የእለት ዜና

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ለግለሰብ አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት ሊጀምር ነው

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ለግለሰብ አርሶ አደሮች የተለያዩ የብድር አገልግሎቶችን መስጠት ሊጀምር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ባንኩ ለግለሰብ አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት የሚያቀርበው የአርሶ አደሩን ማኅበረሰብ ክፍል የገንዘብ እጥረት ለመፍታት መሆኑን የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ስትራቴጂና ኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ታደለ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በግርብናው ዘርፍ በተለያዩ መስኮች ለተሰማሩ ግለሰብ አርሶ አደሮች ባንኩ የሚያቀርበው ብድር አርሶ አደሮች ባላቸው አቅም ላይ ተጨማሪ ገንዘብ አግኝተው የግብርና ሥራቸውን እንዲሳድጉ ያስችላል ተብሏል።
ባንኩ ከዚህ በፊት የብድር አገልግሎት በብዛት የሚያቀርበው ለሕብረት ሥራ ማኅበራት እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአርሶ አደሩን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀው የብድር አገልግሎት በወለድ መጠኑ ከሌሎች የብድር አይነቶች አነስተኛ ነው ተብሏል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከሆነ ለግለሰብ አርሶ አደሮች ባንኩ ያዘጋጀው የብድር አገልግሎት ከሌሎች የብድር አይነቶች ወይም ለነጋዴዎች ከሚሰላው ወለድ እንደየ ብድር አይነቱ ቅናሽ እንደሚኖረው ከመናገር ባሻገር የወለድ መጠኑን ለጊዜው ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ለገጠሩ አርሶ አደር የብድር አገልግሎት በስፋት ከማቅረብ አንፃር ውስንነት እንዳለባቸው ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ባንካቸው ለአርሶ አደሮች ብድር ከማቅረብ በተጨማሪ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የቁጠባ አገልግሎቶችን አብሮ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በግለሰብ ደረጃ ለአርሶ አደሮች የሚቀርበው የብድር አገልግሎት በውስጡ ከያዛቸው ጥቅሎች መካከል በመስኖ ግብርና፣ በሰብል ግብርና፣ በአትክልት ልማት ግብርና እና በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ያማከለ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ያብራሩት።

ለአርሶ አደሮች ባንኩ የሚያቀርባቸው የብድር አገልግሎቶች በቅርብ ጊዜ ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ለግለሰብ አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት የማቅረብ ችግር እንዳለ ያነሱት ዳይሬክተሩ በገጠሩ ማኅበረሰብ በኩል ግብርናውን ለማገዝ የተሰሩት ሥራዎች አነስተኛ በመሆኑም የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የገጠሩን ማኅበረሰብ ክፍል ያማከለ ሥራ በመሥራት አርሶ አደሩን የቁጠባ ልምድ ማዳበርና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ወደፊት የዘመነ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑ እንደሆነ ጠቁሟል።

ለአርሶ አድሮች ባንኩ ለዚህ በፊት መስጠት የጀመራቸው አገልግሎቶች አርሶ አደሮች ትራክተር መግዛት እንዲችሉ 30 በመቶ እንዲቆጥቡ በማድረግ ቀሪውን ገንዘብ በብድር መልክ በመስጠት አርሶ አደሮችን የትራክተር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ባሳፍነው 2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 1.9 ቢሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን ፣ባንኩ ያገኘው ትርፍ ከ 2011 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በእጥፍ ያህል እድገት እንዳሳየ ተገልጾ ነበር።
የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የ2012 በጀት ትርፍ በአገሪቱ ካሉ ባንኮች በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጠው የሚታወስ ሲሆን፣ በ2011 የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ከነበረበት 47.79 ቢሊየን ብር የ11.13 ቢሊየን ብር ጭማሪ በማሳየት፣ በ2012 ዓመት 52.92 ቢሊየን ብር እንደ ደረሰም ታውቋል።

በተመሳሳይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 45.52 ቢሊየን ብር መድረሱ ተነግሯል። የባንኩ ደንበኞች ብዛት ከግል ባንኮች ቀዳሚ መሆኑ እንደሆነ ነው የሚነገረው። አሁን ላይ የባንኩ የደንበኞች ብዛት ሰባት ሚሊዮን እንደተጠጋ ታደለ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። የባንኩ የተከፈለ ካፒታሉ ሦስት ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ የቅርንጫፎች ብዛት 420 ደርሷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!