ኮሮና- ጦርነት-ጭፍጨፋ-ምርጫ!!

Views: 103

የኮቪድ-19 አያያዝ አጠያያቂ ከሆነባቸው አገራት እንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ እንኳ ገዥው ፓርቲ የሚጠራቸው ስብሠባወች፣ የድጋፍ ሰልፎች፣ የምረቃ ስነ-ስርዓቶችና የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ሕዝባዊ ግርግሮች (ንቅናቄወች) ወዘተ… በተደጋጋሚ ሲካሄዱ ተስተውለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልቅ በሆነ መንገድ መነሳቱን ተከትሎ ሰልፎች፣ አውደ-ርዕዮች፣ ስብሰባወች፣ ስልጠናወች፣ አላስፈላጊ የስፖርት ውድድሮች፣ በዐስር ሽወች የሚቆጠሩ ሰወች የሚገኙባቸው ተከታታይ የማስ ስፖርት መርሐ-ግብሮች ወዘተ….. ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተወ ቡራኬ እየሰጡባቸውና የፖለቲካ ዲስኩር እሰሙባቸው ተካሂደዋል።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ጤና ሚ/ር እና አጋሮቹ ኮቪድ-19 በአደገኛ ሁኔታ በመላ አገሪቱ መስፋፋቱና የተጎጅወች ብዛት እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን በማወጅ ለዚህ አደገኛ ችግር መስፋፋት ሕዝብ ተጠያቂ ተደርጓል። የሚገርመው በትንሹና በትልቁ ባለስልጣን አንደበት ለኮቪድ-19 መስፋፋት ሕዝብ በተደጋጋሚ ተጠያቂ ሲደረግና ሲወነጅል በአዲስ አበባ ከተማ ከሚካሄዱ አደገኛ ወንጀሎች ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ በየቦታው እስከ ሚካሄዱ ጭፍጨፋወች፣ ግጭቶች፣ ውድመቶች፣ የሕዝብ መፈናቀሎች ወዘተ ደግሞ የጁንታው እጅ አለበት እየተባለ ሕወሐት ተጠያቂ እየተደረገ ነው። ሕወሐት ሞተ ተብሎም እየተጠየቀ ነው። ዓቅምና እውቀት አለኝ ተብሎ ስልጣን ከተያዘ በኋላ በዓመት 365 ቀናትን ሌላውን እየወነጀሉና ተጠያቂ ነው እያሉ አገርን ከዓመት ወደ ዓመት ወደ አዘቅት መጨመር ተገቢና ሩቅ ለመጓዝ የሚረዳ አይደለምና ሊታሰብበት ይገባል። ለላፉት ሶስት ዓመታት የታዩት አስተዳዳራዊ መዝረክረኮች ከአመራር ብቃት ማነስ የሚመነጩ ችግሮች አገሪቱን በአደገኛ አፋፍ ላይ ቆማ እንድትታይ እንዳደረጋት ግልጽ ነው። መከራወችና ችግሮች ከፍተኛ ኪሳራ ካደረሱ በኋላ ተላላኪወች ነበርን ብሎ ራስን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ መሞከር የተበላ ቁማር ሊሆን ይችላል።

በጤና ሚ/ር በኩል የተስተጋባው ስጋት ለብዙወች ድንገተኛ አልነበረም። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደ ሽፋን በመጠቀም በተቃዋሚወች በኩል የሚደረጉ የምርጫ ቅስቀሳወችንና እንቅስቃሴወችን ለማገድ ወይም ለማሳነስ የሚሰራ ስራ ሊኖር እንደሚችል የብዙወች ጥርጣሬ ነበረ። እንደተፈራውም ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ ሰወች ከ50 በላይ ሆነው እንዳይሰባሰቡ የሚልና ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያሰናክል ሰው እስከ 3 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ የሚችል መሆኑ ተነግሯል። የዚህ ማስጠንቀቂ አፈጻጸም የገዥው ቡድን ኮቪድ-19ኝን ተቀናቃኞቹን ለማዳከምና ለማሳደድ መጠቀሙንና አለመጠቀሙን የሚያሳይ ይሆናል።

