እንደራሴዎቻችን ለህሊናቸው ይኑሩ!

Views: 22

የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የማቋቋም ዓላማ እውነተኛ የሕዝብ ወኪሎችን በማሰባሰብ እንደ አገር በጋራ ትልልቅ አገራዊ ውሳኔዎች ላይ በእውቀት በመከራከር ለአገር እና ሕዝብ የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ነው። ይህ ምክር ቤት ከፍተኛው የሥልጣን እርከን በመሆኑ የሚያስተላልፋቸው ማንኛውም ዓይነት ውሳኔዎች ምክንያታቸው ምንም ሆነ ምንም፤ ተፈጻሚነት አላቸው። ውሳኔውን ለማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት ማንኛውም አካል ማስፈጸም እንዲሁም መፈጸም ይጠበቅበታል።

ውሳኔውን አለመፈጸም የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል። ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው የሕዝብ እንደራሴዎች ቦታውን የሚመጥን፣ የሕዝባቸውን እና የአገሪቱን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት ወዘተ ግምት ውስጥ ያስገባ ሃሳብ እና አስተያየት ሊያነሱ ይገባል። ከዚህም ውጪ ምክር ቤቱ ያወጣው የአባላት ሥነ ምግባር መመሪያንም ግምት ውስጥ በማስገባት ንግግራቸው ልከኛ እንዲሆን ይጠበቃል።

ካለ በቂ ምክንያት በየጊዜው እየጠፉ ያሉ ሕይወቶች እጅግ በርካታ ናቸው። እውነት ነው! እጅግ በጣም የሚያሳምሙ፣ በጥብቅም ልናወግዛቸው የሚገቡ አፀያፊ ድርጊቶች በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየተፈጸሙ ነው። እነዚህን አሰቃቂ ግድያዎች አሁንም ልናስቆማቸው አልቻልንም፣ ጭራሽ ተለማምደናቸው የእለት ዜና ማሟሻ አደረግናቸው።

እንደ አንድ ሕዝብ በየቦታው በወገኖቻችን ላይ የሚፈፀምን ግድያ በአንድነት በቃ ልንል ይገባል። እንዲህ ያለ ኹነት በተለይ ደግሞ የሕዝብ ወኪል የሆኑ እንደራሴዎችንን ካለባቸው ድርብ ኃላፊነት የተነሳ ብስለታቸውን የሚያሳዩበት የታሪክ አጋጣሚ ነው። ብሔር እና ሃይማኖትን ለይቶ ማልቀስ ለወከሉት አካባቢ ሕዝብ ያለውን እውነተኛ ወኪልነት የሚገልጽ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት ለሕዝብና ለሕሊና ያለበትን ተጠያቂነት መሸሽ ነው።
የሕዝብ እንደራሴ ሆኖ የጥላቻና ዘረኝነት፣ የሀይማኖትና የብሔር ግጭት ለማስነሳት፣ የተነሳውንም ለማባባስ በፓርላማ ቁጭ ብሎ በቀጥታ በሚተላላፍ መርሃ ግብር ላይ መናገር የታሪክ ተጠያቂ የሚያደርግ ተግባር ነው።

ሁኔታውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርን በጣሰ መልኩ በወገንተኝነት የሚነሱ ጥያቄዎችና ሐሳቦች ተቀባይነት እንደሌለው እናምናለን። የምክር ቤቱ አባላት ተስማምተው የጥላቻ ንግግር አዋጅን ማጽደቃቸው እንዲህ ያለ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭን ንግግር ለመገደብ እና ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመከላከል በማሰብ እንደሆነ ይታወቃል። ይህን አዋጅ ቁጭ ብሎ ያጸደቀ የምክር ቤት አባል ተግባራዊ በማድረግ ለሌላው አርአያ መሆን ይገባዋል ብለን እናምናለን ።

