ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ ደመቀ መኰንን

Views: 222

ኢትዮጵያውያን ለአገራቸውና ዳር ደንበራቸው ቀናኢ ናቸው። በቅርቡ የሱዳን ወታደራዊ ኀይል በሰሜኑ የአገራችን ደንበር የፈጸመው ወረራ እና የመንግስት የተድበሰበሰ ምላሽ ህዝቡን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው። በዚህ ዓምድም ጌጥዬ ያለው የወረራውን ጥለቀትና ታሪካዊ ዳራ በማንሳት የመንግስት ባለስልጣናት ግልፅ መልስ ይሰጡ ዘንድ ይሞግታል።

ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ ደመቀ መኰንን
ሱዳኖች ኢትዮጵያውያን የጉልበት ሰራተኞችን በእሳት ስለ ማቃጠላቸው!
‹ሰዎች ለሰዎች› የተሰኘው የጀርመኑ ተራድኦ ድርጅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ሠርቷል። በዚህም መሥራቹ ካርል ሄንዝ በሕዝብ ዘንድ ተወደዱ። ታዲያ በአንድ የምርጫ ወቅት ኢሕአዴግ ‹ነፍጠኛ› እያለ ሲጨቁነው ወደ ኖረው የሸዋ አማራ የ‹ምረጡኝ› ቅስቀሳውን ይዞ ሄደ። በወቅቱ የመርሐቤቴ ሰው ‹‹ካርል የሚወዳደር ከሆነ እርሱን እንመርጣለን። ከእርሱ ውጭ ምርጫ የለንም።›› ማለቱን የሰማሁት እኔ ብቻ ነኝ የሚል ግምት የለኝም። ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እርስዎም ሰምተው እንደሚሆን እገምታለሁ። እንዳውም ከእኔ ወፏ ነገረችኝ ዓይነት ወሬ ይልቅ እርስዎ በሪፖርት ደረጃ የተጠናቀረ መረጃ ከበታች ካድሬዎችዎ ደርስዎት ይሆናል። ኧረ እንዳውም ‹ካርል የሚባል ሶላቶ ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርገን እናስወጣልን› የሚል ደርጅታዊ ግምገማም አድርጋችሁ ይሆናል። ከእናንተ መካከል ‹ካርል ሄንዝን የኢሕአዴግ እጩ ተወዳዳሪ እናደርጋለን። የተመራጭ ሕጉንም እናሻሽላለን› ያለ ካድሬም ይኖር ይሆናል። እርስዎ ኖት የሚያውቁት።

ይህንን ያስታወስኩት ጎንደርን ባሰብኩ ጊዜ ነው። በዚህ በእርስዎ የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነትም ዘመን ሱዳን የኢትዮጵያን የደንበር ሉዓላዊነት ገርስሳ ገብታለች። ካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ አሁን ከዕለት ዕለት ምሽጎቿን እያበዛች እና ወደ መሀል ጎንደር እየገሰገሰች ነው። ዘመናዊ የቡድን እና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቀ ሰራዊቷ ኢትዮጵያን የወረረው በመንግሥትዎ መልካም ፈቃድ እንደሆነም የሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተናገሩ ናቸው። በርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ቃል አቀባይዎ ዲና ሙፍቲ፣ አለቃዎ አብይ አሕመድ የወለፈቱትን ለማስተስርይ ሞክረዋል። ማስተባበያውም ቢሆን ‹አልሸሹም ዞር አሉ› አይነት ነው። የሱዳን ወታደሮች የጎንደርን ገበሬዎች ከዕለት ዕለት ይበልጥ እያፈናቀሏቸው ነው። አዝመራቸውን እና ከብቶቻቸውን እየዘረፉባቸው ነው። ሰዎችን አፍነው እየወሰዱ ነው። በተለይም ከሰሞኑ አሚራ ሐውልት ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ላይ አፈና እና እገታው እንደ ሰሞነኛው የምርጫ ቅስቀሳችሁ ደርቷል። ታግተው ከተወሰዱት መካከል ሻምበል እና ይልቃል የተባሉ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሳሉ። የጉልበት ሠራተኞች ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል በተለይ በሱዳን ወታደር ተገድለው በሳር እሳት ተለብልበው አስክሬናቸው የተቃጠለ ሁለት ሰዎች ጉዳይ አሳዛኝ ነው። ይህ ሲሆን የእርስዎ መንግሥት ዜጎቹን ለማዳንም ሆነ ሉዓላዊነቱን ለማስከበር ምን አደረገ? የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለብሔራዊ ምስጢርነቱ ስል ቁጥሩን የማልገልፀው ሰራዊት ደለሎ እና አብደራፊ ላይ እንዳለው አውቃለሁ። ከመከላከያ በተጨማሪ የዐማራ ልዩ ኃይል እና የፀረ ሽምቅ ታጣቂዎችም በዚያው እንዳሉ ሰምቻለሁ። ታዲያ ይህ ሃይል አገሩን እና ዜጎቹን የሚከላከለው መቼ ይሆን?