የከዚህ በፊት በጤና ሚ/ር በኩል የኮሮና ወረርሽኝ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም የሚል ሃሳብ ለምክር ቤት አቅርቦ ምርጫ-2012 ሲሰረዝ መንግስትም በበኩሉ የወረራ ስጋት አለብኝ ብሎ የምርጫውን መሰረዝ አጨብጭቦ ተቀብሎት ነበረ። አሁን በዚህ ጊዜ ኮቪድ-19 ከመቼውም ጊዜ በላይ በመላ አገሪቱ ተንሰራፍቷል፣ የወረራ ስጋቱ ዕውን ሆኖ ሱዳን ግዛቴ ነው የምትለውን መጠነ ሰፊ መሬት በጉልበት ይዛ የእኔ ነው የምትለውን ተጨማሪ መሬት እንዲለቀቅላት እየጠየቀች ነው። ግብጽ የአባይ ግድብን በውኃ የመሙላት ዕቅድ እየተቃወመች የውኃ ድርሻየ በጠብታ ከተቀነሰ ምስራቅ አፍሪካን ትርምስምሱን ሊያወጣ የሚችል ጦርነት ሊከሰት ይችላል እያለች ነው። በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ከ1981 ዓም በፊት በዚያው ሲካሄድ ወደ ነበረው ዓይነት ሽምቅ ውጊያ የመመለስ አዝማሚያ እየታየበትና ሕወሐት እንደሚካሂዳቸው የሚጠረጠሩ ግድያወች በከተሞች እየተፈጸሙ ነው። ትግራይ ሚዲያ ሐውስ ሊገደሉ የሚችሉ ሰወችን በስም እየጠቀሰ ማስጠንቀቂ ከመስጠት አልፎ እርምጃ የተወሰደባቸው ‘ባንዳ የብልጽግና ተላላኪወች’ ነበሩ የሚላቸውንና በሕወሐት እርምጃ የተወሰደባው የሚላቸውን ተጋሩ ስም በየጊዜው ይጠራል። በሮምያና በቤኒሻንጉል አንዳንድ አካባቢወች መጤወች በሚባሉ ሰላማዊ ነዋሪወች ላይ፣ ሕጻናትንና አዛውንቶችንም ጨምሮ ግልጽ የጭፍጨፋ ዘመቻወች ሞቅ ቀዝቀዝ እያሉ እየተካሄዱባቸው ነው። ይህን መሰሉ ጭፍጨፋ በአማራ ክልል ኦሮምያ ዞን እያሰለሰ እየተከሰተ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ሰላማዊና ዲሞክራሲዊ ምርጫ እንደሚካሄድ እየተነገረ ነው።

እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት አንድ ነገር በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ለዘበኝነት የማይመጥኑ ሰወች ለስርዓቱ ታማኝ ተላላኪ ለመሆን ያላቸው ዝግጁነትና ተነሳሽነት ብቻ እየታየ ለሹመትና ለኃላፊነት ይበቁ የነበሩ መሆኑና አሁንም እነሱው በየቦታው ተኮፍሰው የሚገኙ መሆኑ ነው። ለዘነኝነት የማይመጥኑ የሚለው ያሹማምንቱ መገለጫ በአቶ መለስ ዜናዊ የተነገረ መሆኑ የሚረሳ አይደለም። በስርዓቱ በሰፊው እንደታየው ለዘበኝነት የማይመጥኑ የሚለው መገለጫ ‘ሳይማሩ የተማሩ’ ሆነው ለከፍተኛውም ሆነ ለዝቅተኛው የሹመትና የኃላፊነት ቦታ የሚመደቡ ሰወችን የሚወክል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተምረውና በከፍተኛ የእውቀት ደረጃ ላይ ደርሰው የስልጣን ጥማውና ጥቅማ ጥቅሞችን የማሳደድ ስስታው ሙያቸውን ክደው የፖለቲከኞች ተላላኪወች የሚሆኑ ምሁራንንም ጭምር የሚያካትት ነው ብሎ መገመት ይቻላል።

