የታክሲ አሽከርካሪዎች ሮሮ

Views: 157

በከተማችን አዲስ አበባ ቁጥራቸው ከ 10 ሺሕ የሚበልጡ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች አሉ።አሽከርካሪዎቹ በተለያዩ አካላት በሚደርስባቸው ያልተገባ አሰራር እና በቅጣት እርከን ፣እንዲሁም በተሃድሶ ስልጠና ላይ ያላቸውን ቅሬታ ያለሳሉ።
መጋቢት ስምንት ቀን በመዲናዋ በታክሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ በተለይም መስመራቸው ወደ ሽሮሜዳ አካባቢ የሆኑ ቁጥራቸው 100 የሚደርሱ አሽከርካሪዎች ‹አድማ አድርጋችኋል› በሚል ምክንያት መንጃ ፍቃዳችን እና ታርጋችን ተወስዶብናል በማለት ቅሬታቸውን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ መንጃ ፈቃዳችን ተወሰደብን ብለው ቅሬታ ያቀረቡ አሽከርካሪዎችን በማነጋገር ተከታዩን ጽሁፍ አዘጋጅታለች።
የታክሲ ሾፌሮች እንደሚገልጹት ከትራፊክ ሕግ መተላፍ ጋር ጥፋቶች ሲገኙብን በሕግ አስከባሪ ትራፊኮች በኩል የሚያዘው ነጥብ በዓመት ውስጥ 17 ከደረሰ መንጃ ፈቀዳችን ለሦስት ወራት ያሳግድብናል። 21 ከደረሰ ደግሞ ለስድስት ወራት እንዲታገድ ይደረጋል። ለሦስት ወርም ሆነ ለስድስት ወር ስንታገድ ድጋሚ አጭር የተሐድሶ ስልጠና ወስደን መንጃ ፈቃድ እንድንወስድ እንገደዳለን። የተሐድሶ ስልጠናውን ጨርሰን መንጃ ፈቃዳችንን መልሰን እስክንወስድ ድረስ መኪና ማሽከርከር ስለማንችል ለሦስት እና ለሥድስት ወራት ያለሥራ እንከርማልን። በቀን የእለት ገቢ ለምንተዳደር የታክሲ አሽከርካሪዎች ሥራ ማቆሙ እና ድጋሚ ክፍያ ከፍሎ የመንጃ ፈቃድ ተሐድሶ ስልጠና መውሰዱ ከባድ ሆኖብናል፤ ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታክሲ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም የትራፊክ ሕግን በመተላለፍ በዓመት ውስጥ የሚያዝብን ነጥብ ዓመቱን በሙሉ የሚቆይ እና በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ነጥብ ሊያዝብን የሚችል በመሆኑ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ17 ጊዜም በላይ ነጥብ ሊኖርብን ስይችላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ታክሲ ማሽከርከርን እጂግ ከባድ እያደርገብን ነው፤ በማለት ገልጸዋል። ሌላው ደግሞ፣ ለምሳሌ በእርከን አንድ ተቀጥተን 100 ብር የምንከፍል ቢሆንም ባንክ ስንሄድ እስከ 300 ብር ድረስ እንከፍላለን ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች የታክሲ አገልግሎት ተጠቃሚው በሥርዓት ተሰልፎ እና ወረፋ ጠብቆ እንዲሳፈር እና ታክሲዎች ተራቸውን ጠብቀው እንዲጭኑ በማድረግ አብረን የምንሠራ ቢሆንም የተራ አስከባሪ ኃላፊዎች ሌላ ሠው በመወከል በቀን ይህን ያህል ገቢ አድርግ በማለት የሚያዙ በመሆኑ የተወከለው ሠው በታክሲ ሾፌሮች ላይ ጫና በማሳደር ከተገቢው በላይ ገንዘብ ይቀበለናል። ሕጉ አንድ ታክሲ ከመነሻው አምስት ብር ለተራ አስከባሪዎች እንዲከፈል የሚያዝ ቢሆንም መንገድ ላይ አንድ ሠው ለማውረድ ቆመን አንድ ሰው ስንጭን ሌላ አምስት ብር እንድንከፍል እንጠየቃለን፤ ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም።›› ሲሉ ተናግረዋል።

የአሽከርካሪዎቹ ቅሬታ የሚሰማው በመደበኛ ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን ላዳ እና ሌሎች ተሸከርካሪዎችን በሚያሽከረክሩትም ጭምር መሆኑን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ለመረዳት ችላለች።
የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ የሆነው ሰለሞን አለሙ ‹‹የዛሬ ወር ገደማ ቀኑ የማርያም ክብረ በዓል ነበር፤ የትራፊክ መጨናቅ ስለነበር መኪናዩ መተላለፊያ አጥቶ ቆሜያለሁ። በዚህ አጋጣሚ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ታርጋዩ በትራፊኩ ስለተፈታብኝ የቅጣት ክፍያ ለመክፈል ስሄድ መንጀ ፈቃዴ ሲስተም ላይ እንደታገደ ተነገረኝ።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