አቶ ደመቀ ሆይ፤ የሱዳን መንግሥትና ሰራዊት ‹ቤንሻንጉል ጉምዝ የእኛ ነው› እስከ ማለት ደርሰዋል። ሰራዊታቸው ጎንደር ከተማ ድረስ ያልዘለቀውም በአማራ ፋኖ መካችነትና ጀግንነት እንደሆነ ጎንደር በሰነበትኩባቸው ጊዜያት ተረድቻለሁ። አገር እየጠበቀ ያለው እርስዎ በሬ የሚቀልቡት መከላከያ ሳይሆን በሶ እየጠጣ በዱር በገደሉ የሚንከራተተው ፋኖ ነው። የዐማራ ሕዝብ ‹ፋኖ የሚወዳደር ከሆነ እንመርጣለን። ከፋኖ ውጭ ምርጫ የለንም፤ ወግድ›› ቢል ከካርል ታሪክ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ይህ ሕዝብ ብልፅግና ፓርቲ በመፈንቅለ መንግሥት ከተወገደው የኡማር አልበሽሩ ብሔራዊ ኮንግረስ ጋር ቢምታታበትስ ጥፋቱ የማን ነው? መቼም እርስዎ ብዙ የምርጫ ዘመኖችን ስላሳለፉ ይህንን በደንብ የሚረዱት ይመስለኛል። የምርጫውን ጉዳይ ለዛዲግ አብርሃ ልተወውና እንደ ውጭ ጉዳይ ሚንስትርነትዎ ወደ ሱዳን ወረራ ልመልስዎ።

ከመተማ ከተማ ወደ ሰሜን አቅጣጫ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የመነኩሴዋ ሻይ ቤት የሚባል ቦታ አለ። በእዚህ ቦታ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ አቶ ሞላ ደስታ የተባሉ ባለንብረት ታግተው ተወስደዋል። በጎቻቸው፣ ላሞቻቸው እና አህዮቻቸው ተዘርፈዋል። የሱዳን ወታደሮች እረኞችን እና በአካባቢው የተገኙ የጉልበት ሠራተኞችን ሁሉ አፍነው ወስደዋል። ተስፋዬ ወርቁ፣ መልካሙ፣ ለምለም እና አደራጀው የተባሉ ባለሀብቶች ሁሉ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከመተማ ከተማ በግምት ከመቶ እስከ አምሳ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ገለባት ከተማን የሱዳን ሰራዊት እየጠበቀው ነው። ከተማው ውስጥ ምሽጎች ሠርቷል። ከተማዋን ከሚከፍለው አስፋልት መንገድ ግራና ቀኝ ምሽጎች አሉት። ከዚህ ጀርባ ደግሞ ሌላ ሦስት ምሽጎች አሉ። አንደኛው ጠቅላላ ምሽግ ነው። ይህ ቅይጥ ጦረኞች ያሉበት ነው። ኹለተኛው የእግረኛ ምሽግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሜካናይዝድ ማዕከል ሆኗል። የሱዳን ሰራዊት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በምዕራብ ጎንደር በኩል ከወረራቸው ቦታዎች መሀከል አብደራፊ፣ አቦጥር፣ ኮረድም፣ ኮር ሁመር፣ ስናር ተራራ (ሱዳን ግዛት ውስጥ ያለው ስናር ከተማ እንዳይመስሎት። ይሄ ተራራ፤ ያ ከተማ። ይሄ ጓንግ ወዲህ ማዶ፤ ያ ጓንግ ወዲያ ማዶ፤ አይገናኙም።)፣ ደለሎ ቁጥር 1፣ ደሎሎ ቁጥር 2፣ ደለሎ ቁጥር 3፣ ደለሎ ቁጥር 4፣ ደለሎ ቁጥር 5፣ ማሩ ሻይ ቤት፣ አዲስ ዓለም፣ ኮርጃ ሀሙስ፣ መነኩሴዋ ሻይ ቤት እና ቄሱ ሻይ ቤት ይጠቀሳሉ። ከመተማ ደቡብ ክፍል ደግሞ ምንዳያና ፎርጊና ተወረዋል። ቲሃ ውስጥ ስኳር ተራራ (ሱዳኖች ጀበል ስኳር የሚሉት)፣ ቋራ ቁጥር 2፣ ኪዳነ ምህረት እና ነፍስ ገበያ የወራሪው ሰራዊት መዳረሻዎች ናቸው።