ኢትዮጵያችን መንግስት የሌላት እስክትመስል ድረስ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የምትታመሰውና ሕይወትን እየነጠቁ ባሉ አደገኛ ቀውሶች የምትንገላታው ለውጡን የማይደግፉና የኢትዮጵያን ሕልውና የማይሹ ቡድኖችና ግለሰቦች በሰፊው በመሰራጨታቸው ብቻ ሳይሆን ለዘበኝነት የማይመጥኑ የሚባሉት ግለሰቦች ከፌደራሉ ስልጣን ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉ የኃላፊነት ቦታወች ስለሚጨፍሩበት መሆኑ የሚካድ አይደለም። እነዚህና እነዚኞቹ የሚተባበሩባቸውና አብረው የሚሰሩባቸው አጋጣሚወችም እንዳሉም መንግስት ራሱ ደጋግሞ ያመነበት ጉዳይ ነው። ሌላው ጉዳይ ይቆይና ሰሞኑን ኮቪድ-19 ስለመስፋፋቱ፣ የእልቂት አደጋ እያንዣበበ መሆኑ በተነገረ ቁጥር ሕብረተሰቡ ተጠያቂ እየተደረገ በመሆኑ ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ማስክ መጠቀምን ግዴታ የማድረግ ዘመቻ ወይም ንቅናቄ ጀምሬአለሁ ሲል ይሰማል። ይህን ዘመቻ ለማስጀመርም ከጥር 3/2013 ዓም ጀምሮ ስብሰባወች፣ ንግግሮችና የመገናኛ ብዙሐን ግርግሮች ጎልተው እየታዩ ነው። ከነዚህ የንቅናቄ ግርግሮች አንዱ ጥር 4/2013 የጤና ሚ/ሯ በተገኙበት የተካሄደው ስብሰባ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉ የፖለቲካና የኃይማኖት ባለስልጣናት ሁሉ ንግግር ያደረጉት ማስካቸውን ሳያወልቁ ነው። ማስክ አድርገው ንግግር ካደረጉት ባለስልጣናት መካከል አቶ ጃንጥራር አባይ ይገኙበታል። አቶ ጃንጥራር አባይ አዲሰ አበባ ውስጥ ዕሑድ ዕሑድ በክፍል ከተሞች በሚካሄደው የማስ ስፖርት ከሕዝብ ፊት ለፊት በመድረክ ላይ ሆነው ዱብ ዱብ ሲሉ የሚታዩ ሰው ናቸው። በነዚህ ዕሁዶች አቶ ጃንጥራርና መድረኩ ላይ ሆነው ሕዝቡን ወይም ማስ ስፖርቱን ከሚመሩ ሰወች ብዙወቹ ማስክ ሳያደርጉ ነው ስፖርቱን ሲመሩ የሚታዩት።

እንደ አዲስ ቲቪ ወሬ ከሆነ ደግሞ በነዚህ ማስ ስፖርቶች ከአምሳ ሸህ እስከ መቶ ሽህ ሕዝብ ተገኝቶ ነው ‘ስፖርት ለጤንነት’ እያለ አደባባዮችንና ጎዳናወችን ሞልቶ ሚታየው። ሁሉም ሰወች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ወደ ስፖርቱ ሲመጡ ማስክ አድርግው ሚታዩ ቢሆንም ስፖርቱ እየቀጠለ ሲሄድ በጣም ብዙው ሰው ማስኩን በክርኑ አንጠልጥሎና በኪሱ ውስጥ ወሽቆ ነው ሰፋ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፈው። ስፖርቱ እየቀጠለ ሲሄድ አየር እንደሚጥር፣ ከላይ ከላይ በፍጥነት መተንፈስ የግድ አንደሚሆንና የኦክስጅን እጥረትን የሚስከትል ይህ ደግሞ ማስክ መጠቀምን አስጨናቂ እንደሚደርገው ማንም አይስተውም። የማስ ስፖርትም ሆነ ሌሎች የስፖርት ውድድሮች የሚጠሩት ይህ ሁሉ እየታወቀ ነውና ለኮቪድ-19 መስፋፋትም ሆነ ይመጣል ለሚባለው እልቂት ሕዝብ ተጠያቂ ማድረግ ኢ-ማራላዊ ነው። ከዚህ ሌላ በፌርማታወች፣ በገበያ ቦታወችና በሌሎች ስፍራወች ማስክ የማይጠቀሙና ቸልተኝነትን የሚያሳዩት የተወሰኑ ሰወች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባናል ለኮቪድ-19 መስፋፋት እነዚህ ቸልተኛ ግለሰቦች፣ ግለሰቦቹ ሕግንና መመሪያን እንዲጥሱ የፈቀዱ ሕግ አስከባሪወች፣ በየሰበቡ ሕዝብ እንዲሰበሰብ የሚያርጉ የብልጽግና ሹማምንትና ባለስልጣናት ከማንም በላይ ተጠያቂወች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል።