አክሎም ‹‹ከዚህ በፊት ምንም አይነት የቅጣት ሪከርድ ወይንም ደግሞ ክስ የለብኝም፤ ግን መንጃ ፈቃዴ ሲስተም ላይ ታግዷል ተብዬ ድጋሚ መንጃ ፈቃዴን ለማግኘት የ15 ቀን የተሐድሶ ስልጠና ለመውሰድ ተገድጃለሁ በማለት ያነሳል። ለስልጠናው 2ሺሕ 500 ብር ከፍያለሁ። ከእኔ ጋር ሌሎች ሦስት አሽከርካሪዎች ስልጠና ወስደዋል። አሁን የቀረን የመስክ ፈተና መፈተን ነው።›› ብሏል።

ቀጥሎም ‹‹የመስክ ፈተናውን ማለፍ ካልቻልን ድጋሚ ከፍለን ልንፈተን እንገደዳለን። ታክሲ እና ላዳ እያሽከረከርን የምንተዳደር ሰዎች መንጃ ፈቃዳችን ተወስዶብን ሥራ ስንፈታ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናችን በርካታ ችግሮች ይኖሩብናል።እኔ ለምሳሌ መንጃ ፈቃዴ ሲስተም ላይ ታገደ እንጂ እጄ ላይ ስለሚገኝ መኪና ማሽከርከር አልተውኩም ምክንያቱም የምተዳደረው በዚህ ሥራ ብቻ በመሆኑ።›› በማለት ሰለሞን ገልጿል።

ሰለሞን የተሐድሶ ስልጠናውን በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት እንደወሰደ እና አብረውት ስልጠናውን የወሰዱት አሽከርካሪዎች የታክሲ፣ ከባድ እና ቀላል የቤት መኪና የሚያሽከረክሩ መሆናቸውን ተናግሯል።
በከተማችን ውስጥ በአብዛኛው ለትራንስፖርት እጥረቱ እንደ ምክንያት የሚነሳው ነገር የነዳጅ እጥረት እና የነዳጅ ዋጋ መናር ብሎም የትራፊክ መጨናነቅ ቢሆንም በአሽከርካሪዎችና እና በመንገድ ትራንስፖርት በኩል ያለው አለመግባባት ደግሞ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ለመታዘብ ይቻላል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ እንደተናገሩት ‹‹ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘ ችግር ካለ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን እየሰሩ ቅሬታቸውን ማቅረብ ነው ያለባቸው›› ብለዋል። አክለውም ‹‹እስካሁን ጥያቄዎች እየቀረቡ ያሉት በአሽከርካሪዎች በኩል እንጂ በማህበራት አማካይነት አይደለም፤ ይህ ደግሞ አግባብነት የለውም።›› ብለዋል።

‹‹የአሽከርካሪዎች ጥያቄ የመመሪያ ጉዳይ ነው፤ መመሪያ እንዲሻሻል ለመጠየቅ የታክሲ ማኅበራትና ባለንብረቶች ወይንም ወኪሎች አሉ። ጥያቄዎቻቸውን በተናጠል ከማቅረብ ይልቅ በተደራጀ መልኩ ማቅረቡ የተሻለ ነው። ማነው ያለው
ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ የጥፋት ሪከርድ ወይንም የእርከን ቅጣትን የተመለከተ ፣ ከታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እና ቁጥጥር እና ክትትልን በተመለከተ ከተቆጣጣሪ አካላት ገንዘብ እንጠየቃለን የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል ።
አቶ አረጋዊ እስከ አሁን ድረስ ከትራንስፖርት ተገልጋዮች እንጂ ከአሽከርካሪዎች ቅሬታ ቀርቦላቸው እንደማያውቅ ገልጸው፣ አሁን ከአሽከርካሪ ወገን ቅሬታ መቅረቡ የሚያሳየው ‹‹የቁጥጥር ስርዓቱ የጠበቀ መሆኑን ነው።›› ብለዋል።

በታክሲ አሽከርካሪዎች በቀረቡ ቅሬታዎች ላይ ከሁለቱ ምክትል ከንቲባዎች ጋር የታክሲ ማህበራት እና ትራንስፖርት ቢሮው በጋራ ለመስራት እና ችግሩን ለመቅረፍ እንደተወያዩ አቶ አረጋዊ ገልጸው፣ ከውይይቱ በመነሳት ‹‹ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ አገልግሎት መስጠት ማቆም አስፈላጊ እንዳልሆነ እና ጥያቄያዎቹም አገልግሎት እስከማቆም የሚያደርሱ እንዳልሆነ ከታክሲ ማኅበራቱ፣ ከባለንብረቶች እና ከአሽከርካሪዎች ጋር ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰናል።›› በማለት ገልጸዋል።