ሱዳኖች በክረምት ወቅት ለመንቀሳቀስ እንዳይቸገሩ ጓንግ ወንዝ (ሱዳኖች አትባራ ይሉታል) ላይ እስከ አብደራፊ ድረስ ስድስት ድልድዮችን እየገነቡ ነው። አንደኛው ድልድይ ፍንዱስ ላይ ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ከፍንዱስ በላይ ነው። በረከት ላይ፣ አሲራ ላይ እና ባሕረ ሰላም (አቦጥር) ላይ ሌሎች ድልድዮች እየተገነቡ ናቸው። በተጨማሪም የጓንግ እና የአንገረብ ወንዞች መገናኛ ላይ ሌላ ድልድይ ተጀምሯል። የሱዳን መሪዎች በየጊዜው በሄሊኮፍተር እያረፉ የኢትዮጵያን መሬት በሽንሸና ለገበሬዎቻቸው እያከፋፈሉ፣ በየቀኑ ግዛታቸውን እያስፋፉ ነው። ለዚህ ደግሞ ወያኔ ለዘመናት አስፍሯቸው የኖሩ የትግራይ ባለሀብቶችም ጭምር ተባባሪዎች ናቸው። የእርሻ ማሳቸውን በፈቃዳቸው እየለቀቁ ሱዳን ኢትዮጵያን እንድትወር መንገድ መሪ ሆነዋል።

በነገራችን ላይ ይህ ወረራ ሱዳን በየዓመቱ በኢትዮጵያ ላይ ከምታደርገው ትንኮሳ የተለየ ነው። የተለመደውን ዓይነት ወረራ ባለፈው ዓመት በተለይ በግንቦት ወር በተጠናከረ ደረጃ አድርጋለች። በዚህም ታጣቂ ቡድኑ ጓንግን ተሻግሮ የኢትጵያ ግዛት ውስጥ ኮረዲም፣ ምድሪያ፣ ግራር ውሃ የተባሉ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ነበር። የተለያዩ የአረቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ኢትዮጵያ ለሱዳን ለም የእርሻ መሬት ለመስጠት መስማማቷን ዘግበዋል። ከእነዚህ መካከል ‹አሽራክ አልሳውት› የተባለው ጋዜጣ ጉዳዩን በስፋት አስነብቧል። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ኢትዮጵያ በ1995 ዓ.ም በአቶ አባይ ፀሐዬ ፊታውራሪነት ከተሰጠው በተጨማሪ 600 ስኩየር ኪሎ ሜትር ለም የእርሻ መሬት ለመስጠት መስማማቷን ፅፏል። የመሬት እርክክቡም በኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አብራርቷል። ዛሬ የሱዳን መንግሥትና ሰራዊት የወረራ ግዛቱን ማስፋቱ የዚህ ስምምነት አካል ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ስህተት አይሆንም። ክቡር ሚንስትር ሆይ! መቼም ይሄን የገዱ አንዳርጋቸው እና የአብይ አሕመድ ስምምነት ነው ብለው እንደማያልፉት ተስፋ አደርጋለሁ። ተስፋዬ ከንቱ ምኞት ሊሆን እንደሚችል ደግሞ የ1995 ዓ.ም. ታሪኮ ይነግረኛል። ለሱዳን ስለሰጡት የደለሎ መሬት ተጠይቀው ‹‹በእነ አባይ ፀሐዬ መሪነት የቃል ስምምነት ከሱዳኖች ጋር ተደርጓል። ፊርማውን አላውቅም። ያን ጊዜ የክልል አመራር ነኝ። የክልሉ መንግሥት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመፈረም ስልጣንም የለውም።›› ያሉትን አስታወሱ ወይ? የኢትዮ-ሱዳን ጉዳይ ከእርስዎ አልሸሽ አለ። ይኸው ታሪክ መልሶ በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት አመጣዎ። እርስዎ ባይዘነጉትም ይች ደብዳቤ ግልፅ ስለሆነች እስኪ ለለጋ ካድሬዎችዎ ታሪኩን እናስታውሳቸው፤