እሁድ እሁድ አዲስ አበባ ውስጥ ኮሮና የለም ካልተባለ በስተቀር በነዚህ ተሳታፊወች በአብዛኛው ማስካቸውን አውልቀውና ከሰው ብዛት እንጻር ተገቢውን ርቀታቸውን መጠበቅ በማይችሉባቸው አጋጣሚወች ስፖርቱ ለጤንነት ሳይሆን ኮሮናን ለማሰራጨት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን መካድ አይቻልም።

እነዚህ የማስ ስፖርቶች በአዲሰ አበባ ስፖርት ኪሚሽን ስም የሚጠሩና የሚካሄዱ ቢሆንም እነዚህን የስፖርት ፕሮግራሞ ሲጠቀምባቸውና ለገጽታ ማሳመሪያ መሳሪ ሲደርጋቸው የሚታየው የአዲሰ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ነው። በነዚህ መርሐ-ግብሮች መሪ ሆነው ለመታየት የሚሞክሩት የስፖርት ምሁራንና የስፖርት ኮሚሽን አለቆች የሚባሉት ግለሰቦች ተራ የፖለቲካ ግብ ለማራመድ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያወች ብቻ ናቸው። የኮቪድ-19 አደጋን ችላ ብለው ለፖለቲከኞች መሳሪ ለመሆን የተንበረከኩ ግለሰቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ጤና ሚ/ር እና የኢትዮጵያ ሕብተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለስልጣናት ሕብረሰቡን ማስክ ለመጠቀም ቸልተኛ ሆነ ብለው ያለማቋረጥ የሚወነጅሉ ቢሆንም እነዚህን የማስ ስፖርት የሚባሉ የአዲሰ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሚያካሂዳቸው ግርግሮችን ጨምሮ በብልጽግና ፓርቲ የሚጠሩ በአዳራሾችና በስቴዲዮሞች ሕዝብ በገፍ የሚሰበሰብባቸውን ስብሰባወችን፣ ስልጠናወችን፣ የድጋፍ ሰልፎችን ወዘተ… በዝምታ ሲመለከቱ ይታያሉ። ዶ/ር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጤና ሚ/ር እና የኢትዮጵያ ሕብተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዶክተሮችና ማስተሮች፣ አቶወችና ወይዘሮወች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ኮቪድ-19 በሰፊወ እንዲሰራጭ የሚያደርጉ መሰባሰቦችን በዝምታ ያልፋሉ። እነዚህ የጤናው ዘርፍ ባለስልጣናትና ባለሙያወች ሙያዊ ሞታቸውን እየሞቱ ለመሾምና ለመሸለም የሚያቃ ሰብዕና እያዳበሩ መሆኑ ግልጽ ነው።

በብልጽግ ቡድን እና በባለስልጣናቱ የሚጠሩ በሽወች የሚቆጠሩ ሰወች የሚሰባሰቡባቸውን አገጣሚወች በዝምታ ሲመለከቱ የቆዩት የጤና ሚ/ር እበና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባከለስልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮቪድ-19 የተያዙና የሞቱ ሰወችን ቁጥሮች ተጠቅመው ቁማር ለመጫወት ዳር ዳር ሲሉ እያየን ነው። ለቁጥሮቹ ማሻቀብም ራሱን ሕዝቡን ተጠያቂ እያደረጉ ብቻ ሳይሆን እልቂት ሊከተል እንደሚችል ጭምር እያሟረቱ ነው።

