሁ ውድድር በ17 ዘርፎች 33 ፊልሞች ተመዝግበው 23ቱ ሲያልፉ፤ ከ87 በላይ ዳኞች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም ‹የሕይወት ዘመን ተሸላሚ› የተሰኘ ዘርፍ ተካትቶ ነበር።

በዛ መልክ ከስምንት ዓመታት በፊት የጀመረው ጉማ ሽልማት በድጋፍ አድራጊ፣ በእጩ ተሳታፊና በውድድር ዘርፎች እየጨመረና እየሰፋ፣ ተቀባይነቱም እያደገ እስከ ስድስተኛ ዙር ድረስ ጉዞውን ቀጠለ። መግቢያችን ላይ እንዳነሳነው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ግን አንድ ዓመት ሳይካሄድ እንዲሻገር ግድ ሆነበት።

6ኛው የጉማ ሽልማት የተካሄደው መጋቢት 17 ቀን 2011 በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ነበር። በዚህ የሽልማት ዓመት ታድያ በቁጥር 61 ፊልሞች ተመዝግበው 25 የሚሆኑት ለውድድር ቀርበው ነበር።
ተሸላሚዎቹንም መለስ ብለን ስናወሳ፤ ልዩ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ነበሩ። በየዘርፉ ደግሞ ተከታዮቹን እናገኛለን። በምርጥ የፊልም ሙዚቃ ድምፃዊ መሳይ ተፈራ፣ ዜማ አህመድ ተሾመ /ዲንቢ/ እና ግጥም ወንደሰን ይሁብ (ሚስቴን ዳርኳት)፤ በምርጥ የፊልም ስኮር ሱልጣን ኑሪ (በሲመት)፤ በምርጥ የፊልም ሜክአፕ መሰረት መኮንን (በሲመት)፤ በምርጥ የፊልም ስክሪፕት በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) በእናት መንገድ፤ በምርጥ የፊልም ቅንብር ልዑል አባዲ (ወደ ኋላ)፤ በምርጥ ፊልም ቀራፂ እውነት አሳሳኸኝ (ውሃ እና ወርቅ)፤ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ሴት ተዋናይት ሕፃን ማክቤል (ሞኙ ያራዳ ልጅ ቁጥር 4)፤ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ወንድ ተዋናይ በኃይሉ እንግዳ (ጃሎ)፤ በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘነቡ ገሠሠ (ትህትና)፤ በምርጥ ረዳት ተዋናይ ካሳሁን ፍስሀ ማንዴላ (ወደ ኋላ)፣ በምርጥ ሴት መሪ ተዋናይት ሶኒያ ኖዌል (አንድ እኩል)፤ በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ ኤርሚያስ ታደስ (አላበድኩም)፤ በደሌ ስፔሻል የተመልካቾች ምርጫ (ሚስቴን ዳርኳት)፤ ምርጥ የሥራ መሪ (ዳይሬክተር) በኃይሉ ዋሴ (በእናት መንገድ)፣ የዓመቱ ምርጥ ፊልም (በእናት መንገድ) ተሸላሚ ሆነው ነበር።

2013 የጉማ ሽልማት
በ2013 የጉማ ሽልማት አራት ቀን በወሰደ ጥቆማ 45 ፊልሞች ተመዝግበዋል። ከእነዚህም ውስጥ ዳኞች በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት 15 ፊልሞችን ለመጨረሻ ዙር ውድድር አሳልፈዋል። እነዚህ ፊልሞች በደሌ ስፔሻል ምርጥ የተመልካቾች ምርጫን ጨምሮ በ18 ዘርፎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ናቸው ተብሏል።

የጉማ ሽልማት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ 7ኛውን የጉማ ሽልማት በ2012 ለማዘጋጀት ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳል። ነገር ግን ከዝግጅቱ አንድ ወር አስቀድሞ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በወጣ የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ሳይካሄድ ሊቀር ችሏል ብሏል።

የ2013 ጉማ ሽልማት በ2011 እና 2012 የወጡና የታዩ ፊልሞችን ያካተተ ነው። ከቀረቡ ፊልሞች ውስጥ በመጨረሻ ለውድድር የቀረቡትም በተለያየ መስፈርት መመረጣቸውን በሚገባ የማጣራት ሥራ መሠራቱንም አንስቷል። ኦሪጅናል የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃዎች መሠራታቸውን እንዲሁም ጽሑፎችም አዲስ መሆናቸውን በሚመለከት በደንብ ማጣራት ተደርጓል። እንዲሁም በሲኒማ ቤት የታዩና ለድረገጽ ወይም ለኦንላይን ተብለው የተሠሩትን መለየትና ማጣራት ላይ መሠራቱንም ነው ዮናስ የተናገረው። ከዛ በተጓዳኝ ብዙ የውጪ አገር ዜጎች የተሳተፉባቸው ፊልሞች መለየታቸውንና የውድድሩ አካል እንዳልሆኑም ተናግሯል።

በዚህ መሠረት ከተለዩት 15 ፊልሞች መካከል ‹እንሳሮ› የተሰኘው ፊልም በ13 ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚ ሲሆን ቁራኛዬ በ12 ዘርፎች እንዲሁም ተፈጣሪ የተሰኘው ፊልም በ10 ዘርፎች በተከታታይ ተቀምጠዋል። ወጣት በ97፣ ሱማሌው ቫንዳም፣ 3ኛው ዐይን፣ ህዳር፣ ኪያ፣ 10 አስር፣ ወደፊት፣ ቦሌ ማነቂያ፣ ከፍሎ ሟች፣ ዘመኔ፣ ያገር ሌባ እና ጥቁር እና ነጭ 2 ከቀረቡት እጩዎች መካከል ናቸው። አዲስ ማለዳ እጩዎችን መልካም እድል እንዲሁም እንኳን ደስ አላችሁ ትላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com