በ1995 ዓ.ም. ለሱዳን የተሰጠው የኢትዮጵያ መሬት
በ1988 ዓ.ም. የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚደንት በአዲስ አበባ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው። ሙከራውን ያደረጉት ደግሞ ሱዳናውያን ነበሩ። ወንጀለኞች ሩጠው ሀገራቸው ገቡ፤ ሱዳን። የኢትዮጵያ መንግሥት የግድያ ሙከራውን ያደረጉት ግለሰቦች እንዲሰጡት ቢጠይቅም የሱዳን መንግሥት ዜጎቹን አሳልፎ እንደማይሰጥ ተናገረ። በዚህ ምክንያ በዚያው አመት የኢትዮጵያና የሱዳን ጦርነት ተደረገ። በኢትዮጵያ አሸናፊነትም ተጠናቀቀ። የደርግ መንግሥት ተወግዶ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሱዳናውያን በጎንደር በኩል የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥረው ነበር። ይህንን ለማድረግ ኹለት መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅመዋል።

አንደኛው፣ ሕወሓት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ሱዳን ታግዘው ስለነበር ያለፈ ውለታዋ የኢትዮጵያን መሬት እንድትወስድ አስችሏታል። ሁለተኛው፣ ኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ አለመረጋጋት ላይ ስለነበረች ሁነቱ ለሱዳን አመችቷታል። አገሪቱ በሽግግር መንግሥት የምትመራበትና በርካታ ነገሮች ፈርሰው እንደ አዲስ የሚገነቡበት ጊዜ ስለነበር ለሱዳን አመች ነው። በየጊዜው ስለ አገር የሚጮሁ ምሁራን ሁሉ ተገልለው ፊደል ያልቆጠሩ ወያኔዎች ጠመንጃ እያንቀጫቀጩ በዋና ዋና የሀገሪቱ ተቋማት የሚዘዋወሩበት ጊዜ ነበር። ታዲያ በዚህ ጊዜ ወራው የነበረውን መሬት ሱዳን በ1988ቱ ጦርነት ለቀቀች። ሱዳን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተቃዋሚዎችን የመደገፍ ልምዷ ከፍተኛ ነው።

ሕወሓት ተቃዋሚ በነበረ ጊዜ ትደግፈው እንደነበረው ሁሉ ተገልብጣ የሕወሓትን ተቃዋሚዎች ደግሞ መደገፍ ጀመረች። ጥቂት የማይባሉ ተቃዋሚዎች ሱዳን ውስጥ እየመሸጉ ሕወሓትን ለሥልጣኑ አሰጉት። ቀጥሎም ኹለቱ አገራት በምስጢራዊ ድርድር ተስማሙ። በዚህ ሂደት ተለዋዋጩ የሱዳን ባህሪ በርካቶችን ዋጋ አስከፍሏል። ሱዳን ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር የውክልና ጦርነት የምታደርግባት አገርም ነች። በመሆኑም የራሷን ጥቅም እስካስከበረላት ድረስ በየጊዜው አቋሟን ትቀያይራለች። እስስት የሆነችው ሱዳን በሀገሯ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ለሕወሓት አሳልፋ ሰጠች። የመሬቷን ጉዳይም አልዘነጋችም። በ1988 ዓ.ም. መልሳ ያጣችውን የኢትዮጵያ መሬት እንዲመለስላት ጠየቀች፤ ወያኔ ፈቀደላት። የኢትዮጵያ ገበሬዎችን አፈናቅላ መሬቱን ዳግም ተቆጣጠረችው። በወቅቱ የነበሩት የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ ጉዳዩን በመቃወማቸው ታስረዋል።