‹‹ከአሽከርካሪው ወገን ደግሞ የሚነሳ ጥያቄ ካለ ሥራቸውን ሳያቆሙ፣ ህብረተሰቡ አገልግሎት እያገኘ በማኅበር ወይም በተወካይ በኩል ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፤ ብለዋል። የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ ላያገኙ ይችላሉ፣ ነገር ግን ምላሽ ይኖራቸዋል።›› በማለት ተናግረዋል።

‹‹ከተነሱት ጥያዎች መሀከል አንዱ የሆነው የቅጣት እርከን ሲሆን፣ የእርከን ቅጣት አዲስ ሳይሆን ለአንድ ዓመት ያክል እየተሠራበት ያለ ነው። በዚህ አሠራር መሰረት አሽከርካሪው እየተቀጣ ሲመጣ ጥያቄው እየጨመረ መጣ። ይህ ማለት ቁጥጥሩ እና ክትትሉ የበለጠ እየተጠናከረ ሲመጣ የሥነ ምግባር ጥሰት አይኖርም ማለት ነው።›› በማለት ገልጸዋል።

አቶ አረጋዊ ‹‹ቅጣት ካለ ጥንቃቄዎች ይኖራሉ፤ ጥንቃቄ ካለ ደግሞ አደጋ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ በመሆኑ የቅጣት እርከኑ ይሻሻልልኝ ብሎ መጠየቅ ፣ ይፈቀድልኝ እና አደጋ ላድርስ እንደማለት ይቆጠራል።›› ብለዋል።
የቅጣት እርከኑ እና በዚህ እርከን ተቀጥተው አሽከርካሪዎች መሥራታቸው የከባድ አደጋ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል። ካፈው ዓመት ስድስት ወር ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት የ39 ሰዎች ህይወትን ለማዳን ተችሏል ወይንም 21 በመቶ አደጋ መቀነስ ተችሏል›› ብለዋል።
‹‹የአሽከርካሪዎች የተሓድሶ ስልጠና መስጠት ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ስልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ የተመለሱ አሉ። ከላይ የተጠቀሱት የአደጋ መቀነስ እና ሌሎች ለውጦችም የመጡት ሰፊ ቁጥጥር በመደረጉ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች በእርከን አንድ ተቀጥተን 100 ብር መክፈል ሲገባን 300 ብር ክፈሉ ተባልን በሚል ላነሱት ቅሬታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፌስ ቡክ ገጹ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ከኹለት እስከ ስድስት ነጥብ የተመዘገበበት አሽከርካሪ የገንዘብ ቅጣት 300 ብር እንደሆነ እና ከሰባት እስከ አስራ አንድ ነጥብ የገንዘብ ቅጣት 350 ብር፣ ከአሰራ ሁለት እስከ አስራ ስድስት ነጥብ የገንዘብ ቅጣት 400 ብር፣ ከአሰራ ሰባት እስከ ሃያ አንድ ነጥብ የሦስት ወር የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እገዳ እና የተሃድሶ ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ተገልጿል።

ከሃያ ሁለት እስከ ሃያ ሰባት ነጥብ የተመዘገበባቸው ጥፋተኛ አሽከርካሪዎች ለ ሥድስት ወራት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እገዳ እና የተሃድሶ ስልጠና፣ እንደሚወስዱ ከሃያ ስምንት እና ከዛ በላይ ነጥብ ደግሞ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለአንድ ዓመት ይታገድና የተሃድሶ ስልጠና እንደሚወስዱ ተገልጿል።

የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች የተጣለባቸውን ቅጣት በወቅቱ ባለመክፈል ምክንያት ከፍተኛ ወለድ እየተጠየቁ መሆን በተለያዩ አግባቦች ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን ተከትሎም ፣ቅጣቱ 100 ብር የሆነ የትራፊክ ደንብ ተላላፊ፣ ከተቀጣ እስከ 10ኛ ቀን ድረስ ከከፈለ ምንም አይነት ተጨማሪ ክፍያ የማይጠየቅ ሲሆን ከ11ኛው ቀን እስከ 30ኛው ቀን ለመክፍል ቢሄድ ግን አምስት በመቶ ተጨምሮ 125 ብር እንደሚቀጣ ተቀምጧል። ከ30ኛ ቀን በኋላ ለመክፈል ቢሄድ ግን ከ 11ኛው ቀን ጀምሮ ላሉት ለእያንዳንዳቸው ቀናት የቅጣቱን መጠን አምስት በመቶ ጨምሮ እንደሚቀጣ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com