በዚሁ ጊዜ አንዳንድ አባላት ከምክር ቤቱ የአሰራር ሥነ ምግባር ውጪ ሐሳቦችን በስሜታዊነት መሰንዘራቸው ተገቢ አለመሆኑን፤ ነገር ግን የፓርላማ አባላት በወከሉት ሕዝብ ላይ የሚደርስ በደል እንዲታረም መጠየቃቸው ከኃላፊነት ባለፈ ግዴታ ጭምር እንደሆነ እናምናለን። የሚቀርቡና የሚነሱ ሐሳቦች ከስሜታዊነት በጸዳና የሕዝቡን ሥነ ልቦና በማይጎዳ መልኩ መሆን ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

ምንም አይነት አደጋ ኖር በጋራ እየተጋፈጡ፣ ተዋልደው ተጋምደው ለዘመናት የኖሩ ሕዝቦችን ለመነጣጠል መሞከር ከኢትዮጵያዊ ባህል እና እሴት ውጪ በመሆኑ በምክር ቤቱ የጸደቀው አዋጅ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየትኛው የሥልጣን እርከን ባሉ ሰዎች ላይ ተግባራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ከምክር ቤቱ አሠራር ውጪ የተንቀሳቀሱ የምክር ቤት አባላትም ላይ በተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ አለበት።

በፓርላማው አሰራር መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች አስቀድመው በጽሕፈት ቤት በኩል ያስገባሉ። ከዚያም ያስገቡትን ጥያቄ በንባብ ያቀርባሉ። ይህ የሚታወቅ አካሄድ ነው። ነገር ግን በእለቱ አባላቱ ያስገቡትን ጥያቄ ትተው ትዝብት ላይ የጣላቸውን ንግግር የፓርላማውን ሕግ በጣሰ መልኩ አቀረቡ። ይህንንም ንግግር እንደ ፌስቡክና ዩትዩብ ባሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ጽንፈኛ አክራሪ ብሔርተኞች አጀንዳ አድርገው አራገቡት። የአገሪቱ የሕግ አውጪ አካል ሆኖ መንግሥትን ሊቆጣጠር የተቀመጠ አንድ የምክር ቤት አባል በዚህ ደረጃ ወርዶ በስሜት ሲጋልብ መመልከቱ ተገቢም አግባብም ሆነ ትክክል አይደለም።

ኢትዮጵያ ዛሬ የተሸከመቻችው ዘርፈ ብዙ እዳዎች የዘመናት ፍጥጫዎችና ፍትጊያዎች፤ ትርክቶችና ግጭቶች ውጤቶች በመሆናቸው፣ ዛሬ ለሚታየውና ጆሮንም ጭው ለሚያደርገው ዘግናኝ ወሬዎች በቅተናል። ከግጭቶቹ ፖለቲካዊ ትርፍ የሚያሰሉ የኢትዮጵያ ለማፈራረስ ቀን ሌት የሚሠሩ ኃይሎች ውስጣዊ አንድነታችን ለመናድ በብሔር እና ሃይማኖት ልዩነታችን አማካኝተው ሊያንበረክኩን መቋመጣቸው እሙን ነው። ሁሉም የራሱን ቁስል ከማከክ አልፎ ስለአገር፣ ስለአንድነት መናገር ይገባዋል።

በማኅበራዊ ገጾችና በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያውያንን ብዝኀነት ለእርስ በእርስ ግጭት መጠቀሚያ ሊያደርጉ የሚሹ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ የሆኑ አጥፊዎች እንዳሉ ይታወቃል። ቢያንስ ግን ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች በአንጻሩ ሕዝብን የሚያቀራርብና ለሁሉም ሰላም የሚያመጣ መንገድን እንዲያስቡ ይጠበቃል። ኃላፊነታቸውን መወጣት ባይችሉና እንዲህ የእርስ በእርስ ግጭት ቀስቃሽ ሆነው በሰፈሩበት ሲሰፈሩ፤ ሕግ ሊጠይቃቸው ይገባል። ከዛ በላይ ግን ሕሊና ቀዳሚ አለቃ ናትና፣ ለተመደቡበት የአገልግሎት ድርሻ ደግሞም ለሕሊናቸው ይደሩ ስትል አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታሳስባለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com