ይህ መሬት በ1995 ዓ.ም. ለሱዳን በድጋሜ ሲሰጥ የወቅቱ የኢትዮጵያ የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስቴር ሚንስትር የሕወሓቱ አቶ አባይ ፀሐዬ ከአዲስ አበባ መተማ፣ ደለሎ ድረስ በሄሊኮፍተር ሄደው መሬቱን አስረከቡ። በአስር ሺህዎች ሄክታር የሚቆጠር ማለትም አብዛኛው የደለሎ መሬት ተሰጠ። በዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቀሉ። በተለይም ዘለቀ እርሻ ልማት ተወገደ። በ2000 ዓ.ም. ላይም ሌላ ተጨማሪ መሬት ለመስጠት እንቅስቃሴ ተጀምሮ በሕዝብ ተቃውሞ ሳይሳካ ቀረ። አቶ አባይ እንደ መለስ ዜናዊ በእንባ የመሸኘት እድል ጠሞባቸው፣ እንደ ስብሃት ነጋ ወህኒ ቤት ውስጥ መቀመጥም ከፕላኔት ሆቴል በላይ ውድ ሆኖባቸው፣ የሱዳን ወታደሮች በእሳት እንዳቃጠሏቸው የጉልበት ሠራተኞች ደመ ከልብ ሆነዋል። አቶ ደመቀ ለእርስዎ ግን ታሪክ ዳግም እድል ሰጥቶታል። የዐማራን ሕዝብ ባይክሱ፣ ንስሀ መግብት ባይችሉ እንኳን እየሄዱበት ካለው የዳግም ስህተት መንገድዎ እንዲገነጠሉ እመክሮታለሁ።

ክህደትዎ!
‹የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን እንዲሰጥ የእርሶም እጅ አለበት ወይ?› የሚል ጥያቄ ቀርቦሎት መልሰዋል። እንዲህም አሉ፡- ‹‹እኔ በወቅቱ ‹ፊርማ ፈረምህ› በተባልኩበት ጊዜ እንግሊዝ ሃገር ለትምህርት ሄጀ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ እጄ የለበትም። እኛ በሪፖርታችን መሰረት የድሮ መሬታቸው ነው የተመለሰው (የሱዳኖች ማለት ነው) ብለናል። እዚያው እንጨት ለቅሞና ከብት ጠብቆ ያደገው ሕዝብ ‹አይደለም› ይለናል። ይሄ የደረቅ ፖለቲካ ነው። ከጓንግ ወዲህ ማዶ ሱዳኖች የኢትዮጵያን መሬት እንደያዙ ኗሪዎች ነገሩን። በእነ አባይ ፀሐዬ መሪነት የቃል ስምምነት ከሱዳኖች ጋር ተደርጓል። ፊርማውን አላውቅም። ያን ጊዜ የክልል አመራር ነኝ። የክልሉ መንግሥት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመፈረም ስልጣንም የለውም።››

እርስዎ ይህንን ቢሉም መሬቱ በ1995 ዓ.ም. ለሱዳን ከመሰጠቱ አንድ አመት ቀድሞ የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር። በወቅቱ እርስዎ አማራ ‹ክልል› ሲል ሕወሓት ለሰየመው አካባቢ የአስተዳድርና ፀጥታ ቢሮ ሓላፊ ነበሩ። የድንበር ኮሚሽኑ መሥራች አባልም ነበሩ። የኢትዮ- ሱዳንን ድንበር የሚወስነው እና መሬቱ ለሱዳን ስለ መሰጠት አለመሰጠቱ የሚወስነውም ይኸው ኮሚሽን ነው። ስለዚህ የክልል አመራር በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመፈረም ስልጣን እንደለሌለው የገለፁበት አመክንዮ ፉርሽ ይሆናል። ምክንያቱም የድንበር ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመ ነውና።

