ጥብቅ ማሳሰቢያ የተሰጠበት የኮቪድ-19 መመሪያ

Views: 64

ኮቪድ ወደ አገራችን ከገባ ጀምሮ ለ2.3 ሚሊዮን በላይ ግለሰቦች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከ200,000 በላይ ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። 154,323 የሚሆኑ ሰዎች ከኮቪድ-19 ቫይረስ አገግመዋል።
ቫይረሱ እስካሁን ድረስ ለ2,801 ግለሰቦች ሕይወት ሕልፈት እና ለብዙዎች ደግሞ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶችን መነš ሁ•ል።
ኢትዮጵያም ከአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ ሞት ካስተናገዱ የአፍሪካ አገራት መካካል ከደቡብ አፍሪካ፣ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ቀጥሎ በ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

እየተባባሰ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሰኞ መጋቢት 20 /2013 ጀምሮ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ መጣስ እንደሚያስቀጣ መጋቢት 18 ቀን 2013 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሄዱ እና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ አስገዳጅ እርምጃዎችን እና ግዴታዎችን የሚጥለውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 በሚተላለፉ ሰዎች ላይ የወንጀል ሕጉን መሰረት አድርጎ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

እርምጃውን ለመውሰድ ምክንያት የሆነው በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ አስገዳጅ የጥንቃቄ ዘዴዎችን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆን፣ በተለይም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ያለማድረግ፣ ተቀራርቦ ወይም ተጠጋግቶ መቆም ወይም መቀመጥ፣ የእጅ ንጽህናን አለመጠበቅ እና በተቋማትም ደረጃ ማስክ ላላደረገ ሰው አገልግሎት መስጠት፣ ተገልጋዮች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ያለማድረግ እና መሰል በመመሪያው የተከለከሉ ተግባራትን እና የተጣሉ ግዴታዎችን የሚጥሱ ሰዎች እና ድርጅቶች በመበራከታቸው እና ለስርጭቱ መንስዔ እየሆኑ በመምጣታቸው ተብሏል።

በመሆኑም ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጭ ማስክ በማድረግ በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ባለመጠጋት እና የእጅን ንጽህና በመጠበቅ የህግ አስከባሪዎችን እንዲተባበር የተጠየቀ ሲሆን፣ የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶችም በመመሪያው የተጣለባቸውን ግዴታ በመወጣት የስርጭቱን መጠን ለመቀነስ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠይቋል።

ይሁንና ይህን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ ፖሊስ የህዝቡን ጤንነት ለመጠበቅ ሲል እንደ ሕግ ጥሰቱ ክብደት አጥፊዎችን ከመምከር እና የመከላከል ዘዴዎቹን እንዲተገብሩ ከማስገደድ ጀምሮ የወንጀል ምርመራ እስከመጀመር ሊደርስ የሚችል እርምጃ እንዲወስድ የሥራ መመሪያ የተሰጠው በመሆኑ ግዴታውን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ መመሪያ ከወጣ አምስት ወራት ያለፉት እንጂ አዲስ አለመሆኑም ታውቋል።

በመመሪያው ከተከለከሉ ተግባራት በከፊል
ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ አገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት፣ ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ፣ የተከለከለ ነው።

ማንኛውም ሰው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አሰፈላጊነ አለመሆኑ እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ከመኖርያ ቤት ውጪ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ከስድስት አመት በታች የሆነ ህጻናት ወይም በማሰረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንም።

በግለሰቦች ላይ የተጣሉ ግዴታዎች
እራሱን ኮቪድ አለብኝ ብሎ የሚጠረጥር ማንኘውም ሰው ለሚመለከተው አካል ሪፖርት በማድረግ የመመርመርና ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳያስተላፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል።
በተጨማሪም በሽታው አለበት ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ሰለመኖሩ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለጤና ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በአቅራቢያው ለሚገኙ የጤና ተቋም ወይም ባለሙያዎች የማሳወቅ ግዴታ አለበት።
ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ መንግስታዊ እና የግል ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ እና ተገልጋዮች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎች መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

እንደ ትራንስፖርት እና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የተጣሉ ግዴታዎችም አሉ
አገር አቀፍም ሆነ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በህግ ከሚወሰነው የመጫን አቅም ልክ ሰዎችን የመጫን፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት አለመስጠት፣ መስኮቶችን በመክፈት በተሽከርካሪው ውስጥ በቂ የአየር ዝውርውር እንዲኖር የማድረግ እና በዘርፉ በመመሪያ የሚወጡ ሌሎች መወሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመተግበር፣ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

እንዲሁም በሆቴል፣ በአስጎብኚነት እና በሌሎችም የቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ተቋማት በሰራተኞቻቸው እና ተገልጋዮቻቸው መሀከል ሁለት የአዋቂ እርምጃ ወይም የሁለት ሜትር ርቀት እንዲኖር የማድረግ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን የመቆጣጠር፣ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ተግባራትን የመፈተፀም ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን መጣስ የሚያስከትለው ቅጣት
በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች እና ግዴታዎች ተላላፊ በሽታን ለመከላከል እና ለመግታት የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች አካል ሲሆኑ ክልከላዎቹን መተላለፍ እና ግዴታዎቹን አለመወጣት አግባብ ባለው የወንጀል ህግ እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጎ ይገኛል።
ድንጋጌዎቹን ተላልፎ የተገኘ በተፈጥሮ ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ተላላፊ በሽታን ለመከላከል፣ ለመግታት ወይም ለማቆም በህግ የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቦ የጣሰ እንደሆነ ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል። እንዲሁም ወንጀሉ የተፈፀመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ መሆኑን አንቀፅ 522/2 ይደነግጋል።

የኮቪድ 19 አስገዳጅ መመሪያ በወጣበት ወቅት የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው መመሪያው ሦስት ነገሮችን ያገናዘበ መሆን እንደሚገባው ገልጸው፣ኅብረተሰቡ ራሱ ጤናውን እንዲጠብቅ ስለ ቫይረሱ ተከታታይ እና በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል በሁሉም ዘንድ ቁርጠኛ መሆን ፣እንዲሁም ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል፤ በማለት ሀሳባቸውን መስጠታቸው ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com