በአዲስ አበባበ፣ አዲሰ አበባ ዙሪያና በበርካታ የኦሮምያ ከተሞች በየጊዜው ሚካሄዱ ብልጽግና መራሽ ሰልፎች፣ ስልጠናወች፣ አላስፈላጊ የስፖርት ውድድሮች እና ሌሎች ግርግሮች ከተበራከቱ ኮቪድ-19 በሰፊው እንደሚሰራጭ ለማወቅ ዶክተር መሆን የሚሻ ጉዳይ አይደለም። ምርምር የሚስፈልገው ጉዳይ ‘….ፖለቲከኞቹም ሆኑ እነ ሊያ ታደሰ ሕዝባዊ ግርግሮችን በቸልተኝነት የሚያካሂዱት ወይም ግርግሮቹ ሲካሄዱ በቸልታ የሚመለከቱት ከኮቪድ-19 መስፋፋት ምን ትርፍ ለማግኘት ነው?’ የሚለው ጥያቄ ነው። በእርግጥ ከፖለቲካዊ ግብ ያለፈ ሌላ አጀንዳ የላቸውምን? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።

ከወር በፊት በመላ ኦሮምያ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ በደቡብ ኢትዮጵያም በብዙ ከተሞች አንዲሁም በአማራ ክልል ወሎ ውስጥ ለጠቅላይ ሚ/ሩ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል። በነዚህ ሰልፎች ርቀትን መጠበቅ እና ማስክ መጠቀም የሚሉት የኮቪድ-19 መከላከያ ዋና ወና ዘዴወች በሰፊው የተጣሱ ቢሆንም ጠቅላይ ሚ/ሩ ስለ ተሰለፋችሁኝልኝ አመሰግናለሁ ብለው ለሰልፎቹ ቡራኬአቸውን ሰጥተው አልፈውታል። ይህ አጋጣሚ ገጽታን ለማሳመርና ፖለቲከዊ ትርፍ ለማግኘት ሲባል የሕዝብን ደኅንነት ችላ የማለቱ ጉዳይ የጠቅላይ ሚ/ሩ ችግርም መሆኑን ያጋለጠና ጠቅላይ ሚ/ሩ ጭምር ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው። ከጠቅላይ ሚ/ሩ በተጨማሪ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሚባሉ ግለሰቦችም ከተጠያቂነት የሚመልጡ አይደሉም።

ኮቪድ-19 መሰራጨት በጀመረባቸው የመጀመሪያ ወራት ማስክን ከመሳሰሉ ዝቅተኛ የመከላከያ ቁሳቁሶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የእስትንፋስ ድጋፍ መስጭያ መሳሪያወች እጥረት የነበረ ቢሆንም ወረርሽኙ ከጀመረ ከስድስትና ከሰባት ወራት በኋላ ግን እነዚህ ወሳኝ ነገሮች ማግኘት ሕዝብ ለመረዳትና ወረርሽኙን ለመዋጋት በቂ ገንዘብ የመመደብና ያለመመደብ ጉዳይ ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት በመላ ኢትዮጵያ የመተንፈሻ ድጋፍ መሳሪያወች እጥረት መኖሩና በዚህ እጥረት ብዙወች ታማሚወች ከአደጋ እተጋለጡ መሆኑ ከጤና ጥበቃ ሚ/ሯ ጀምሮ በክልሎች እስከሚገኙ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊወች እየተነገረ ነው። በርካታ ቢሊዮን ብሮችን ለፓርክ ግንባታወች፣ ለመናፈሻወችና ለቤተ-መንግስት እድሳት ወዘተ… ያለ ማቋረጥ እየከሰከሰ በምረቃ ስም በርካታ የጭፈራ ስነ-ስርዓቶችን ያካሄደ መንግስት በሚመራት አገር በዓም ገበያ ላይ ያለ ነገርን እንደ ችግር አድርጎ መናገር አሳፋሪ ነው። ጠቅላይ ሚ/ሩ እንዲሁም በሌሎች አገራት መንግስታት እንደሚደረገው ሊዘገዩ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች ቆም ተደርገው ገንዘቡ ሕዝብን ከእልቂት ለመታደግና ወረርሽኙን ለመዋጋት ይውል ዘንድ ለማናገር ያልቻሉት ፕሬዘደንቷ፣ የመንግስት ሚኒስትሮች፣ የጠቅላዩ አማካሪወችና የምክር ቤት አባላት ሁሉ ይህ እጥረት ሊያሳፍራቸው ይገባል። ተጠያቂም ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 126 መጋቢት 25 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com