‹‹እጀ የለበትም፤ አልፈረምኩም።›› ቢሉም መሬት በእነ አባይ ፀሐዬ ሲሰጥ ግን ያውቁ እንደነበር አልሸሸጉም። ስለዚህ መሬት የወቅቱ የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ በ1996 ዓ.ም. ከብአዴን ተባርረዋል፤ ታስረዋል። ከዚኽኛው አስተዳዳሪ በፊት የነበሩት የወረዳው አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደሳለኝ አንዳርጌ ሽፍታ ተብለው በሱዳን መንግሥት ቲሃ የተባለች የሱዳን ከተማ ድረስ ታፍነው መወሰዳቸውን በአንድ ወቅት ይፋ ባደረጉት የፅሁፍ ሐተታ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በኋላም በትምህርት ምክንያት አስተዳዳሪነታቸውን ለቀዋል።

በዚህ ጊዜ እርስዎ የ‹ክልሉ› ከፍተኛ አመራር ኖት። የፓርቲውም ጭምር። የወረዳው አስተዳዳሪዎች ሲፈራረቁ ከሕዝቡ ጋር በመሆኑን ለበላይ አመራሮች ጉዳዩን ያሳውቁ እንደነበር ተናግረዋል። የበላይ አመራር ከተባሉት መካከል የአስተዳድርና ፀጥታ ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ደመቀ ጉዳዩ ቀድሞ እንደሚደርስዎት አያጠራጥርም። ታዲያ ለምን መሪ ከሆኑ በወቅቱ የሕዝብን ጥያቄ ሰምተው የአገሪቱን ሉዓላዊነት አላስከበሩም? ለምንስ የሚመሩትን የዐማራ ሕዝብ ደህንነት አላስጠበቁም? ተባባሪ አልነበሩም ወይ? በዚህ ጉዳይ እጄ የለበትም ማለትስ ምን አይነት ክህደት ነው? የሕዝብ መሪ እኮ ኖት። ዋናው ወንጀል ሕዝቡን አሳልፈው መስጠትዎ እና ሉዓላዊነትን በማስደፈሩ ጉዳይ ተባባሪ መሆንዎ አይደለምን? በጉዳዩ ከተስማሙ የወረቀት ፊርማውን ፈረሙና አልፈረሙስ ምን ይፈይዳል?

ይህ የደለሎ መሬት አሁንም ድረስ በሱዳኖች እንደተያዘ ነው። ባለፈው ግንቦት ተሰጠ የተባለው ለም የእርሻ መሬት ደግሞ ሱዳን በአባይ ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለኢትጵያ በሚደግፍ መልኩ እንድታደርገው የታሰበ መሆኑን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት ጊዜ ነግረውናል። ‹‹ከሱዳን ጋር ያለንን ግንኙነት በተለየ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው የምናየው። ምክንያቱም የአባይ ግድብ ከሱዳን ጋር አወዳጅቶናል። በሱዳን ላይ ጦርነት መክፈት አንፈልግም።›› ሲሉ ነበር የተናገሩት። ይህ የተንበርካቲነት ዲፕሎማሲ አይመስሎትም?

ከላይ ካስታወስሆት ንግግሮ ለመረዳት የሚቻለው ትክክለኛ ድንበሩን እንደማያውቁት ነው። ወይም እያወቁ አላዋቂ ለመምሰል ሞክረዋል። ያም ሆነ ይህ ወግ ደርስዎት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ከሱዳን ጋር የሚደራደሩ ከሆነ ሊጠቅሞት ይችላልና ጥቂት የታሪክ ማጣቀሻዎችን እንቃኝ፡- በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው የሚኖረው ኢትዮጵያውይም ሆነ የተለያዩ ፀሐፊዎች የሚስማሙበት የአገራቱ ድንበር ጓንግ ወንዝ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ነገስታት ከወንዙ ወዲያ ማዶም የኢትዮጵያ ግዛት አካል አድርገው ይገዙት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። ለአብነትም ከ1624 ዓ.ም. እስከ 1659 ዓ.ም. ድረስ የነገሱት አፄ ፋሲል ይጠቀሳሉ። የዛሬው የሱዳን ከተማ ስናር ድረስ በመሄድ አስገብረው እንደነበር ‹የኢትዮጵያ የ5ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢሕአዴግ› የተሰኘው የፍስሐ ያዜ መፅሐፍ ይገልፃል። እንደራሴያቸውን ንጉስ ጊዮርጊስን በሚያስገብሩት አካባቢ ሹመዋቸው ተመልሰዋል። ሱዳንን ማስገበራቸውን በተመለከተም አዝማሪ እንዲህ በማለት ገጥሞላቸዋል፣
‹‹ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ፣
ኑብያና ስናር ወርቁን ጫኑልህ።
ሳሩን ተጠየፈ የፋሲል ፈረሱ፣
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለእርሱ።››

በተመሳሳይ አፄ ቴዎድሮስም ወዲያ ማዶ ተሻግረው ከሰላ ላይ የጦር መንደር መሥርተው ነበር። በአንፃሩ ሱዳኖች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር የሚዳዱት እንግሊዛዊው ቅኝ ገዣቸው ሻለቃ ግዎይን ድንጋይ እየካበ ያሰመረውን መስመር ተከትለው ነው።
እየተሻሻለ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ‹ቋሚ ጠላትም ሆነ ቋሚ ወዳጅ የለም› የሚል እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ‹መደመር› ባሉት መፅሐፋቸው ገልፀዋል። አለቃዎ ይህንን ቢሉም ግብፅ ከአባይ ተፈጥሮ ጋር አብራ የተፈጠረች ቋሚ የኢትዮጵያ ጠላት ነች። ይህንን ደግሞ በሱዳን በኩል እያስፈፀመች ነው። እዚህ ላይ እንደ ሱሌማን ደዴፎ አይነት አምባሳደሮች ሲጨመሩበት ጦሱን ያንረዋል። የሕይዎት ዘመን ያፖለቲካ ርዕዮታቸው ዐማራን በመጥላት ላይ የተመሰረተው የኢሳያስ አፈወርቂ ካርቱምና አዲስ አበባ መመላለስም ጦሱ ገና መቼ ተጀመረ ያስብላል።

ክቡር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆይ፤ በአጠቃላይ ሱዳን ይፋዊ ወረራ ላይ ነች። ይህን በስሙ መጥራትና መመከት ያስፈልጋል። የዐማራን ሕዝብ ሁለት ጊዜ አይግደሉት። በኦሕዴድ/ብልፅግናነት ሌላ ትውልድ መግደል አይጠበቅቦትም። በሕወሓት/ብአዴንነቶ አንድ ትውልድ ገድለዋል፤ የዘለቀ እርሻ ልማት ትውልድ። አንድ ትውልድ ስንት ነው የሚል ቆጠራ ውስጥ እንደማይገቡ እገምታለሁ። ብዙዎች የእርሻ መሬቶቻቸውን ተነጥቀው ሎተሪ አዟሪ እንደሆኑ ለማወቅ እንደ እኔ የአርቲስት ፋሲል ደሞዝን ቃለ መጠይቅ መስማት የሚጠበቅብዎት አይመስለኝም። ፋሲልን ካነሳሁ አይቀር ‹አረሱት› የሚለውን ዘፈን በደንብ ያዳምጡልኝ። በተረፈ ይችን ደብዳቤ ስፅፍሎት ለሕገ ወጥ መንግሥትዎ እውቅና የሰጠሁ እንዳይመስሎት። ከቻሉ ሥልጣን ይልቀቁ፤ ካልቻሉ የሚገዙት ሕዝብ እንዳያጡ ከወራሪ ይጠብቁን ነው ምክሬ።

ጌትየ ያለው
nawsgett@gmail.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com